በአሳምነው ጎርፉ
በአገራችን ከተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት የተስፋ ጉዞ በኋላ ከፍተኛ የሚባል የድርቅ አደጋ ተከስቷል፡፡ በኢልኒኖ መዘዝ በየአሥር ዓመቱ በሚፈጠረው የአየር መዛባት የተከሰተው ይህ የተፈጥሮ ‹‹ቅጣት›› አፋጣኝና ዘርፈ ብዙ ርብርብ ካልተደረገበት ወደ ረሃብ እንዳይቀየር ሥጋት አለ፡፡ እርግጥ መንግሥት ‹‹ድርቅ እንጂ ረሃብ አልተፈጠረም›› በሚለው መግለጫ ፀንቶ በድርቅ አደጋው አንድም ሰው አለመሞቱን ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎች መፈናቀልና ፍልሰት አለመፈጠሩን ይናገራል፡፡
በድርቅ አደጋው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በቀጥታ ተጎጂ ሆነዋል፡፡ ከዜጎች በተጨማሪ 30 ሚሊዮን ለሚደርሱ የቁም እንስሳት የምግብና የመጠጥ ውኃ ዕርዳታ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በእርግጥም በቅርቡ የአገር ውስጥና የውጭ የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች በአፋር፣ በሶማሌ፣ በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በሰሜን ምዕራብ አማራ፣ በደቡብ ትግራይ አካባቢ ተዟዙረው እንደዘገቡት ዕርዳታ የማድረሱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ችግሩም በዚያው ልክ ይታያል፡፡
በመንግሥት በኩል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ የድርቅ አደጋውን ለመከላከል መዋቀሩ አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ እስካሁን ለጋሽ ድርጅቶችን ብዙም ሳይማፀን እስከ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ በመመደብ ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ የዕርዳታ እህልና አልሚ ምግቦች እስከ መግዛት ደርሷል፡፡ በተለይ ከውጭ የተገዛውን ከፍተኛ መጠን ያለው እህል ወደ መሀል አገር እንደደርስ አዲሱን የባቡር ትራንስፖርት ጭምር መጠቀም መቻሉ አንድ የቁርጠኝነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ግን ከተፈጥሮ የድርቅ አደጋው ባሻገር በአንድ ጀንበር ለዕርዳታ እጃቸውን የዘረጉ አሥር ሚሊዮኖች ከየት መጡ የሚለውን መፈተሽ ነው፡፡ መንግሥት ባለፉት 13 ዓመታት ገደማ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ነድፎ ያስመዘገባቸው የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የመሠረተ ልማት ለውጦች እንዳሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ያለምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ትንታኔና አመክንዮ በፕሮፓጋንዳ ተጀምሮ ‹‹ባለሁለት አኃዝ ዕድገት አለ፣ ሚሊየነር አርሶ አደሮች ተፈጥረዋል፣ 280 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በዓመት ተገኝቷል፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ 700 ዶላር ደርሷል፣ አብዛኛው አርሶ አደር በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ማምረት ጀምሯል …›› ሲባል ተከርሟል፡፡ በዚህ መሀል በአንድ ጊዜ አሥር ሚሊዮን ሕዝብ ይልሰው ይቀምሰው እንዴት ሊያጣ ቻለ ማለቱ ጠቃሚ ነው፡፡
አሁን ለማለት የተፈለገው በአንድ በኩል በተጋነነ አሃዝና ፖለቲካዊ ንግግር የተለበደ ዕድገት የተደበቁ ድሆችና የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጡ ዜጎች ነበሩ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ዕድገቱ ቢኖርም በአንድ ክረምት ለዕርዳታ ሜዳ ላይ የበተናቸው ዜጎች የዕድገቱ ተጠቃሚ አልነበሩም ማለት ነው (የፍትሐዊነት ጥያቄ!)፡፡ በተለይ ይህ የድርቅ አደጋ በእንስሳት ሀብት ክምችት ላይ የተደቀነ በመሆኑ ደግሞ፣ በተለይ የአርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን ቋሚ ሀብቶች በማሳጣት ለዓመታት ለሚሻገር ድህነት የሚዳርግ በመሆኑ የድርቁን አደገኝነት ያመለክታል፡፡
የድርቅ አደጋና እኛ
ኢትዮጵያና ድርቅ ብቻ ሳይሆን ረሃብ፣ ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ጦርነት ቢያንስ ከስድስት መቶ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የተሰናሰሉ ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከ150 ዓመታት ወዲህ እንደ ክፉ ቀን፣ አፋጀሽኝ፣ ዋግና የድርቅ ዘመን ባሉት የሰቆቃ ጊዜዎች በተለይ በሰሜንና በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሺዎች በረሃብ አልቀዋል፡፡ ለስንት አገር ሊበቃ የሚችል የቀንድና የጋማ ከብት አልቋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ብርቅዬ የዱር አራዊት አልቀዋል፣ ተሰደዋል፡፡ እፀዋቱም ከስመዋል፡፡ እነዚያን ክፉ ዘመናት ዳግም አያምጣቸው፡፡
ከቅርቦቹ የ1965/66 ዓ.ም.፣ የ1977 ዓ.ም. ድርቅ አንፃርም ኢትዮጵያዊያን የደረሰባቸው ቸነፈርና ረሃብም እስከ መቼውም ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ እነዚያ የድርቅና የረሃብ አደጋዎች በተለይ በነበሩት ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች የተዛባ ፖሊሲና በጅልነት የታጀለ ‹‹ሚስጥራዊነት›› (አልተራብንም በሚል መግደርደር) ብዙዎች ረግፈዋል፡፡ መንግሥታቱም ወደኋላ ከሥልጣን እስከ መባረር ባደረሰችው የድርቅና የረሃብ ቁጭት ተጨፍልቀዋል፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም በተለይ በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት የድርቅ አደጋዎች በተደጋጋሚ ተከስተዋል፡፡ በ1987፣ በ1994 እና 1998 ዓ.ም. እንደ ደቡብ ወሎ፣ የትግራይ ብዙዎቹ ክልሎች፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አፋርና ሶማሊያ በዋናነት ከፍተኛ የዕርዳታ እህል የሚሰፈርላቸውም ነበሩ፡፡ በእርግጥ በዚህ የኢትዮጵያ ገጽታ ምክንያት እጁን የሚዘረጋው ዓለም ቸርነትም ሆነ፣ መንግሥት የድርቅ አደጋን ለመታደግ የዘረጋው ስትራቴጂ በብዛት ወደ ረሃብ የተቀየረ ነበር ማለት አይቻልም፡፡
ለድርቅ የሚውለው ዕርዳታ ግን በአንደ በኩል ጥገኝነትና ስንፍናን በማስፈን ጠባቂነትን አባብሷል፡፡ በሌላ በኩል በዕርዳታ እህል ማጓጓዝና ሥርጭት ላይ የተንሰራፋው የሙስናና የስርቆሽ ቀዳዳ የመንግሥትን የበታች አመራር ዋና ሥራ ‹‹ዕርዳታ መስጠት›› እስኪመስለው ድረስ ሙሰኛ አድርጎት እንደነበረ፣ ኢሕአዴግ ራሱ ያለፈውን ታሪክ በገመገመባቸው ሰነዶቹ አመልክቷል፡፡
‹‹አንቺ ምጣድ ጣጂ እኔ ውኃ ልቅዳ፣
አንሰፍስፍ ተጠርቷል እንውጣ ማለዳ፤
እህል አጥቼ ነብሴ ሊወጣ፣
ሳላስብ ድንገት ዕርዳታው መጣ፤
የዕርዳታውስ ነገር ምንም አልደረሰን
አውቶብሱ መጥቶ ሀውሳ በወሰደን፤›› የሚሉ ሥነ ቃሎችና እንኑርጉሮዎች የሚያስገነዝቡት ከላይ የተነሳሁበትን እውነት ነው፡፡
እነዚህን የሰቆቃ ዘመኖች ለማስቀረት መንግሥት የተለያዩ የግብርና፣ የተፈጥሮ ሀብትና የእንስሳት ሀብት ልማት ስትራቴጂዎችን መንደፍ ብቻ አልበቃውም፡፡ ይልቁንም ጠባቂነት፣ ስንፍና፣ ዕርዳታ ልመና፣ አባካኝነትና ድግስን የመሳሰሉ ኋላቀር የአርሶ/አርብቶ አደሩ ልማዶችን ለማስቀረት፣ በየአካባቢው አድካሚ የንቅናቄ ሥራ መሥራቱ ይታወቃል፡፡ ቆጣቢነትን፣ የተለያዩ የምርታማነት ማሳደጊያ ሥልቶችን ከመጀመር ባሻገር፣ ደርግን ሲተችበት የኖረውን የሠፈራ ፕሮግራም (የመንደር ምሥረታ ብሎታል ስሙን) በክልል ደረጃ ወስኖ ለመተግበር ጥረት አድርጓል፡፡
እነዚህና ሌሎች የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተውና ከፍተኛ የአገሪቱ ሀብትም በግብርናው ዘርፍ ላይ እየፈሰሰ ብቻ ሳይሆን፣ አርሶ/አርብቶ አደሩም ጉልበቱን በስፋት ተጠቅሞ ምርታማነት ጨምሯል፡፡ እውነት ለመናገር የተፈጥሮ በደልም ስላልተጨመረበት በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት ይህ ነው የሚባል የድርቅ አደጋና የዕርዳታ ጥሪ አልተሰማም፡፡ ይህ ማለት ግን ከላይ እንደተገለጸው ‹‹የአድገናል ጫጫታው›› ደፍቋቸው እንጂ የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠ፣ በየጊዜው የዕርዳታ ድጋፍ የሚፈልጉ፣ በልመና ጉሮሮአቸውን ለመድፈን ምንዱባን ሆነው የሚጠብቁ፣ ወዘተ. በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡
የድርቅ ፖለቲካና የጨሰው አቧራ
ዘንድሮ እንደተለመደው በየአሥር ዓመቱ የዝናብ እጥረት ብቻ ሳይሆን፣ መቆራረጥና መዛባት ቀላል በማይባል ደረጃ የቀሰቀሰው የድርቅ አደጋ አለ፡፡ ያለጥርጥር የመከላከል አቅማችን በማደጉ እንጂ ከ1987 እና 1998 ዓ.ም. የድርቅ ሥጋቶች የባሰ፣ ከ1977 ዓ.ም. ድርቅ የማይተናነስ አደጋ ነው የተደቀነብን ይሉታል ሙያተኞች፡፡ በቀጣዮቹ ወራት የጎርፍ ሥጋት ይዞ መምጣቱ መገመቱም የስፋቱን ቀላል አለመሆን ያሳያል፡፡
ይህን ተከትሎ የገዥው ፓርቲና መንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚቃወሙ ወገኖች ከፍተኛ የሚባል አቧራ አስነስተዋል፡፡ በውጭ በሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን፣ ቢቢሲን በመሳሰሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎችና በተለያዩ ድረ ገጾች አልፎም በማኅበራዊ ድረ ገጽ አጀንዳው ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ጉዳዩ ትኩረትን የሳበው ‹‹ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ስለተቸገሩ እናግዛቸው…›› በሚል አቀራረብ ቢሆን ምንም አይደለም፡፡ ይልቁንም ድርቁ በተፈጥሮ አደጋ የመጣ መሆኑን ዘንግቶ መንግሥት ያመጣው ቁጣ እንደሆነ መቀስቀሱ ነው፡፡ አለፍ ሲልም በአገሪቱ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ሙስና በመንገሡ ከፈጣሪ የተሰነዘረ በትር እንደሆነ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ይህንን ፖለቲካዊ ገጽታ ያለው ጩኸት በብዙኃኑ ላይ ለማስረፅ ደግሞ ከሥነ ምግባር ውጪ በ1977 ዓ.ም. ድርቅ መላውን ዓለም ያሳዘኑ ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎች፣ ከዚያ በኋላም በሱዳንና በሶማሊያ የድርቅ አደጋ የተስተዋሉ ምሥሎችን እስከመጠቀም ተደርሷል፡፡
እዚህ ላይ በአንድ እውነት መስማማት ያስፈልጋል፡፡ ድርቅም እንበለው ረሃብ ወይም ድህነትና ኋላቀርነት ከፖሊሲ መጣመምና ድክመት አይመነጩም ሊባሉ አይችሉም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ተፈጥሮ ያላት አሉታዊ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ሳይዘነጋ፣ የድርቅና የረሃብ ፖለቲካ በቀጥታ ከመንግሥታት ፖሊሲና የአስተዳደር ሥርዓት ጋር መገናኘቱ ስህተት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በተጋነነና በሐሰት መረጃ ሥልጣን ላይ ያለውን የመንግሥትን እግር በመጥለፍ ለመጣል መሞከሩም ሆነ የአገርን ገጽታ መልሶ አመድ ለማልበስ ጥረት መደረጉ፣ ይተች እንደሆነ እንጂ ሥርዓቱ ከችግሩ ጋር ለምን ተነሳ ሊባል አይችልም፡፡
በዚያው ልክ ሥርዓቱን ወደ ቀድሞዎቹ ኢዴሞክራሲያዊና አሃዳዊ አስተዳደሮች ተርታ ለማሠለፍ የተደረገው ዘመቻም አሳማኝ አይደለም፡፡ በተለይ ሰው ያለቀበትም ሆነ የተፈናቀለበት ተጨባጭ ማስረጃ እንደሌለ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በገለልተኝነት ባረጋገጡበት ሁኔታ በጅምላ ያለቁ እንስሳትንና በበፊቶቹ ድርቆች የሞቱ ሕፃናት በማሳየት በአገር ላይ የፖለቲካ ደባ መፈጸም ተቀባይነት ያለው ድርጊት አይደለም፡፡ ተናጋሪውንም ሆነ መልዕክት አስተላላፊውን ትዝብት ላይ የሚጥል ተግባር ነው፡፡
በተቃራኒው በኢሕአዴግአዊያኑ በኩል ያለው መከላከልም (Defencive Approach) ለተረጂው ወገን አንዳች ፍሬ ጠብ የማያደርግ አጉል ፖለቲካ መሆኑን መጥቀስ እሻለሁ፡፡ በአገሪቱ አሥር ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ/አርብቶ አደር ሕዝብ ዕርዳታ ፈለገ ማለት፣ ያውም በከተሞች ለምግብ እጥረት የተጋለጠውን አብዛኛው ነዋሪ ሳይጨምር እጅግ ከፍተኛ የሚባል አኃዝ ነው፡፡ በዚህ ላይ ዛሬ የዕለት ዕርዳታ ባይጠይቅም ድርቁ ከቀጠለ ለምግብ እጥረት የሚጋለጠውና ‹‹ቤሳ ቤስቲኒ›› የሌለው ዜጋም ምን ያህል እንደሆነ በየጓዳችን እናውቀዋለን፡፡ ይህን ገጽታ ዓይንን ጨፍኖ ለመደበቅ መሻት የሚያፈጥነው ውድቀትን ነው፡፡
አገሪቱ ለአሥራ ሦስት ዓመታት በሁለት አኃዝ በተከታታይ አድጋለች በሚለው እውነት (ፕሮፓጋንዳ) ብቻ በመታበይ፣ ‹‹ዕርዳታ ከፈለጋችሁ ስጡን ካልሆነም ፕሮጀክት አጥፈንም ቢሆን እኛው እንሸፈነዋለን›› ማለትም አጉል መግደርደር ነው፡፡
መንግሥት ብዙ የሚያኮሩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ግዙፍ መንገዶች፣ ከመቶ ዓመት በኋላ ባቡር፣ አይደፈሬውን ዓባይ በመገንባት እያሳየ ነው፡፡ ከተሞች በመቀየር ላይ ናቸው፡፡ የሰላም ጥበቃውና የዲፕሎማሲ ፖለቲካው ከፍታም የጥረት ውጤት ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች መልካም ሥራዎችን የፈጸመ ድርጅት/መንግሥት ድክመቶቹንም አብጠርጥሮ መመልከት አለበት፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ስላልሆነ ባልሄድበትም ዴሞክራሲና መልካም አስተዳዳር ማስፈን ላይም ሆነ፣ የፀረ ሙስና ትግሉ መቀጠል ላይ የተጠላለፉ ችግር እንዳለ ጥርጥር የለውም፡፡
በገጠር ያለው ድህነትም አሳሳቢነቱ ሊድበሰበስ አይችልም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በሥራ አጋጣሚ ተዟዙሬ እንደታዘብኩት ‹‹ድርቅ አልነካቸውም ዕርዳታ አይፈልጉም›› በተባሉ አካባቢዎች እንኳን የድህነት ስሜት ጎልቶ ይታያል፡፡ የምግብ ውድነት፣ የውኃ መጥፋት፣ ከገበያ ምርት መቀነስና የከብት ዋጋ ማሽቆልቆል ያለጥርጥር የድርቅ ሥጋት ምልክቶች ናቸው፡፡ በከተሞችም በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉቱ የምግብ ዋስትና ሴፊቲኔት ፈጥኖ ተግባራዊ የሚደረግላቸው ድሆች በአፅንኦት ሊታዩ ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በድርቅ ሥጋት እየዋዥቀ ባለው የምግብ እህል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ እያደቀቀው ያለው ዜጋ ስንቱ ነው?!
ይህን ለዘመናት የተከማቸና የመረረ ሀቅ ተገንዝቦ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ያላቋረጠ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ድርቁ የሚያመጣውን አደጋም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥፋት በመዘንጋትም ሆነ ‹‹በድል ዜናዎች›› ለመደበቅ መመከሩም አይጠቅምም፡፡ የባቡር፣ የግድብ፣ የመንገድም ይባል የድርጅት በዓል (የብአዴንን ፌሽታ ከደርግ 10ኛው የአብዮት በዓል ጋር ያነፃፀሩት ነበሩ) በአግባቡና በሚዛኑ መስተናገድ አለበት፡፡
ረሃብ (ድርቅ) እና ጦርነት አንድ ናቸው፡፡ ጊዜ የማይሰጡ የመንግሥትን ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ፅኑ አጋርነት የሚሹም ናቸው፡፡ ይህንን አደጋ በእኔነት ስሜት ሁላችንም ተረባርበን መቋቋምና ወገኖቻችን መታደግ ለኢትዮጵያዊነታችን የሚያኮራ ተግባር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘትም ሆነ የፖለቲካ ኪሳራ እንዳይደርስ ለመመከት የሚደረገው እሰጣ ገባ መቆም አለበት፡፡
ማጠቃለያ
ያለጥርጥር የአገራችን ድህነት ገና ተራግፎ አላለቀም፡፡ ሕዝብና መንግሥት የተቀዳጇቸው አኩሪ ሥራዎች ቢኖሩም፣ የደረስንበት ደረጃ ብዙ የሚያኩራራም ሆነ የሚያስፎክር አይደለም፡፡ አሁንም ገና ለአሥር ሚሊዮኖች ዕርዳታ ለመቅረብ የሚያስገድድ ሁኔታ አለ፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ያለው ፍልሰት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጭ የሚደረገው አስከፊ ስደት ያለጥርጥር የድህነት ጭንቀት የወለደው ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡
መንግሥት በረጅም ጊዜ ዕቅዱ መፈተሽ ያለበት የፖሊሲና የአሠራር አቅጣጫ እንዳለ አመላካች ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ቻይናን ጨምሮ ብዙዎቹ የዓለም አገሮች የሚጠቀሙበት የመልሶ ማልማትና የመልሶ ማስፈር አገራዊ በሆነ መንፈስ ሊቃኝ ግድ ይለዋል፡፡ ‹‹አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማኅበረሰብ እንፈጥራለን›› እየተባለ አሶሳና ጋምቤላ የተፈጥሮ ማንጎን የሚበላው አጥቶ ወድቆ ሲበሰብስ፣ የሰቆጣና የመተሃራ አርሶ አደር ድንጋይ ላይ ሆኖ እንዴት በችጋር ይለቅ ይባላል?! (የፌደራሊዝም ፖለቲካና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ካልታረቁ በይና የበይ ተመልካች መኖራቸው አይቀርም)
በገጠር ከግብርና ምርታማነት ማሳደግ ዘዴዎች ባሻገር የተጀመሩ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ የእንስሳት ሀብትን ጨምሮ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ጋር ማስተሳሰርና የገጠር ሥራ አጥነትና ድህነትንም መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ለሚሰጠው የቅድሚያ ቅድሚያ እየሰጡ መረባረብ ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም የአገሪቱ ዜጎች ድርሻና ኃላፊነት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትም ድርቅ፣ ረሃብና ችግር እንዲባባስ ብቻ ሳይሆን መተማመንና መልካም ግንኙነት እንዳይኖርም መታገል ያስፈልጋል፡፡ የተጣመሙ ፖሊሲዎችንና የማስፈጸሚያ ዘዴዎችንም መፈተሽ የግድ ይላል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሠፈነበት አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም መትጋት አለበት፡፡ ድርቅን ወይም ረሃብን የፖለቲካ መቆመሪያ ማድረግ ደግሞ መቆም አለበት፡፡ ድርቅ የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ የሚሰላበት መሆን የለበትም የሚባለው፣ በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ መቆመር ክልክል በመሆኑ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡