Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበመሀላቸው በማለፉ ግለሰቡን በመደብደብ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ፖሊሶች ታሰሩ

በመሀላቸው በማለፉ ግለሰቡን በመደብደብ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ፖሊሶች ታሰሩ

ቀን:

– ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ላይ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ አንድ ግለሰብ ለምን በመሀላችን አለፈ ያሉ አራት ፖሊሶች፣ ግለሰቡን በመደብደብ የአካል ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

ግራና ቀኝ ተራርቀው በቆሙ ፖሊሶች መካከል እያለፈ የነበረው ግለሰብ ለምን በመሀላቸው እንዳለፈ ሲጠይቁት ‹‹አላየኋችሁም ይቅርታ›› ሲላቸው፣ ‹‹እንዴት አላየኋችሁም ትላለህ?›› የሚል ጥያቄ ሲያስከትሉበት፣ ‹‹ፖሊስ የሕዝብ ነው ብዬ ነው፣ ይቅርታ›› ቢላቸውም ሊተውት ባለመፈለጋቸው፣ በአካባቢው በነበረ የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ቢሮ በመውሰድ ከፍተኛ ድብደባ እንደፈጸሙበት የሚገልጽ ዝርዝር ዘገባ፣ አንድ የኪነ ጥበብ ሰው  በማኅበራዊ ድረ ገጹ አውጥቷል፡፡

- Advertisement -

ፖሊሶቹ ፈጽመውታል ስለተባለው ድርጊት ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር ልዑል ገብረ ማርያም እንደገለጹት፣ ፖሊሶቹ አራት ናቸው፡፡ ድርጊቱን መፈጸማቸው በአንድ ግለሰብ አማካይነት ለጣቢያው በመገለጹ፣ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በተደረገ ስብሰባ ፖሊሶቹ መጠየቅ እንዳለባቸው በመታመኑ፣ ከኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡

ኮማንደር ልዑል የፖሊሶቹን ስም ለጊዜው ከመግለጽ ቢቆጠቡም በድርጊታቸው በጣም ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የፖሊስ ኮሚሽን የዲሲፕሊን ዕርምጃ እንደሚወስድና በፍርድ ቤትም በሕግ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ ወንጀል በመሆኑ ክስ ስለሚመሠረትበትና ቅጣት ስለሚጣልበት አግባብ ተጠይቀው ኃላፊው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የክስና የፍርድ ሒደት የራሱ አካሄድ አለው፡፡ ፖሊሶቹ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙትም ግለሰቡ ለፀጥታ ሥራ አልተባበር ስላላቸው መሆኑን ቢገልጹም፣ ተጣርቶና ምርመራው በደንብ ተካሂዶ ለፍርድ ቤት ሲቀርብ ከዚያ በኋላ የፍርድ ቤቱ ሥራ ይሆናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ፖሊሶቹ ለፀጥታ ሥራ ያልተባበራቸውን ወይም ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽም ያገኙትን እንኳ ቢሆን የመደብደብ መብት አላቸው ወይ ተብለው የተጠየቁት ኮማንደር ልዑል፣ ‹‹ፖሊስ ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን ድብደባ ሳይሆን በካቴና ማሰርና ኃይሉን እንዲቀንስ ማድረግ፣ ሁለትና ሦስት ሆነው በመያዝ ወደ ሕግ ማቅረብ የመሳሰሉትን እንጂ ፖሊስ መደብደብ አይፈቀድለትም፤›› ብለዋል፡፡ ፖሊሶቹ የወሰዱት ዕርምጃ የተመጣጠነ ወይም ያልተመጣጠነ መሆኑን በማጣራት ላይ መሆናቸውን አስረድተው፣ ፍርድ ቤት ቀርበው የ14 ቀናት ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀባቸውም አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ የሕዝቡን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ሥራው ሁሉ የተገላቢጦሽ እየሆነ መምጣቱን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡ ዘወትር እሑድ ቀትር ላይ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሚተላለፈው ፕሮግራም፣ ፖሊስ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሕገወጦችንና በወንጀል ተግባር የተሰማሩን በማጋለጥ ጥሩ ሥራ እየተሠራ መሆኑ የሚገለጸውና በተግባር እየታየ ያለው የተገላቢጦሽ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

ሕገወጥ ድርጊት የተፈጸመበት ነዋሪ ወይም ዜጋ መጀመሪያ የሚታየው ለፖሊስ ማመልከት ቢሆንም፣ አሁን አሁን ሁሉንም ፖሊሶች ማለት ባይቻልም ተባባሪ እስከሚመስሉ ድረስ ድብደባም ይሁን ስርቆትን እንዳላዩና እንዳልሰሙ በመሆን እንደሚያልፉ ነዋሪዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በየክፍላተ ከተሞቹ ብዛት ያላቸው ማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊሶች ያሉ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ የወንጀል መከላከል ሥራን ቀለል አድርገው ከማየት ባለፈ፣ ችግር የደረሰበትን አካል ለመርዳት ፍላጐት እያጡ መምጣታቸውን ነዋሪዎች ገልጸው፣ በተለይ የጣቢያ አዛዦችና  የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ተረኞችን የሚቆጣጠሩበትን አሠራር ካላጠናከሩ ችግሩ እየባሰ እንደሚሄድ ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

በርቀት ፖሊስን የሚመለከት ዜጋ ደኅንነት ከሚሰማው ይልቅ ሥጋትና ፍርኃት እንዲፈጠርበት የሚያደርጉ አንዳንድ ፖሊሶች ስላሉ፣ በተለይ የማታ ተረኛ ፖሊሶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ሕጉንም እንዲያውቁ ቢደረግ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ብዙኃኑ ምሥጉን የፖሊስ አባላት በእንዲህ ዓይነቶቹ ምክንያት ሞራላቸው እንዳይነካ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ እነዚህ ምሥጉኖችም እንዲህ ዓይነቶቹን ማጋለጥ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ኮማንደር ልዑል እንዳስረዱት ለፖሊስ አባላት በየፈረቃውና ሁልጊዜ ትምህርታዊ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የሠሩት ሥራ ተገምግሞ የማብቃት ሥራ ይከናወናል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሥነ ምግባር የጎደለው ሊኖር ስለሚችል ከተቋሙ ዕይታ ውጪ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ቢኖርም፣ በአብዛኛው ግን ጥሩ ሥራ የሚሠሩ አባላት እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ ተቋሙ ከሌላ ጊዜ በተሻለ ብቃትና በአባላት ጥሩ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...