ከቻድ ዋና ከተማ እንጃሚና ወደ አዲስ አበባ መንገደኞችን አሳፍሮ ይበር በነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ፣ ተጓዦችን በመደብደብ ወንጀል የተጠረጠረው የሱዳን ዜጋ ክስ ተመሠረተበት፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተበት ሱዳናዊው አህመድ አልሼክ እድሪስ የ19 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በበረራ ላይ በነበረው የበረራ ቁጥሩ ኢት-938 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ፣ ሆን ብሎ ሚስተር አርክ ምርዶቻይን የተባሉ የእስራኤል ዜጋን መደብደቡን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡
ወጣቱ ሱዳናዊ ሆን ብሎና የኃይል ድርጊት ለመፈጸም አስቦ ባደረገው የድብድብ ድርጊት፣ ተሳፋሪው ከመጐዳታቸውም በተጨማሪ ሌሎች መንገደኞችን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ከቶ እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡
በወቅቱ በበረራ ላይ የነበረው አውሮፕላን ውስጥ ችግር ይፈጠራል የሚል ሥጋት በሁሉም መንገደኞች ውስጥ የተፈጠረ ቢሆንም፣ በመንገደኞቹ ዕርዳታና በተደብዳቢው ግለሰብ ትዕግሥት አውሮፕላኑ በሰላም ማረፉ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ በፈጠረው የሚበር አውሮፕላንን ሥጋት ውስጥ የመጣል ወንጀል መከሰሱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሹ ዋስትና ተከልክሎ በማረሚያ ቤት ሆኖ ክሱን እንዲከታተል ፍርድ ቤቱ በማዘዝ፣ ለየካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡