Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ድርቁና ተጓዳኝ ጉዳቶቹ ይታሰብባቸው

በአማን ዘበአማን

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ኤልኒኖ በተባለው ተፈጥሯዊ ክስተት ሳቢያ ለድርቅ በመጋለጣቸው ሚሊዮኖች ለምግብ ዋስትና ችግር ተዳርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ያደረገው አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 8.2 ሚሊዮን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ የተረጂው ቁጥር ከ15 ሚሊዮን በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ሥጋቶች አሉ፡፡

ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ከተጋረጠናቸው አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ነች፡፡ በቅርቡ በውጭ መገናኛ ብዙኃን መከታተል እንደተቻለው የደቡብ አፍሪካ ገበሬዎች ከፍተኛ ተጎጂዎች ሆነዋል፡፡ በተለይ ከብት አርቢዎች ብዙ የደከሙባቸውን እንስሳት በድርቁ ሳቢያ እያጡ እንደሚገኙ ሲናገሩ አይተናል፡፡ በኢትጵያም ተመሳሳይ ኩነቶች ይታያሉ፡፡ በርካታ የቀንድ ሀብት ያላቸው ክልሎች የአደጋው ሰለባ በመሆናቸው ከብቶች እየሞቱ ነው፡፡

እርግጥ ከከብቶች እልቂት ይልቅ ለሰዎች ሕይወት መታሰብ አለበት፡፡ ይኽም በመሆኑ መንግሥት ለነፍስ አድን ሥራዎች ትኩረት መስጠቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ መደመጡ ተገቢ ነው፡፡ መሆንም አለበት፡፡ አንድም ሰው በረሃብ እንዳይሞት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተገኙበት መድረክ ይህንንኑ ሲያስረግጡ እንሰማለን፡፡

ምንም እንኳ አሁን የተከሰተው ድርቅ በአስከፊነቱ ከፍተኛ እንደሆነ በመንግሥት ቢነገርለትም፣ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንደሌለ ወይም የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚጠበቀው መጠን ማደጉን እንደሚቀጥል መንግሥት ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ ነገር ግን ሌሎች ክስተቶች እንደተጠበቁ ሆነው ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች በኢኮኖሚው ላይ መጋረጣቸው ይታወቃል፡፡ የመጀመርያው የግብርና ምርት ይጠበቅ የነበረውን ያህል ሊሆን እንደማይችል መታየቱ ነው፡፡ በአብዛኛው አካባቢ የተዘራው ዘር፣ የአዝመራው ቡቃያ በእንጭጭነቱ መድረቁን ገበሬዎች በሐዘን ሲገልጹ ዓይተናል፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥት የሸለማቸው ልማታዊ አርሶ አደሮች ሳይቀር በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ለዕርዳታ እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን በገጠር አከባቢ ለድርቅ አደጋ የተጋለጠው ሕዝብ ቀድሞውንም በመላ አገሪቱ ለዓመታት ሲተገበር በቆየው የምግብ ሴፍቲኔትና የማኅበራዊ ዋስትና ድጋፎች ተጠቃሚ ሆኖ የቆየው ከጠቅላላው ተረጂ ሕዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ እንደሆነ መንግሥት አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምግብ ለሥራ የሚባሉ ተግባራት ላይ እንዲሳተፍ እየተደረገ የገጠሩ ነዋሪ ድጋፍ ሲያገኝ ይታያል፡፡

በአንፃሩ የከተማው ደሃ ሕዝብ ግን የምግብ ሴፍቲኔትም ሆነ የምግብ ለሥራ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ይህንን ችግር የሚያባብሰው የሰሞኑ ድርቅ ይብሱን የምግብ ሸቀጦችን ዋጋ እንዳያንር ሥጋት አለ፡፡ አቅርቦቱም ቢሆን እንኳንና ምንም አቅም የሌላቸውን ቀርቶ በደመወዙ የሚተዳደረውን፣ ጡረተኛውንና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ የሚተዳደረውን ከተሜ ትልቅ ራስ ምታት ውስጥ የሚከት አደጋ ጋርጦበታል፡፡

መንግሥት እንዲህ ያሉ ሥጋቶችን በውል የሚመክትበት፣ ይህ ክስተት በከተማ ነዋሪ ድሆች ላይ አስከፊ ችግር ሳያደርስ የሚያልፍበትን ስልት መከተል ይኖርበታል፡፡ ለገጠሩ የድርቅ ተጎጂ የሚደረገው ርብርብና መሯሯጥ ለከተማው ተጋላጭ ሕዝብም ሊዳረስ ይገባዋል፡፡ ድርቁ በሚያስከትለው የእህል ምርት እጥረት ሳቢያ ሊከሰት ስለሚችለው የዋጋ ንረት ሥጋት ስላለን መንግሥት ያሰበውንና ያቀደውን እንዲነግረን እንሻለን፡፡ የዋጋ ንረቱና ግሽበቱ እየባሰበት መምጣቱም የመንግሥት መረጃዎች በየጊዜው እያሳዩን በመሆኑ፣ ድርቅ ሲጨመርበት ደግሞ ሊከሰት የሚችለውን ከወዲሁ በመገመት የሚወሰደውን ዕርምጃ መስማት እንናፍቃለን፡፡

በሌላ በኩል የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች እንደሚያሳዩት ከ26 ከመቶ በላይ አገሪቱ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ይኖራል፡፡ ይህም ማለት በዓመት ከ3,700 ብር ያልበለጠ ገቢ እያገኘ ይተዳደራል፡፡ ይህ ዝቅተኛ ገቢ አንድ ሰው በቀን ማግኘት የሚገባውን የካሎሪ መጠን ሊያገኝ የማይችል ሆኖ ይገኛል፡፡

ከድህነት ወለልም ሆነ ከምግብ ድህነት በታች የሚኖረው የከተሞች ነዋሪ ሕዝብ ውስጥ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ 4.7 ሚሊዮኖችን ለመርዳት በማሰብ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መዘጋጀቱ እሰየው ቢያሰኝም፣ በመሠረታዊነት ግን በገቢ መጠን ልዩነት ላይ የሚታየውን ሰፊ ክፍተት ለማጥበብ የሚያስችል ሥራ መሥራት ከመንግሥት የሚጠበቅ አጣዳፊ የቤት ሥራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ራሳቸውን እያስተዳደሩ ገቢ የሚያገኙበትንና ከምግብ ድህነት ሊያላቅቃቸው የሚችል ዕቅድ መንደፉ የዘገየም ቢሆን አሌ አይባልም፡፡

በገጠር ከሚታየው ድህነት ይልቅ በከተማ የሚታየው ድህነት እያየለ መምጣቱን መንግሥት አምኗል፡፡ ይህ የሆነውም ለከተማ ነዋሪዎች የኑሮ መደጎሚያ፣ ለከፋ የኑሮ ውድነት መቋቋሚያ የሚሆን ሥርዓት እስካሁን ሳይዘረጋ በመቆየቱ እንደሆነ ማመኑን መልካም ጅምር ቢሆንም፣ የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ችግር ተጋላጭነት በዘላቂነት ለመፍታት መነሳት ብቻም ሳይሆን በቁርጠኝነት መሥራትም ተገቢ ይሆናል፡፡ ከመንግሥት ሰነድ ለመረዳት እንደተቻለው የከተማ ሴፍቲኔትን ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት ለመተግበር ከ123 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ  በመጀመሪያ ምዕራፍ ለሚተገበረው ሥራ ተገኝቷል፣ መንግሥትን ምን ያህል ከካዝናው በመመደብ የከተማ ነዋሪ ችግረኞችን ለመደጎም ቆርጧል ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሹን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

እንደሰማነው የዓለም ባንክ ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለመስጠት ወስኗል፡፡ ሌሎችም ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሲታሰብ የከተማ ድህነትን ለመቅረፍ የተጀመረው መንገድ ከጅምሩ ዕርምጃው በጎ እንደሆነ ይታያል፡፡

ይሁንና ጊዜ የማይሰጥ ችግር ውስጥ የሚገኙትን እንደ አቅመ ደካሞች፣ በሽተኞች፣ ተንከባካቢ የሌላቸውና በየጎዳናው የወደቁ ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ ደጋፊና ጧሪ ያጡ አረጋውያን፣ የአዕምሮ ሕሙማንና ሌሎችም በየጊዜው በፍጥነት እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት መቋቋም የሚችሉበት ድጋፍ ከመንግሥት ማግኘት የሕገ መንግሥት መብታቸው መሆኑም በመንግሥት የሚታወቅ ነው፡፡ 

 በጠቅላላው ድርቁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተከሰቱት ሁሉ የከፋ መሆኑን መንግሥት እየነገረን ባለበት ወቅት፣ በድርቁ ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ ተጓዳኝ ጉዳቶችን ከወዲሁ መከላከል የሚያስችሉ የመንግሥት አፈጣኝ መፍትሔዎችና ዕርምጃዎች በግልጽ ይታወቁ እንላለን፡፡

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት