Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ ከ860 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–   የ2.5 ሚሊዮን ብር የበጎ አድራጎት ድጋፍ አደረገ

የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  861.8 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡንና የባንኩ  ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢም ዓምና ካስመዘገበው 1.9 ቢሊዮን ብር ወደ 2.3 ቢሊዮን ብር ማደጉን አስታወቀ፡፡  ገቢ የ19.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በተገባደደው የፋይናንስ ዘመን ውስጥ 19.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር የ3.4 ቢሊዮን  ብር ወይም የ21 ከመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡ የባንኩ 20ኛ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በሒልተን አዲስ አበባ ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታቦር ዋሚ በባንኩ 20ኛ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የዓመቱን የባንኩን ሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት፣ ያለፈው የፋይናንስ ዘመን መልካም አጋጣሚዎችና ፈታኝ ክስተቶች የታዩበት ዓመት ነበር፡፡ የዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አንፃራዊ መሻሻል ማሳየቱና ወደ አፍሪካ እየመጣ ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም እየበዛ መምጣቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታዩት መልካም አጋጣሚዎች መካከል ለፋይናንስ ዘርፉም በጥሩ ጎን የታዩ ክስተቶችን እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡

የወጪ ምርቶች ዋጋ በተለይም የቡናና የሰሊጥ ምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ በመቀነሱ ምክንያት አገሪቱ ያገኘችውና አሁንም ድረስ  እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ የተጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ፣ በባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ጠቁመው፣ ሆኖም አዋሽ ባንክ ያገገኛቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀም የባንኩን አጠቃላይ ገቢና ትርፍ ማሳደጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ባንኩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቦንድ ግዥ ያዋለውን የ5.3 ቢሊዮን ብር ብድር ሳይጨምር ለተለያዩ መስኮች ከዚህ በፊት የሰጠው አጠቃላይ ብድር 3.3 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግን የ36 ከመቶ ዕድገት የተመዘገበበትን የ12.5 ቢሊዮን ብር ብድር ለደንበኞች መስጠቱን የቦርድ ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በየዓመቱ የ383 ሚሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት እ.ኤ.አ. ጁን 30 ቀን 2015 ድረስ 1.8 ቢሊዮን ብር ከመድረሱም በተጨማሪ፣ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ሀብትም አምና ከነበረበት  22.1 ቢሊዮን ብር ወደ  25.2 ቢሊዮን ብር ብር ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡

አዋሽ ባንክ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች 52 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ለአልግሎት አብቅቷል፡፡ ይህም በባንኩ ታሪክ ውስጥ በአንድ ጊዜ ይህንን ያህል አዳዲስ ቅርንጫፎች በብዛት የተከፈቱበት ሊሆን እንደበቃ የገለጹት አቶ ታቦር፣ በአሁኑ ወቅት ባንኩ በጠቅላላ የሚያስተዳድራቸውን ቅርንጫፎች ብዛትም 202 እንዳደረሰ አስታውቀዋል፡፡

ሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ በኮምፒውተር መረብ የተገናኙ ሲሆን፣ የባንኩ ደንበኞችም ከየትኛውም ቅርንጫፍ ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ እንደቻሉም ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የባንኩ ደንበኞች ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች አውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖችና የግብይት መፈጸሚያ ማሽኖችን (POS) በመትከል ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት የሚሰጡ የ24 ሰዓት የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባንኩ ተጨማሪ 150 የክፍያ ማሽኖችና 600 ተንቀሳቃሽ የግብይት መፈጸሚያ ማሽኖችን ለመግዛት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ የአውቶማቲክ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖቹን ከአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋ መጠቀም የሚያስችል አሠራር ዘርግቶ ለደንበኞች ማስተዋወቁንና አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በሕንፃ ግንባታ ረገድም ላለፉት ሦስት ዓመታት በግንባታ ላይ የነበረው ባለአሥር ፎቅ ወይም ወለል ያለው የባልቻ አባ ነፍሶ ሕንፃ ግንባታ በመገባደጃው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝና፣ በዚህ ዓመት ተመርቆ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተነግሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሐዋሳ ከተማ በመገንባት ላይ ያለው ባለስድስት ፎቅ ሕንፃ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር የቦርድ ሰብሳቢው ለጉባዔው ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የባንኩ 19ኛ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔን ጨምሮ ከዚህ በፊት ይካሄድ የነበረው ለባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ የእራት ግብዣ ፕሮግራም ቀርቶ ለእራት ግብዣው ይወጣ የነበረውን ወጪ ለባንኩ የማኅበራዊ ኃላፊነት ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ እንዲውል ባለአክሲዮኖች ወስነዋል፡፡ በመሆኑም ባንኩ 2.5 ሚሊዮን ብር ለተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት በዕርዳታ መለገሱን ጠቅሷል፡፡

በዚህ መሠረትም አዋሽ ባንክ ለሙዳይ በጎ አድራት ማኅበር 350,000 ብር፣ ለክብረ አረጋውያን ምግባረ ሰናይ ድርጅት 500,000 ብር፣ ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 650,000 ብር እንዲሁም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የ1,000,000 ብር ዕርዳታ ማበርከቱን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች