– የፋብሪካ ግንባታውን 70 ከመቶ አጠናቋል
በሆለታ አካባቢ በ150 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በመገንባት ላይ ያለው የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ 70 ከመቶ ያህሉ መጠናቀቁ ቢገለጽም፣ በኃይል አቅርቦት እጥረት ሳቢያ ለከፍተኛ ወጪና ኪሳራ መዳረጉን ገለጸ፡፡ የቀረውን ግንባታ በቶሎ ለመጨረስ የሚያስችል እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ መሆኑንም የኩባንያው ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን እንዲያንቀሳቅስበት የገባለት የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከሚፈለገው በታች ሆኖ በመገኘቱ ሊጠቀምበት እንዳልቻለም ተገልጿል፡፡ በዚህ የተነሳም በኪራይ በተገኙ ስድስት ጄኔሬተሮች መገልገል ግድ ሆኖበታል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም የአክሲዮን ማኅበሩ የኤሌክትሮኒክስና ኢንስትሩመንቴሽን ክፍል ኃላፊ እንደገለጹት፣ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገው የኃይል መጠን ከ380 እስከ 400 ኪሎቮልት ሲሆን የቀረበለት የኃይል መጠን ግን 320 ኪሎቮልት ነው፡፡ በዚህ የኃይል መጠን ምንም ዓይነት ሥራ ማከናወን ስለማይቻል በጄኔሬተሮች መጠቀም ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በዚህ የተነሳ ለጄኔሬተሮቹ ኪራይና ለነዳጅ ግዥ በየወሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እያወጡ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህም አክሲዮን ማኅበሩን ላልታሰበ ወጪና ለኪሳራ ዳርጎታል ብለዋል፡፡ የሚፈለገው የኃይል መጠን ቢቀርብለት ኖሮ ለአገልግሎት ክፍያ የሚያወጣው 16 ሺሕ ብር ብቻ ይሆን እንደነበር አቶ ቴዎድሮስ አስረድተዋል፡፡
‹‹ይህንን ችግር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሆለታ ቅርንጫፍና ለሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት አሳውቀናል፡፡ ለሥራ የሚያስፈልገን የኃይል መጠን እንዲቀርብልን በተደጋጋሚ ጠይቀናል፡፡ ይህም ሆኖ ምንም ዓይነት መፍትሔ እስካሁን ድረስ አላገኘንም፤›› ብለዋል፡፡
ሌላው ችግር ፋብሪካው የሚያስፈልገው የሁለት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር እስካሁን ወደ ማምረቻ ቦታው አለመግባቱ በሥራ ላይ ያስከተለው መጓተት ነው፡፡ ለኖራ ድንጋይ መፍጫና ወፍጮው በሚተከልበት አካባቢ በመገንባት ላይ ላለው የሠራተኞች መኖሪያ ቤት የሚውለውን ይህንኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት፣ አክሲዮን ማኅበሩ የሚፈለግበትን ገንዘብ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገቢ አድርጓል፡፡ ‹‹ድርጅቱ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ መስመሩን ለመዘረጋት ዛሬ፣ ነገ እያለ ያመላልሰናል፡፡ ተመላልሰንም ምንም መፍትሔ አልገኘንም፤›› በማለት አቶ ገመቹ ድጉማ፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ የምህንድስና ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ቀናው ገንዘቡ፣ ‹‹ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችለው እንቅስቃሴ የሚካሄደው ልዩ ልዩ መሣሪያዎችንና ማሽነሪዎችን በመገጣጠምና ፋብሪካውን በመትከል ተግባር ላይ በማተኮር ነው፡፡ ይህም ተግባር በስምንት ወራት ውስጥ ተጠናቆ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ላይ የማምረት ሥራ ይጀመራል፤›› ብለዋል፡፡
ከተጠናቀቁት የግንባታ ተግባራት መካከል ለማሽኖቹ መትከያ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የመሠረት ግንባታ ሥራዎች፣ ጥሬ ዕቃዎች ከተፈጩ በኋላ የሚጠራቀሙባቸው ጎተራዎች (ሳይሎ)፣ የሲሚንቶ ማቃጠያ ሥራዎችና ባለሦስት ፎቅ የላብራቶሪና የመቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ ይገኙበታል፡፡
ከዚህም ሌላ እያንዳንዳቸው 44 ሜትር በ24 ሜትር የሆኑ፣ ልዩ ልዩ ጥሬ ዕቃዎች የሚከማቹባቸው ሦስት ሼዶች ከተጠናቀቁት ግንባታዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በአንደኛው ሼድ ኖራ፣ በሁለተኛው ሼድ የአፈር ድንጋይ፣ ሸክላና ከሰል ድንጋይ፣ በሦስተኛው ሼድ ጂፕሰምና ፑሚስ ይከማቹበታል፡፡ ከዚህም ሌላ ለፋብሪካው ተከላና ለመሣሪያዎች መገጣጠሚያ የሚያስፈልጉ ዕቃዎች በተሠራላቸው ዲዛይንና ቅርጽ መሠረት እየተቆራረጡና እየተበየዱ የሚዘጋጁባቸው ሁለት የማምረቻ ተቋማትን የማመቻቸት ሥራም በመከናወን ላይ ነው፡፡
እንደ ኖራ፣ የአፈር ድንጋይና የሸክላ አፈር የመሳሰሉ ጥሬ ዕቃዎች በአንድ ላይ ተቀላቅለው ከመፈጨታቸው በፊት እያመጣጠነ ወደ ወፍጮ የሚልክ ስቴሽን ይቋቋማል፡፡ ወፍጮው ያደቀቃቸውን ጥሬ ዕቃዎች ለዚህ ሲባል ወደተዘጋጀው ጎተራ ያቀርባል፡፡ ጎተራው በአንድ ጊዜ አሥር ሺሕ ቶን የተፈጨ ሲሚንቶ የመያዝ አቅም እንዳለውና ከመሬት በላይ ከፍታው 60 ሜትር፣ የስፋት መጠኑም 18 ሜትር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ወፍጮው ጥሬ ዕቃውን በሚፈጭበት ወቅት አካባቢውን ሊበክል የሚችል ብዙ አቧራ እንደሚኖር ሲታወቅ፣ ይህንን ብክለት ለመከላከል ሲባል ወይም አቧራውን ከንጹህ አየር የሚለይና የሚያጣራ ‹‹ባግ ሐውስ›› የተባለ ማጣሪያ ስፍራም በፋብሪካው ይዘጋጃል ተብሏል፡፡ ይህ ማጣሪያ ንጹሁን አየር ውጭ ካለው አየር ጋር እንዲቀላቀልና ጠጣርና አየርን ሊበክል የሚችለውን ዝቃጭ ግን መልሶ ወደ ምርት ሒደት እንዲገባ ያደርጋል፡፡
በሚገባ ተመጣጥኖ ከተፈጨ በኋላ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ጎተራ ውስጥ የሚጠራቀመው ሲሚንቶ ወደ ማቃጠያ ክፍል ከመግባቱ በፊት አስፈላጊውን ሙቀት ማግኘት ወደሚችልበት ቅድመ ማሞቂያ መሣሪያ ክፍል ውስጥ ገብቶ ይከማቻል፡፡ ቅድመ ማሞቂያው ከመሬት በላይ 106 ሜትር ከፍታ ያለው መዋቅር ሲሆን ግንባታውም እየተከናወነ ነው፡፡
ሲሚንቶው የሚጠበስበት ወይም የሚቃጠልበት ማሽንም ከውጭ ገብቶ ለተከላ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ለተከላው የመሠረት ግንባታ ተከናውኗል፡፡ ሲሚንቶው የሚቃጠለው 1,800 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ባለው የሙቀት መጠን ሲሆን፣ ሲሚንቶው በዚሁ ሁኔታ ከተጠበሰ ወይም ከተቃጠለ በኋላ በመጋዘን ለማስቀመጥ ወይም ወደ ተከታዩ የምርት ሒደት ለመውሰድ ወደ ማቀዝቀዣ ቦታ ይሄዳል፡፡ ለዚህ የሚሆንና በግራና በቀኝ አየር የሚሰጡ መዘውሮች ወይም አየር የሚነፉ መሣሪያዎች ይተከላሉ፡፡ ይህ ማቀዝቀዣ ሲሚንቶውን ከጋለበት የምርት ሒደት በማቀዝቀዝ ወደ ቀጣዩ ሒደት ያዘጋጀዋል፡፡
ሲሚንቶው በዚህ ሁኔታ ከቀዘቀዘ በኋላ ስፋቱ 30 ሜትር የሆነና ከመሬት በላይ 22.5 ሜትር ከፍታ ባለው በአንድ ጊዜ 20 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ መያዝ የሚችል ማጠራቀሚያ ውስጥ ይከማቻል፡፡ ለዚህ የሚሆን መሠረት እየወጣለት ግንባታ የተካሄደ ሲሆን፣ ቀሪው ሥራ የማጠራቀሚያውን አካል መገጣጠም ብቻ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
አቶ መርዕድ በየነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰሜን አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ለፋብሪካው የሚፈለገውን የኃይል መጠን አለመቅረቡንና ሁለት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ መስመር አለመዘርጋቱን በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹ችግር መኖሩ ትክክል ነው፡፡ መንስዔውም በገፈርሳ ሰብስቴሽን ላይ ያለው የኃይል አቅም ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሰብስቴሽኑን የኃይል አቅም የማሳደግ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ሥራው ሲጠናቀቅ ችግሮቹ ሙሉ ለሙሉ እንደሚወገዱ ገልጸዋል፡፡