Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየሃይማኖት ሰላማችንን እንደ ተሰባሪ ዕቃ መንከባከብ አለብን

የሃይማኖት ሰላማችንን እንደ ተሰባሪ ዕቃ መንከባከብ አለብን

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በዓለማችን ከሚታየው አሳሳቢ ችግር አኳያ፣ በአገራችን ያለው የሃይማኖት ሰላም ምን ያህል ውድና ብርቅ ሀብት እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም፡፡ ባለብዙ ሃይማኖት በሆነችው ኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ በገዢዎች ምንም ተደረገ ምን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሁሉንም ችለውና ተቻችለው እያሳለፉ አብሮ በመኖር እዚህ አድርሰውናል፡፡ ይህንን በሰላም አብሮ የመኖር ቅርስ የአሁኑ ትውልድ ማስቀጠሉን የሚያረጋግጠው ዛሬ ያለንበት የመብት ንቃት ደረጃ የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ተግባር መሸከም ከቻለ ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ለታሪክ ያህል የሚሆኑ የሽብር ጥቃቶች መከሰታቸው አይታበልም፡፡ በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋ/በሶማሌ ክልል፣ በደሴ ወዘተ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት አመጣሽ የሆኑት ኢምንት ናቸው፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ አሸባሪነትን የሚያውቁት በሌላው ላይ ሲፈጸም በሚያዩትና በሚሰሙት ነው ማለት ይቻላል፡፡ መለስ ቀለስ እያለ በመሀላችን ተሸሽጎ የመኖር ዕድል ያገኘ አሸባሪነት የሚፈጥረውን የቁም ስቅል ቀምሰነው አናውቅም፡፡ በ2007 ዓ.ም. ውስጥ ሽብር ይፈጸማል የሚል ወሬ ቦሌ አካባቢ ያስከተለው ንግድ ቤቶችን እስከ መዝጋት ያደረሰ ድንጋጤ የሰርክ ቢሆን፣ ወይም የሆነ ጉዳይ ለመፈጸም ወጣ ያለ ሰው በድንገተኛ ፍንዳታ ወደ አካለ ጎደሎነትና ወደ ተበጣጠሰ ሬሳ የሚቀየርበት አዙሪት እኛ አገር ውስጥ ቢመጣ፣ ከለየለት ሞትና ቁስለኝነት ባለፈ የሚኖረው ሕይወት እንዴት ያለ በሆነ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ዕቃ አስቀምጥልኝ የሚሉ መተሳሰብ የማይቻልበት፣ ገበያ መውጣት፣ ሰው በርከት ባለበት ሥፍራ መገኘት፣ ኳስ ሜዳ መግባት፣ አውቶብስና ታክሲ መሳፈር ሁሉ የሞትና የሕይወት ሎተሪ (ፈንጂ በተቀበረበት ምድር ላይ ነፍስና ሥጋን ሸጦ እንደ መሄድ ያለ) የሆነበት፣ በየመንገዱ ድንገተኛ የፀጥታ አጥርና ፍተሻ፣ ደራሽ ሽሽትና መበርገግ የሚመላለስበት፣ መንገድ ስቶ ግራ የገባውና ቋጠሮ ይዞ የሚቅበጠበጥ ሰው ሲታይም ጥርጣሬና መራድ የሚጋሽብበት … ነፃና ሰላማዊ ኑሮ አገር ጥለው የጠፉበት፣ በእያንዳንዱ ቅፅበት ስለመኖር እንኳ እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት፣ ነፍስና ሥጋ የተፋቱበት ከቀይ ሽብር ጊዜ የባሰ ኑሮ፡፡ ይህ ገለጻ የሚያሳያው ሽብር በደፈናው ሕዝብ ላይ የሚያሳድረውን ብርገጋና ሰቀቀን ብቻ ነው፡፡

ሽብሩ ሃይማኖትን ምርኩዝ ያደረገ ሲሆን ሌላም ጉድ ይመጣል፡፡ ጥቃቱን በሃይማኖት የመጣ አድርጎ የሚተረጉም ቁጣ! ይህንን አደጋ ኢትዮጵያ ከዓረብ አገሮችም ሆነ ከአውሮፓ አገሮች ከምትለይበት የሃይማኖት ጥንቅሯ ጋር እናገናዝበው፡፡ ኢትዮጵያ ባለብዙ እምነት ከመሆኗ በላይ ክርስትናና እስልምና በቁጥርም በሥርጭት ስፋትም ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በየትኛውም ማዕዘን ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ ብንጓዝ ሁለቱን ሃይማኖቶች ተዳብለው ወይም አንዳቸው በሌላቸው ውስጥ ተካትተው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሃይማኖት ጽንፈኛ ትንኮሳና አሸባሪነት እዚህም እዚያም አለሁ የሚል ቢሆንና ሃይማኖታዊ ግጭት የሆነ ቦታ ቢቀጣጠል የሚገታው የቱ ጋ ይሆን? ማንስ ተጠቅቶ ማን ሊተርፍ? ይህ ጥያቄ ለእኛ የሃይማኖት ሰላም እጦት “ሊያጋጥም የሚችል ማኅበራዊ ችግር” ሊባል የማይችል፣ ከምድረ ገጽ የሚያጠፋ ቋያ እሳት ሊሆን እንደሚችል ያስገነዝባል፡፡ ሁላችንም የሃይማኖት ሰላማችንን እንደ ሰበበኛ የሸክላ ዕቃ መንከባክብ የሚገባን ለዚህ ነው፡፡

ለእንክብካቤ የሚሆን ነባራዊና ህሊናዊ ጥሪት አለን? ጉድለትስ?

  1. ሀብት ወደ አንድ ወገን (አካባቢ) እየተግበሰበሰ ነው ወይም ሌላው አካባቢ ከእኔ አካባቢ በሚጋዝ ሀብት እየኖረ ነው ለሚል ሐሜት የማይመች የአካባቢዎች የተመጣጠነ ልማትና ዲሞክራሲ ለሁሉም ዓይነት ሰላም የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ የናይጄሪያ ዓይነት ከሃይማኖት ጋር የሚገናዘብ አካባቢያዊ የሀብትና የልማት ተዛነፍ አገራችንን ያሳስባታል? ዕድገትና ልማት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲታይ በፌደራልም ሆነ በክልል መንግሥታት ደረጃ በሚታቀዱ የልማት መርሐ ግብሮች ውስጥ የሚገባቸውን ያህል ትኩረት ያላገኙ ሥፍራዎች ቢኖሩም፣ የትኩረት ጉድለቶቹ ከእምነት ጋር ለተያያዘ ማሳበቢያ የሚመቹ አይደሉም፡፡ አንፃራዊ ኋላ ቀርነት አለባቸው ለሚባሉ አካባቢዎች ልዩ እገዛ በማድረግ የዕድገትና የልማት ርቀትን የማጥበብ እንጂ የማስፋት አዝማሚያ አደለም እየታየ ያለው፡፡ ገዢው ክፍልም ሁሉን አካባቢ ያዳረሰ ልማት በማሳካት እፁብ ዝናን አፍሶ ገዢነቱን ለማርዘም የሚራወጥ ነው፡፡

ሀብት እያካበቱ በመደርጀት ረገድም ሃይማኖታዊ የሚባል አጥር (ገደብ) የለም፡፡ በዚህ በኩል ቅሬታ ለመፈልሰፍ የሚሞክሩ ቢኖሩ በኢኮኖሚ ሥምሪቱ ውስጥ እየታየ የመጣው የጥንቅር አዝጋሚ ለውጥና ሽግሽግ ራሱ ያሽሟጥጣቸዋል፡፡ በፖለቲካውም ረገድ፣ ከሃይማኖት ፖለቲከኛነት ውጪ፣ የፓርቲ ፖለቲካ ተሳትፎ ለየትኛው ዓይነት ሃይማኖት ተከታይ በሩ ክፍት ሆኗል፡፡

  1. መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኛነት የተገለለ መሆኑ በሕገ መንግሥት ተደንግጓል፡፡ ይህ ማለት የትኛውም ዓይነት ሃይማኖት ፖለቲካ ሆኖ በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት (ስቴት) ላይ ሊወጣና መንበረ መንግሥቱን የእምነቱ መሣሪያ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሃይማኖት ፓርቲ ሊሆን፣ ፓርቲም የሃይማኖት አቀንቃኝ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ከብሔርተኝነት ጋር የተያያዘ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ ቡድን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ተከስቶ ነበር፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የዚያን ዓይነቱን ቀዳዳ ደፍኖታል፡፡ ያ ቀዳዳ ክፍት ሆኖ ቢሆን ኖሮ የመንግሥት ገለልተኛነት የሚፈርስበት ዕድልም አብሮ ይኖር ነበር፡፡ (በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ውስጥም ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብ እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡) መንበረ መንግሥትን ከሃይማኖት ወገናዊነት የማራቅ መነሻና መድረሻ ሃይማኖቶችን መግፋት ሳይሆን፣ የትኞቹም ሃይማኖቶች በየትኛውም ሃይማኖት የበላይነት (ጫና) ሥር እንዳይወድቁ፣ እኩል ተከባሪነትና የህልውና መብት እንዲያገኙ መጠበቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ የቆነጠጠ፣ እምነትን በኃይልም ሆነ በማስገደድ መገድብንም ሆነ ማስቀየርን የሚከለክልና መሠረታዊ የሲቪል መብቶችን በማይሽር ሁኔታ ለባህላዊና ለሃይማኖታዊ የጋብቻ ምሥረታና ዳኝነት ሥርዓቶች ቦታ የሰጠ ሕገ መንግሥት ሊያዋቅር መቻሉ ሁነኛ ጥንካሬ ነው፡፡ እናም ሃይማኖት መንግሥታዊ እንዳይሆን ወይም መንግሥት ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው ሃይማኖት እንዳያጋድል መጠበቅ አንዱ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትኛውም ሃይማኖት የሌላውን ሃይማኖት ነፃነት ሳይጋፋ እምነቱን የማራመድ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የቆሙለትን እምነት በተመለከተ፣ ትክክለኛ አተረጓጎሙና አያያዙ ይህ ነው ብሎ መስበክ፣ የምእመናንን ግንዛቤና የእምነት አተገባበር በማስተማር የማበልፀግ መብት ነው፡፡ በግድ መጫን ግን መብት መድፈር ነው፡፡ መስበክ መብት እንደሆነ ሁሉ መሰበክም የማይገድቡት መብት ነው፡፡ የተሰበኩትን (የተቀበሉትን) እምነት ጠበቅ አድርጎ መያዝ፣ ላላ አድርጎ መያዝ፣ ወይም መቀየርና አለመቀየር የግለሰቡ መብት ነው፡፡ ወላጆች (አሳዳጊዎች) ልጆቻቸውን በእምነታቸው ማነፅ መብታቸው ነው፡፡ የወላጅን እምነት ይዞ ለመቆየት ግን ተወላጅ አይገደድም፡፡ እነዚህን መብቶች ለመጣስ ማንም አልተፈቀደለትም፡፡ ማንኛውም ቤተ እምነት ነባር አማኞቹን ይዞ ከመቆየት ባሻገር አዲስ ተከታዮችን ለማፍራት የማስተማር ሥራ ማካሄድን ትርጉም የሚሰጡትም እነዚህ የግል መብቶች መኖራቸውና መረጋገጣቸው ነው፡፡

እናም የእምነት ቡድናዊና የግል መብቶች እንዳይረገጡ መንከባከብ በሌላው ላይ ሲጓደሉ ሲያዩ እንኳ ነግ በእኔ ብሎ መቆርቆር፣ የራስን የእምነት ተቋምና የምእመናንን መብት የማስጠበቅም ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን መሰሎቹን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ከማስከበር ውጪ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር መወገን የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ወይም ያንን የፖለቲካ ፓርቲ ደግፉ፣ ተቃወሙ፣ አውግዙ ብሎ ለምእመናናቸው መስበክ የሃይማኖት ተቋማትን አይመለከታቸውም፡፡ ምእመናናቸው የተለያየ የፖለቲካ እምነትና ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በአንድ እምነት ውስጥ የተለያየ ፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የየቤተ እምነት መሪዎች ኃላፊነታቸው ከፖለቲካ ውገና ገለልተኛ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮቻቸውን ያለአድሎ ማገልገል ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት መወጋገን ከጀመሩ ለመንግሥታዊ ሃይማኖት መንገድ ይከፈትለታል፡፡ ፓርቲው ሥልጣን ቢይዝ ድጋፍ የሰጠው ሃይማኖትም ባለልዩ መብት ልሁን ባይ ይሆናል፡፡ ወደ ሥልጣን የሚያመራ ወይም ሥልጣን ላይ የወጣ ፓርቲ ለፖለቲካ ድጋፍ የሃይማኖት መድረክን ከመጠቀም መራቁና ይህም ቀጣይነት ማግኘቱ ሃይማኖት ፖለቲካን እንዳይፈተፍት ይከላከላል፡፡

ይህ ማለት ግን ፖለቲካና ሃይማኖት ጭርሱንን አይደራረሱ ማለት አይደለም፡፡ ቢባልም የማይቻል ነው፡፡ ከእምነት ነፃናትና እኩልነት ጋር የተያየዙ መሠረታዊ መብቶች ተደፍረው ይህንን በማውገዝ መንገድ ላይ ፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ የሆነ ፖለቲካ ፓርቲ አጥፊ ቅስቀሳ አድርጎ ሃይማኖታዊ አምባጓሮ ቢከሰት አነሳሹ ፓርቲ ተወጋዥ ከመሆን አያመልጥም፡፡ መንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትንም የሚያገናኛቸው ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ተቋማትን ወደ መንግሥት አካላት ሊወስዷቸው ይችላሉ፡፡ የሃይማኖቶች ሰላም ጉዳይ ሃይማኖቶችንና መንግሥትን ያገናኛሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚኖራቸው የበጎ ሥራና የልማት ዕቅድ ከመንግሥት የልማት ዕቅድ ጋር ተጋጭቶ ብክነት እንዳይሆንባቸው፣ የልማት ዕቅዳቸውን ከመንግሥት ጋር ቢያገናዝቡ አስተዋይነት ነው፡፡ መንግሥት ከሚያካሂዳቸው (ከሚደግፋቸው) የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥም የሃይማኖት ጉዳይ ተደርገው ሊምታቱ የሚችሉ (የሃይማኖት መሪዎችን ማብራሪያና የቅርብ ድጋፍ የሚሹ) ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በተመለከተም አብሮ መሥራት ይኖራል፡፡

ከዚህ ያለፈ መጠጋጋት ግን ለመንግሥትም ሆነ ለሃይማኖት ተቋማት ጠቃሚ አይደለም፡፡ ወሰንን አልፎ በማያገባ ለመግባትም ያጋልጣል፡፡ በደርግ ዕድሜ ማብቂያ ጊዜ ላይ እነ ሕወሓት በሃይማኖት መሪዎች “ወንበዴ፣ ያገር ጠላት” ተብለው እንዲኮነኑ የተደረገበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚያ ዓይነት ጥፋት ዛሬ ላይደገም የሚችለው በሥልጣን ላይ ያለ ገዥ ቡድን/ፓርቲ ለፖለቲካ ዓላማ የሃይማኖት ተቋማትን መገልገያ ከማድረግ ሲፆም፣ የሃይማኖት ተቋማትም መንግሥት የወደደውን መውደድ፣ የጠላውን መጥላት ይገባኛል/ይጠቅመኛል ከሚል የአስተሳሰብ ቅጥር ግቢ ሲወጡ ነው፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ለገዥው ፓርቲ ቅርበት አላቸው፣ የሃይማኖት መሪዎች ምርጫ ውስጥም የመንግሥት ስውር እጅ ይገባል የሚል ሐሜት መነገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ መንግሥትም ስለመታማቱ አይክድም፡፡ ‹‹የልማታዊ ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ›› በተሰኘ የ“ሥልጠና” ወረቀቱ ላይ፣ “በክርስትና እምነት መንፈሳዊ አባቶች ምርጫ ላይ እጁን አስገብቷል” (ገጽ 39) ‹‹ሙስሊሙም መሪዎቹን በነፃነት እንዲመርጥ አልተደረገም›› (ገጽ 41) ስለመባሉ ተወስቷል፡፡ ከመሪ ምርጫ ባለፈም “መንግሥት አልሐበሽ የሚባል የውጭ እምነት አምጥቶ በላያችን ላይ ሊጭንብን ነው” የሚል እንቅስቃሴ እንደነበር ተጠቅሷል (ገጽ 41)፡፡ ‘‘ምርጫ ውስጥ እጅን አስገባ” ከመባል የበለጠ “እምነት ሊጭንብን ነው” ተብሎ መወቀስ ከባድ ነው፡፡ “ሊጭንብን” ቃሉ ራሱ ጠጣር ነው፡፡ በግል ጋዜጣና መጽሔት፣ በሹክሹክታና በመንገድ ቅዋሜ ሁሉ ሐሜቱና ቅዋሜው ሲንፀባረቅ ነበር፡፡ ዋናው ጉዳይ የሐሜቱ እውነት ወይም ሐሰት መሆን ወይም የሐሜቱ ባለቤቶች ማንነት አይደለም፡፡

ዋናው ጉዳይ ‘መንግሥት መግባት በሌለበት ጉዳይ ገባ’ ተብሎ መታማቱ ነው፡፡ በመንፈሳዊ መሪዎቹ ምርጫ ላይ ያለው ሐሜት በተለይ የቆየ ከአቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክነት ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ (በስተኋላ እንዲያውም አቶ ታምራት ላይኔ የቀድሞውን ፓትርያርክ በማባረር እጁ እንደነበረበት ምስክርነት መስጠቱ ተጨምሮበታል፡፡) ዛሬም ነገም በመንግሥት ላይ ሌላ የጣልቃ ገብነት ሐሜት ቢመጣ “እሱማ የታወቀ አይደል!” ባዩ እንደሚበዛ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ተዓማኒነት መጓደሉ ለመንግሥትም ለሃይማኖት ሰላምም ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ ክፍተቱ ተደፍኖ “ሐሰት! መንግሥት ፈጽሞ እንዲህ አያደርግም!” ተብሎ ሐሜት የሚሸማቀቅበት ጊዜ እንዲመጣ የብዙዎች ፍላጎት ነው፡፡ መንግሥትም ለዚህ ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ሐሜቱን ሐሰት ማለት ወይም የሐሜቱን ባለቤቶች “ስውር ዓላማ” መደርደር ወይም ሐሜቱን በሥልጠና “ማጥራት” የጠንካራ ሥራ አብነቶች አይሆኑም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ልፋትም የተናጋን አመኔታ መልሶ አይጠግንም፡፡ መንግሥት ወደኋላ መለስ ብሎ ለሐሜት የዳረጉትንና ያጋለጡትን ተግባሮች ምን ምን እንደሆኑ እስካልመረመረና ለሐሜት የማይመች ያልተድበሰበሰና በተግባር የሚያሳምን ግንኙነት እስካላበጀ ድረስ ከሐሜት አይርቅም፡፡ ከሐሜት አለመራቅ ደግሞ ለጽንፈኝነት ግብዣ አሰናድቶና ቄጠማ ጎዝጉዞ እንደመጠበቅ ያለ ነገር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ላይ ላዩን በሚታየው ደረጃ እንኳ ምን ያህል ጥንቁቅ መሆን እንደሚያሻ የሚጠቁሙ አንዳንድ ነጥቦችን እንወርውር፡፡

በአንድ ወቅት ቅንጅት በመባል ይታወቅ የነበረው የፖለቲካ ቡድኖች ጥምረት አድማ ነገር በሞከረ ጊዜ፣ ከእስልምና ጉባዔ በኩል አንድ ሼክ በእስልምና ጉባዔ ስም በረመዳን ወቅት ይህን ማድረግ ሙስሊሙን መናቅና መድፈር አድርጎ መግለጫ መስጠታቸው፣ ይህንንም የመንግሥት መገናኛ ማስተጋባቱ የመንግሥት ፖለቲካንና የሃይማኖት መሪነትን በተቀራረበ ሸሪክነት ለማማት አስችሎ ነበር፡፡ ባለፈው የእስልምና ጉባዔ ምርጫ ጉዞ ውስጥ የምርጫ ሥፍራ በመስጊድ ይሁን በቀበሌ አካባቢ የሚል ውዝግብ በተፈጠረ ጊዜ፣ መንግሥት አግባብ የሚሆነው ሥፍራ ይህ ነው ብሎ አቋም በመውሰድ ፋንታ፣ ለፀጥታም ለታዛቢም አመቺነቱ ሳይዘነጋ፣ የእምነቱ ሰዎች የሚያስማማቸውን ቦታ እንዲወስኑ ቢተውላቸው የበለጠ ብልህነት ይሆን ነበር፡፡

በዚሁ ሳቢያ ከተነሳሳ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱትን ሰዎች ጉዳይ ፍርድ ቤት መርምሮና አከራክሮ ሰኔ መጨረሻ 2007 ዓ.ም. የጥፋተኝነት ብይን በተከሳሾቹ ላይ መስጠቱ፣ እውነቱ ለየ ማለት ነው የሚል እፎይታ አላስገኘም፡፡ በተጠርጣሪዎች ላይ የተዘጋጀው ዶክመንተሪ ቪዲዮ ክስ ከተጀመረ በኋላ በቴሌቪዥን እንዳይታይ በፍርድ ቤት ማሳገድ ተካሂዶ፣ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝም ለብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ ደርሶት ዝግጅቱ መታየቱ፣ ይህም  በመንግሥት ለሕግ ታዛዥነት ላይ የጣለው ጥቁር ነጥብ፣ በቲቪ በቀረበው ዝግጅት ውስጥም ከተከሳሾቹ በኩል እስላማዊ መንግሥት ስለማቋቋም ውጥንም ሆነ ስለሌላ ጥፋተኝነት ሲነገር ከተሰማ በኋላ በተፅዕኖ ተገደው የሰጡት ቃል ስለመሆኑ በጠበቃ በኩል ማስተባበላቸውና በዚሁ አቋም ሲከራከሩ መቆየታቸው አዕምሮ ውስጥ እየተጉላላ ሲከነክን ቆይቷል፡፡ ይህ ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ዋናው ሥጋት፣ ሃይማኖቶችና ፍርድ ቤቶች ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ መሆናቸው በሕዝብ ዘንድ እምነት የማግኘቱን ነገር በአግባቡ ሳያሳኩ፣ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ገትሮ የማስቀጣት ነገር ትርፉ ‘ከአሳ ጉርጎራ ዘንዶ የማውጣት’ ዓይነት እንዳይሆን ነው፡፡

የሃይማኖት በዓላትን መሠረት አድርገው መንፈሳዊ መሪዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ በእግረ መንገድ “አገራችንን ይባርክልን፤ ሰላማችንን፣ ፍቅራችንን፣ ዕድገታችንንና ልማታችንን ያብዛልን…፤” የሚሉ ዓይነት መልካም ምኞቶችን ከመግለጽ ወጣ ያሉ፣ “የዲሞክራሲ ግንባታን፣ የልማት መስመርን የማስቀጠል…” ወይም በመጪው ምርጫ በንቃት የመሳተፍ ጥሪዎች ሲሰነዘሩ ያጋጥማል፡፡ የዚህ ዓይነት ወጋዊ ጥሪዎች መንግሥትንም ሆነ መርሐ ግብሮቹን ከሚበጁት ይበልጥ ለሐሜት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የዚህ ዓይነት ጥሪዎች በውስጥ ታዋቂ የሚያመላክቱት ተቃራኒ መልዕክትም አለ፡፡ ‘በቀጣዩ ምርጫ ምእመናን በንቃት እንዲሳተፉ እናሳስባለን’ ባይነት በራሱ፣ ነገ ደግሞ በምርጫው አትሳተፉ ለሚል ጥሪ ፈቃድ የሚሰጥ ነው፡፡

መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ለማሳመን በሚጥር የ”ሥልጠና” ጽሑፍ ላይ ስለሼክ አብዱላሂ ሊቅነትና ፀረ አክራሪና ፀረ ጽንፈኛ ስለሆነ “መልካም አስተምህሮአቸው” መስካሪ መሆኑም (የተጠቀሰው ገጽ 43-4) የማያስፈልግ ብቻ ሳይሆን በእናታችሁ እሙኝ ብሎ ከመለመን የማይሻል ነው፡፡ የሼኩን አስተምህሮ መልካምነት የመመስከሩንም ነገር ሆነ በሱፊነት ውስጥ ጽንፈኝነትን ጠንክሮ የሚታገል ወገን አድርጎ የመቁጠርና ያለመቁጠሩን ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ሊቃውንቱ መተው ይበጃል፡፡ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር “በሚፈጠር መግባባት” እና “ቋሚ መድረክ” በመፍጠር ሥልት “የእምነት ተቋማት… ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መልዕክቶች እንዲያስተላልፉ ማድረግ”ን ተገቢና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው አድርጎ መውሰድማ (የተሃድሶው መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ ጥራዝ ኅዳር 2003 ገጽ 102) ከሃይማኖቶች ጉዳዮች ጋር ከመነካካት የማያድን አደገኛ ጨዋታ ነው፡፡

“ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ፆመኛ ነኝ!” ለመሆኑ፣ የዛሬ ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነትና አሻባሪነት ሃይማኖታችን ተነካ ብሎ ለማደናገርና ስውር እንቅስቃሴ ለመሸረብ ትንሽ ማሳበቢያ ብቻ እንደሚበቃው ማስታወስ ያስፈልግ ይሆን? የመንግሥት አካላትንም ሆነ የሃይማኖት ሰዎችን ሊያዳልጥ የሚችል ሌላ እውነታም አለ፡፡ ዛሬ ያለው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ካርታ ከበፊቱ በጣም የተለየ ገጽታ አለው፡፡ ከአካባቢ አካባቢ ባለ የመንግሥት ሥልጣን ውስጥ የየአካባቢው ብሔረሰባዊ ዓብይ ጥንቅር እንደሚንፀባረቅ ሁሉ፣ የዋናዎቹ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች የክምችት ገጽታም ተንፀባርቆ ይታያል፡፡ በክልላዊ የሉዓላዊ ባለቤትነት እሳቤ ውስጥ ንዑሳንን/መጤ ማኅበረሰቦችን የመዘንጋት ወይም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ባለመብትና ባይተዋር የማየት ችግር እንዳለ ሁሉ፣ በሃይማኖትም መሰል ችግር ያጋጥማል፡፡ በተለይ ውጥንቅጥነት በሚሳሳባቸው ሥፍራዎች ዘንድ ባለ ማኅበረሰባዊ ይዞታና የመንግሥት አካላት ውስጥ የአንድ ዓይነት ሃይማኖት ሰዎች ደምቀው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በዚያ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ የገልልተኝነትን ኃላፊነት የመዘንጋት ድጥ አስተዳዳሪዎችን ሊፈታተናቸው፣ ጭራሽ ሳይታወቃቸው ኃላፊነታቸው ሊጠፋባቸውም የሚችልበት ዕድል ይኖራል፡፡ በአካባቢው ዋነኛ የሆነው ሃይማኖት ተከታዮችም የራሳቸውን ሃይማኖት የአካባቢው ባለቤትና ዋና ባለመብት አድርገው ቆጥረው፣ ከዚያ ውጪ ያሉ እምነቶች መብት በእነሱ እጅና ችሮታ ውስጥ ያለ አድርገው የሚያስቡበት ስህተት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ “በአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ወይም ሠራተኞች እንዲሁም በኅብረተሰቡ አባላት የሚገለጹ የሃይማኖት አድልኦ ዝንባሌዎች (ክርስቲያን ምዕመናን በብዛት ባሉበት እስልምናን የማንኳሰስ፣ የእስልምና ምዕመናን በበዙበት አካባቢ ደግሞ በተመሳሳይ … የማንኳሰስ ስህተቶች) አሁንም ጨርሰው እንዳልጠፉ የሚታወቅ” ስለመሆኑ፣ መንግሥትም ‘‘የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ’’ በሚል የሥልጠና ወረቀቱ ላይ አስፍሯል (ገጽ 37)፡፡ የዚህ ዓይነቱ የበላይነት ስሜት የእብሪትም መፍለቂያ ነው፡፡ ላሽቆጥቁጥ፣ በማነስህ ልክ መብትህ አንሶ ይሰፈርልህ የሚል አፈናና መተናኮል ሊያፈልቅ ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ጽንፈኞች ይወዱታል፡፡ በአንድ ወቅት በጅማና በቤንሻንጉል አካባባቢዎች፣ በመንግሥት መረጃ መሠረት ሃዋርጃ የተባለ ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድን የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ግፍ ለመፈጸም የደፈረው፣ የዚህ ዓይነት አካባቢያዊ የባለቤትነት ትምክህትን መንደርደሪያ አድርጎ ነበር፡፡

የሌላውን የእምነት ነፃነት ሳይተናኮሉ እምነት በግልም ሆነ በቡድን የማራመድ (የማምለክ፣ የመማርና የማስተማር) መብት በቁጥር የማይገደብ (የማይሸረፍ) እኩል መብት መሆኑ ሲዘነጋ፣ የሃይማኖት ሰላምም ዋና ውሉን ሳተ ማለት ነው፡፡ የእምነት እኩልነትን የማስከበርና የመብት ጥሰቶችን የሚከለክል ጤናማ (ኃይጅናዊ) አመለካከት፣ ጨዋ የሃይማኖቶች ግንኙነትና የእምነት አተገባበር የማዳበር ሥራዎች መሬት መንካት ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ እንዲሁም በየትኛውም ደረጃ ያለ የአስተዳደር እርከን ሕዝብን ከየትኛውም ዓይነት ጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በዝንጉነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይወጣ ለሚደርስ ጥፋት ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡ ሃዋርጃዎች ጅማ አካባቢ በአንድ ምሽት ብቅ አላሉም፡፡ አስቀድሞ ትኩረት ቢደረግባቸው ኖሮ ያንን የመሰለ ዘግናኝ ነውር ለመፈጸም ባልቻሉ ነበር፡፡

  1. ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና በኩል የሚመጣ ጽንፈኝነት ነገረኝነት የሚጀምረው ከአመለካከቱ ነው፡፡ ሌሎች እምነቶች ከእሱ አጠገብ እኩል የመኖር መብት እኩል ክብር ያላቸው ሆነው አይታዩትም፡፡ በራሱ ሃይማኖት ውስጥ ሳይቀር ለዘብተኛ አማኝ ወይ ሌላ ስንጣሪ መኖር ብሎ ነገር አይቀበልም፡፡ “ትክክልና የተቀደሰ” ከሚለው እምነት ውጪ ያለ ሁሉ የክህደት/የርኩሰት ወይም የሰይጣን ዓለም ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አመለካከት አያኗኑርም፡፡ “የገሃነም/የሳይጣን” ዓለምና “የቅድስና” ዓለም እንዴት ይኗኗራል? ከሰይጣን ማደሪያ ጋር መነካካት መርከስ ወይም ከገሃነም ጋር መነካካት ይሆናል፡፡ ይህን የእርኩሰትና የዘለዓለም ሞት ሠፈር የማስወገድ፣ የማፅዳትና በቅድስና የመተካት ኃላፊነትና ተግባር ከሰማይ የተሰጠው ደግሞ ለእሱ (ለጽንፈኛው) ነው፡፡ ሲሰብክ እንኳ ድርጊቱ ሆኖ የሚታየው ማስተማር ሳይሆን ከዘለዓለም እሳት/ሞት የማትረፍ ሥራ ነው፡፡ ቅድስና ከእኔ ጋር ብቻ ያለ (ሌላው ሁሉ የርኩሰት ጎዳና) ብሎ የሚል እምነት ንዑስ እንኳ ቢሆን ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሁሉ ተሰቅዘውለት እሱ ለመናኘት፣ የሥርዓተ ትምህርት ሰፋሪና የትምህርት ቤቶች ቃኚ ለመሆን ዕድሉን ቢያገኝ አያቅማማም፡፡ የዚህ ዓይነት ጽንፈኛ ፍላጎቶች በኦርቶዶክስ ክርስትና፣ በፕሮቴስታንት ክርስትና ፍልቃቂ እምነቶች ሆነ በእስልምና ውስጥ ያጋጥማሉ፡፡

የዓለማዊ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት በሃይማኖት እንዲቃኝ፣ ፀሎትና ስግደት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲገባ መፈለግ የሃይማኖት ጭቆናንና የመንግሥትና የሃይማኖት ዝምድናን መልሶ መጥራት ነው፡፡ እንደየአካባቢው ሁኔታ ዋነኛ የሆነው ሃይማኖት ትምህርት ቤት ውስጥ ይግባ ቢባል በዚያ አካባቢ ያሉ ንዑስ ሃይማኖቶች ተጨቋኝ ይሆናሉ፡፡ አንዱ ዋና የሆነ ሃይማኖት ሌላ ቦታ ላይ ንዑስ ሆኖ ይገኛልና ጭቆናው ለራሱም መድረሱ አይቀርም፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች በየበኩላቸው የሚሰማሩባቸው የየብቻ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሯቸው ማሰብ በመንግሥትም ሆነ በግል ሊሟላ የማይችል ቅዠት ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ የትምህርት ቤት ልዩነት ሳይኖር ለየትኛውም እምነት ተከታዮች የፀሎት፣ የስግደትና የእምነት ክበብ መብት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተፈቀደ ይሁን ማለትም የትምህርት ሥራ ይመሳቀል፣ የትምህርት ቤቶች ሰላም በእምነት ንቁሪያና መሸራደድ ይበጥበጥ ብሎ መልቀቅ ነው፡፡

ጭንቀታችን ጽንፈኛ ፍላጎት ቦታ አግኝቶ እንዲረካና እንዲያድብ ከሆነ ጽንፈኝነት አልገባንም ማለት ነው፡፡ ለጽንፈኝነት የሚታየው መብትና የመብት መጣስ ብሎ ነገር ሳይሆን ገሃነምና ገነት ነው፡፡ ጽንፈኝነት መብት አክብሮና ተቻችሎ ኗሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ገሃነም የመግባት መብትን ከማክበር ይልቅ በግድ ገነት ማስገባት ይበልጥበታል፡፡ ሃይማኖት ለወጥክ ብሎ ከዝምድና ማግለልና ካልገደልኩ ባይነት የሚከሰተው ለውጡን መብት አድርጎ ከማየት ይልቅ ወደ ቅስፈት (እርኩሰት) መግባት አድርጎ ከመቁጠር ነው፡፡ እስላማዊ ጽንፈኝነት ባለጉልበት በሆነበት አካባቢ እምነትን በግድ ማስቀየርና ማባረር፣ ሲከፋም ግድያ የሚያካሂደው ለዚህ ነው፡፡ (በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያለ ከሌላው ሃይማኖት ጋር ጎን ለጎን ተከባብሮ ከመኖር ይልቅ፣ ሃይማኖታዊ አብዮት መሳይ አጥለቅላቂ ለውጥ ማምጣት የሚታየው፣ የአንዱ ወይ የሌላው እምነት ተከታይ መሆንን ከመብት የማይቆጥር፣ ከእሱ ውጪ ያለውን ሁሉ የክህደትና የቅስፈት መናኸሪያ አድርጎ የሚመለከትና አትቀላቀሉ አትነካኩ ብሎ የሚቀሰቅስ አደገኛ የጽንፈኝነት ዝንባሌ ነው፡፡ በሰይፍ ከሚቀጡትና እምነት ከሚያስቀይሩት የሚለየውም በደረጃ ብቻ ነው፡፡)

በትምህርት ቤቶች ውስጥ እምነቶችን የማራመድ ነገር ያሳሰበን ለመብት ማሰብ ከሆነ ከትምህርት ቤት ውጪ መብቱን ማስከበሪያ መንገዶች መቼ ጠፉና? መኖሪያ ቤት፣ ቤተ አምልኮ፣ የሃይማኖት ትምህርት ቤት፣ የሃይማኖት ጋዜጣና መጽሔት፣ ወዘተ ሁሉ አሉ፡፡ ተማሪዎቻችን (ልጆቻችንን) በሃይማኖታዊ ግብረ ግብነት ለማነፅ አማራጮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ዓለማዊ ትምህርትም ከሥነ ምግባር ጋር አይቃረንምና ትምህርት ቤቶች ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር መጣበቅ ሳያስፈልጋቸው፣ ተማሪዎቻቸውን በመልካም ምግባር ማነፅ ይችላሉ፣ በደንብ ከተሰናዱ፡፡ ከትምህርት ቤቶች ባሻገር፣ ሃይማኖታዊ ያልሆነ የሥራ ገበታን ለእምነት ማሰራጫነት መጠቀም አደገኛ የምግባር ጉድለት ነው፡፡ የገበያና የመጓጓዣ ሠልፎችን፣ አውቶቡሶችን የስብከት መድረክ አድርጎ መጠቀም፣ ወደ ሥራ የሚበር ሰውን “አንዴ ላናግርህ” ብሎ ወይም ቤት አንኳኩቶ ልስበክህ ማለት ከትንኮሳ ይቆጠራል፡፡ በእነዚህ ዓይነቶቹ ስብከቶች ውስጥ አልፈናል፡፡ ስድድብ፣ ንጭንጭ፣ የድብድብ ክስተቶችም አጋጥመውናል፡፡ አግባብ ባልሆነ ቦታ ልስበክ ከመባሉ ይብስ የአሰባበኩ! እምነትና ፅድቅናን ከቶ ከዚህ በፊት ሰምቶ ለማያውቅ ከኃጢያትና ከዘለዓለም ሞት እኔ ላድናችሁ፣ ሌላ መዳኛ የላችሁም የሚል የዚህ ዓይነት አተያይ፣ “እኛን ያልዳንን አድርጎ መዳቢ አንተን ማን አደረገህ?! እኛ ሃይማኖት የለንም?!” የሚል ቱግታን ይቆሰቁሳል፡፡ መንገድ ላይ እምነትን ማሰራጨት ቢያስፈልግ እንኳ፣ የሚሻ እንዲወስድ ጽሑፎችን በመደቀን ብቻ መቆጠብ ጨዋነትን የተላበሰ ነው፡፡

አግባብ ባለው ሥፍራና የመገናኛ ዘዴ እምነትን በመስበክ ረገድም የሌላውን እምነት በመንቀፍ ላይ መመሥረት በእኛ ሁኔታና የሥልጣኔ ደረጃ ጤናማ አይደለም፡፡ በምዕራቡ ዓለም የትኛውንም ሃይማኖት ከመተቸትም ባለፈ ማሽሟጠጥም የንግግር ነፃነት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሃይማኖት ስላልተቸንና ስላላሽሟጠጥን የሚጎድልብን የለም፡፡ ነቀፋና ሽሙጡን እንሞክር ብንል ሃይማኖትን በሃይማኖት ላይ እስከ ማስነሳት የሚሄድ ጣጣ ልንጎትት እንችላለን፡፡ ምዕራባውያኑም አሽሟጠውና ተሳልቀው የእስላማዊ ጽንፈኛ አሸባሪነት ጥርስና ጥቃት ውስጥ ከመግባት በቀር ያተረፉት ነገር የለም፡፡ ከፋይዳ ቢስ ሽሙጥ ፋንታ፣ ዴሞክራሲና የሐሳብ ነፃነታችን ለምን በጽንፈኛ አሸባሪነት ተጠመደ? ከወጥመዱስ እንዴት መውጣት ይቻላል? በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ላይ ቢያነጣጥሩ ፍሬው ለሌላውም የሚፈይድ ውጤት ባመጡ ነበር፡፡

የሃይማኖት መተቻቸት ፀብ ያማዝዛል ብሎ መጠንቀቅና ትችትን በዱላና በጥይት መቅጣትን ተገቢ ብሎ መፈጸም በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ መምታታት የለባቸውም፡፡ ነቀፋና ዘለፋ፣ አምባጓሮ የመጀመር ወይም በቱግታና በጋጋታ የመቅጣት መብትን አያጎናጽፉም፡፡ የዚህ ዓይነት ዕርምጃ (በአንድ ሰው ተፈጸመ፣ በሺሕ ሰው) መብት የሚረግጥ ወንጀል ነው፡፡ እምነቴ ወይም ብሔረሰቤ ተነካ ብሎ በጋጋታና በግንፍልነት የኃይል ዕርምጃ መውሰድን ተገቢ መብት አድርጎ ማሰብ እጅግ አደገኛ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ተሰራጨ ማለት ወደ ሕግ መሄድን የጋጋታና የቱግታ ዕርምጃ እየተካ፣ በየአሉባልታው ሁሉ ዘራፍ እንዲል መሠረት አገኘ ማለት ነው፡፡ የጋጋታ ዕርምጃ አዙሪት ውስጥ ከተገባ በሕግ የተፈቀደ መብት እስኪመስል ድረስ ሊያምስ ይችላል፡፡ ፓኪስታንን የሚያብጣት አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡

  1. የይሁዲ ሃይማኖት፣ ክርስትናና እስልምና ከፍጥረት አመጣጥ አንስቶ ብዙ የተወራረሱ ነገሮች አሏቸው፡፡ ሦስቱም ዘንድ ተመሳሳይ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል እነዚያው ተመሳሳይ ጉዳዮች የተለየ አተረጓጎምና ዝርዝር እንደየእምነቱ ይዘው የሚገኙበት ሁኔታ አለ፡፡ እስልምና በራሱ አተረጓጎም ስለሙሴ፣ ስለአብርሃምና ስለያዕቆብ ልጆች፣ ስለጠቢቡ ሰለሞን፣ ስለክርስቶስና ስለማርያም፣ ወዘተ ቢያወራ በክርስትና ውስጥ መግባቱ እንዳልሆነ ማወቅና አተረጓጎሙን ለየቤተ እምነቱ መተው ከማያስፈልግ ንቁሪያ ያድናል፡፡ ከጊዜ ጊዜ በሚቀርብ የታሪክ ማስረጃና በክርክራዊ ሎጂክ እየተመራ እምነቱን የሚያስተካክልና የሚያጣራ ሃይማኖት እስከ ዛሬ ድረስ አለመታየቱን ማጤንም፣ ትርፍ የለሽ የሃይማኖት ክርክር ውስጥ ከመግባት ለመቆጠብ ይበጃል፡፡

የሃይማኖቶችን የእምነት ስንክሳር ለየራሳቸው ብንተውም፣ በታሪክ ውስጥ ስለነበራቸው አኗኗር ሚዛናዊና እውነታዊ ዕውቀት መያዝ ጭፍን ፈራጅ ላለመሆን ያስፈልገናል፡፡ ነባር እምነትን ተጋፍቶ ብቅ የሚል እምነትም ሆነ ሳይንሳዊ ግኝት በቀድሞ ጊዜ የህልውና ፈተናው ቀላል አልነበረም፡፡ ክርስትናም ሆነ እስልምና በየተነሱበት ወቅት መሳደድ ደርሶባቸዋል፡፡ ሁለቱም በስብከትና በሰላም መንገዶች እንደተስፋፉ ሁሉ፣ በሰይፍና በጎራዴም እየዘመቱና እየተዘማመቱ ተስፋፍተዋል፡፡ አገርና አኅጉር ለተሻገረ ዘውዳዊ ኢምፓየር መስፋፋት ክርስትና ርዕዮተ ዓለም ሆኖ እንደነበር ሁሉ እስልምናም እንደዚያ ሆኖ ሠርቷል፡፡ በቅድመ ዴሞክራሲ አገዛዞች ሁሉ ዘንድ የመንግሥትና የሃይማኖት ቁርኝት የነበረና ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አስገባሪ ሥርዓት ታሪክ ውስጥ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የአገዛዙና የገዢዎቹ ዓይንና እስትንፋስ ሆኖ መኖሩ ወቸው ጉድ የሚያሰኝ ክስተት አይደለም፡፡ በኦርቶዶክስ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖትነት ሥር ሌሎች ሃይማኖቶች ተጨቁነው መኖራቸውም የማይመለጥ ክስተት ነበር፡፡ በኃይል ሃይማኖት ማስለወጥ፣ እምቢ ያሉትን መግደል፣ አንዱን እምነት ተናቂ ሌላውን ተከባሪ ማድረግ ከሥር በዋሉ ሃይማኖቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥታዊው ሃይማኖትም ውስጥ በተፈጠሩ  አፈንጋጭ ዝንባሌዎች ላይ ተካሂዷል፡፡

ተጨቋኝነቱ ከእምነቶች ተፈጥሮ (ባህርይ) ጋር ግንኙነት እንደሌለው ሁሉ፣ ጨቋኝነቱም የጭቆና መንበር ላይ ከተቀመጠው ሃይማኖት ዓይነትነት (ማንነት) ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ የትኛውም እምነት ከላይ በተቀመጠበት (የመንግሥት ሃይማኖት በሆነበት) ሥፍራ ጭቆናውን አስነክቶታል፣ እያስነካውም ነው፡፡) በቅድመ ዴሞክራሲ አገዛዝ ውስጥ ስለምን የሃይማኖት ጭቆና ተደረገ የሚሉ ቁጭት ግራር ለምን እሾህ ኖረው ብሎ የመቆጨት ያህል ከንቱ ነው፡፡ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነትን ባለማክበሩ ያለፈውን ዘመን ለመውቀስ መነሳትም በድሮ ጊዜ ላይ የዛሬን ፍርድ መስጠት ይሆናል፡፡ ያኔ እንኳን በሥርዓት ደረጃ በግለሰብ ደረጃ እንኳን “ሃይማኖቶች እኩል መሆን አለባቸው፣ መንግሥት ሃይማኖት ሊኖረው አይገባም” የሚል አሳቢ የሚፈጠርበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ እንደዚያ ዓይነት ግለሰብ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ እንኳ አዕምሮው የተነካ ወይ ጋኔል የሰፈረበት የጉድ ፍጥረት ተደርጎ ከመታየት አይዘልም ነበር፡፡ ዛሬ ስለሐሳብና ስለእምነት ነፃነት እያወራን ባለንበት ጊዜ እንኳ እኩልነትንና ነፃነትን ከማክበር የሚጎትቱ ዝንባሌዎች እየተፈታተኑን ሳለ፣ የእኩልነትና የፍትሕ እሴት ያልነበረውን ዘመን ባልነበረው ግንዛቤና እሴት መፍረድ አግባብ የለሽ ከመሆንም በላይ ሙልጭ ያለ አድሎኛነት ነው፡፡

አንድ ሃይማኖት የአገርና የመንግሥት መታወቂያ የተደረገበትን ዘመን የሃይማኖት ጫና (በደል) የሌለበት አድርጎ ማድበስበስ እንደማያግባባ ሁሉ፣ ስንት ነገር ተፈጽሞባችኋል እንካችሁ እያሉ በደል መደርደርም ከታሪክ ተምሮ ዛሬን ለማቃናትና አስማምቶ ለማኗኗር አንዳችም ድርሻ አያዋጣም፡፡ ጭቆናን ሲዘረዝሩ ጨቋኝነቱ ከመንግሥት ባለሃይማኖትነት የሚመጣ መሆኑን ግራ ቀኝ እያጣቀሱ ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ዓይነት አተያይ እስካላበጁ ድረስ በክርስቲያናዊ የበላይ ገዢነት ውስጥ የተካሄደውን የውድና የግድ የክርስትና መስፋፋትና በእስላማዊ የበላይ ገዢነት ትግል በኩል የተደረገውን የእስልምና መስፋፋት በአንድ ዓይነት ሚዛን ለመረዳት እንቸገራለን፡፡ ከየሃይማኖቱ አኳያ የተወረወሩ አድሎአዊ ፍርዶችንም ማቃናት ይሳነናል፡፡ የአህመድ ኢብራሂምን የበላይነት ዓመታት አንዱ የቁጣና የውርጅብኝ ዘመን አድርጎ ሲስል፣ ሌላው የእስልምና አርነት ትግል አድርጎ መቁጠሩ አመለካከትን የሆድና የጀርባ ያህል እንዳራራቀ ይቆያል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ንትርክ ጽንፈኞች ይነግዱበታልና የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

  1. የአንድ ኅብረተሰብ ወጣት በባህል ልሽቀት መበሸቃቀጥ ሲደርስበት ኦርጅናሌ ማንነቱ ተሰልቦ ግልባጭነት መለያው (አይደንቲቲው) የሆነበት ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ውድቀት ለሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት መነሳሻ ሰበብ ቢሆን አያስገርምም፡፡ “ኢትዮጵያን አይድል” የዘፈን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተጀመረበት ሰሞን የዳኞቹ ለተወዳዳሪው ስሜት ያልተጨነቀ የድክመት ነገራ፣ ከነሽርደዳና ፌዘኛ ሳቅ፣ እንኳን ተወዳዳሪዎቹን ተመልካቾችንም ያስደነገጠና ሰዎቹን ምን ነካቸው ያሰኘ ነበር፡፡ ነገሩ የተገለጸልን “የአሜሪካን አይድል”ን ውድድር አካሄድ ስናይ ነው፡፡ ለካ ያን ሁሉ ዱብ ዕዳ ያመጣብን የአሜሪካ ዳኞች እንዳደረጉት የማድረግ አባዜ ኖሯል፡፡ የተማረውና ምራቁን የዋጠው ሰው መቀዳት የሌለበትና ያለበት ከነልኩ ጠፍቶት ይህን ያህል ከዞረበት፣ ትኩስ ወጣት ምን ያህል ለከፋ ልሽቀት የተጋለጠ እንደሆነ ማሰብ ነው፡፡

ዛሬ ከምዕራብም የአሜሪካ ባህል (ፊልም፣ መዚቃ፣ ዳንስ፣ አለባበስ፣ የአስተሳስብና የአነጋገር ፈሊጥ፣ ወዘተ) በዘመኑ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂ አማካይነት ዓለምን ከዳር ዳር እየቃኘው ነው፡፡ እንኳን ሌላው ዓለም፣ አውሮፓም ከተቃኚነት አላመለጠም፡፡ በኢራን ድርሰቶችና ፊልሞች ውስጥ እንኳ ሆሊውዳዊ የአስተሳሰብ ፈሊጦች ውስጥ ውስጡን ሲሹለከለኩ እናገኛለን፡፡ ከዓለማዊው (ግሎባል) የባህልና የአስተሳሰብ ልውስውሶሹ ሒደት ማምለጫ ጎሬ እንደሌለም የታወቀ ቢሆንም፣ ማምለጥ አለመቻሉ ጠቅላላ ምርኮኛ ለመሆን ምክንያት አይሆንም፡፡ የሆሊውድ ፊልሞች (በተለይ ለወጣቶች የታለሙት) ዳንስና ሙዚቃን፣ የብስክሌትና የሸርተቴ ስፖርቶችንና የመሳሰሉትን የሚያዛምቱ ብቻ አይደሉም፡፡ ከሙዚቃና ከዳንስ ጋር የመጠጥ ድግሱንና ስካሩን፣ ከስካሩ ጋር እፁና እስከ ሰዶማዊነት የሰፋ የወሲብ ልምምድን ያቀናበሩ ጠንቀኛ ፊልሞችም ሆን ተብለው ይረጫሉ፡፡ የልሽቀት መከላከያ የሌላቸው (የአሜሪካ የሆነን ነገር ሁሉ መቅዳት ሥልጣኔ ሆኖ የሚሰማቸው) ወጣቶቻችን የኮረጁት ዳንሱን፣ ሙዚቃውን፣ “ቴዲቤር” የሚባል አሻንጉሊት በስጦታነት መለዋወጥን፣ አሻንጉሊትና የሳሎን ውሻ አቅፎ ማቀማጠልን፣ ሲናደዱና ደም ሲያዩ ባኞ ቤት ገብቼ እንደ ፈረንጆቹ ላስመልስ ማለትን ብቻ አይደለም፡፡ የመጠጥና የዕፅ ሱሰኝነት፣ የወሲብ ፊልም ሱሰኝት፣ የወሲብ ሱሰኝነት፣ የተመሳሳይ ፆታ ወሲብ (የሴት ለሴትና የወንድ ለወንድ)፣ የቡድን (የፍርርቅ) ወሲብ፣ ወዘተ እንደ ሰርዶ ውስጥ ለውስጥ  እየተዛመቱባቸው ነው፡፡ ረሃብ መብት እንዳልሆን ሁሉ የዚህ ዓይነቱ ዕልቀትም መብት አይደለም፡፡ ዋና ትግል መደረግ ያለበትም “የገና ዛፍ የእኛ ባህል አደለም” የሚሉ ዓይነት ግልብ ነገር ላይ ሳይሆን፣ ወጣቶቻችንን ከጭፍን ቀጅነት በማውጣት ላይ ነው፡፡ ይህም በስብከት መጠቅጠቅ ሳይሆን ባለብዙ ገጽ የቀረፃ ትግል ነው፡፡

  1. እስልምናን የተመረኮዘ ጽንፈኝነትና አሸባሪነት በግራ በቀኛችን እየዞረንና እየተሹለከለከ ባለበት፣ የኦዲዮ ቪዲዮና የጽሑፍ ቅብብላዊ ቅስቀሳውና የኢንተርኔት ውስወሳው የማይገደብ በሆነበት፣ እንዲህ ተደረገ የሚለው ዓለም ነክ የየዕለቱ ዜና ሳይቀር የአባባይነትና የጎንታይነት ሚና እየተጫወተ ባለበት በዚህ ዘመን ውስጥ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት ሳይበገርና ሳይታመስ መቆየቱ የሚደንቅ ነው፡፡ በዚህም ፅናቱ ለኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ሰላም ምን ያህል ባለውለታ ሆኖ እንደቆየ ሌሎች ሃይማኖቶች፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት በወጉ ሊያውቁና ሊያመሰግኑ ይገባል፡፡ የሃይማኖት ጽንፈኝነትና አሸባሪነት ከማንም ሃይማኖት በበለጠ እስልምናን መፈታተኑ ገና ገና የሚቀጥል እንደመሆኑም፣ ሌሎች ሃይማኖቶችና መንግሥት ትንንሽ ፉክክርና መጎነታተልን በማቅለልና ባለማካረር፣ ከችኩል ጥርጣሬና ስም ልጠፋ በመቆጠብ፣ “ሃይማኖት ተደፈረ ወይም በሃይማኖታችን ጣልቃ ተገባ” ለሚል ቅሬታ ሰበብ ባለመሆን ትግሉን ማገዝ ትንሹ ግዴታቸው ነው፡፡ ለዚህና በአጠቃላይ ለሃይማኖቶች ጤናማ ግንኙነት የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባዔ አናት ላይ ከመንሳፈፍ አልፎ እታች ድረስ እንዲዋቀር መወጠኑ ትክክል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቱን የሃይማኖቶች አያያዝ የበለጠ ፍትሐዊ ማድረግ፣ የሃይማኖት መከባበር ሁሉም የሚተነፍሰው ምግባር እንዲሆን መታተር፣ በጎረቤት አገሮች ያሉ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ የሰላም ችግሮች እንዲወገዱ ጠንክሮ መታገል፣ ሃይማኖትን የፖለቲካ መሣሪያ ያደረጉ ድንበር ተሻጋሪ ቡድኖችና ሃይማኖታዊ መንግሥታት ሰላማችንን እንዳይበጠብጡ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም የእስልምናን የሰላም ሃይማኖትነት ከመናገር አንድ ዕርምጃ በመሄድ፣ በዛሬው ምዕራባዊ ዓለም ሙስሊምን ይህን ያህል የሞት መልዕክተኛ ተደርጎ ለመታየት ያደረሰው ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ፊት ለፊት ሊጋፈጡት ይገባል፡፡ ሃይማኖቱ የሽብር መነገጃ መደረጉ? ወይስ ሃይማኖቱ ጠላቴ/በዳዬ የምትለውን ቀጥታ ባታገኝም በዜግነት(በዘር) በእምነት ብጤው የሆነውን ሰው በነሲብ ግደል ትፀድቃለህ ስለሚል? መልሱ የሚያመራምር ባይሆንም ሙስሊምነትን ከጽንፈኝነትና ከአሸባሪነት ጋር አዛምዶ ማየትንና መፍራትን ያመጣው እስልምናን የተመረኮዘ አሻባሪ እንቅስቃሴ መስፋፋት መሆኑን ለማየትና ከዚህ የመጣው፣ የጥርጣሬና የፍርኃት እውነታም “ሙስሊም ሁሉ ጽንፈኛ አይደለም፣ ለምን ሙስሊም ይፈራል?” ብሎ በመከራከር እንደማይቀየር ለመቀበል ይረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ይህንን አጢነው፣ ያን መሳዩ አንጓላይ ፍርኃትና ሽብራዊ መታመስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይመጣ ለአንድ ቀንም የማይዘናጋ ትግል የማድረግ ሸክም ወድቆባቸዋል፡፡

እንደ ፈተናው ትግሉም ብዙ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና አስተምህሮ ከሌሎች መስመሮች (ከሰለፊዎች፣ ከዋሃቢዎች፣ ወዘተ) የሚለይበትን ለምእመናን በቀላሉ እንዲጨበጥ አድርጎ ማንጠርና በሊቃውንቱም፣ በመምህራኑም፣ በምእመናኑም ዘንድ የአስተምህሮ ሴመኛነትን (ህብር) ለመጠበቅ የሚያስችል የትምህርት ሥርዓትን ከከፍተኛ የእስልምና ትምህርት እስከታች መድረስና መስጊድ ድረስ በአግባቡ ማደራጀት፣ ከውጭ ጋር የሚደረግ የዕርዳታና የሃይማኖት ግንኙነት ነፃነትንና የአስተምህሮ ሴመኝነትን እንዳይነካ አድርጎ ፈር ማስያዝ፣ ጥቂቶቹ ግን ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሴመኝነት ቢጠነክርም ሌሎች የእስልምና መስመሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ብቅ አይሉም ተብሎ አይታሰብም፡፡ የአስተምህሮ ሴመኝነት መጠናከር ዓብይ ጥቅሙ፣ ሌሎች አስተምህሮዎች ቢመጡ የራሳቸውን የተለየ ቤተ እምነት አቋቁመው ተከታይ ከመፈለግ በቀር መሀል ገብተው ሊያምሱ የሚችሉበትን ቀዳዳ አይሰጥም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ቱሪዝም ለኢኮኖሚያችንም ሆነ ለኅብረተሰባችን ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም››

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዙብራ ፖሎካሽቪሉ...

ከቀደምት የመስቀል ደመራ አከባበር

ዓመታዊው የመስቀል በዓል፣ መገለጫው ከሆነው ደመራ ጋር በአዲስ አበባ...

ምርቃት በመስቀል ክብረ በዓል

የመስቀል ክብረ በዓልን ከሚገልጹት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ ምርቃት ነው፡፡...

የማራቶን ባለክብረ ወሰኗ ከተዓምራዊ ጫማ ባሻገር ድሏ በታሪክ የሚዘከርላት አትሌት

በኢትዮጵያ በየዕለቱ የረሃብ፣ የመፈናቀል፣ የጦርነትና የኑሮ ግሽበት በተለያዩ የሚዲያ...