Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤቲኤም ማሽን ደንበኞችን ቢያስደንግጥም ንግድ ባንክ ሥጋት አይግባችሁ እያለ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች በኤቲኤም ማሽን ገንዘብ ማውጣት ባለመቻላቸው፣ በአጭር የመልዕክት ጽሑፍ ገንዘብ ማውጣታቸውን በሚገልጸው መልዕክት ከፍተኛ መደናገጥ እየተፈጠረባቸው ነው፡፡ ባንኩ በበኩሉ በጊዜያዊ ገንዘብ ዝውውር የኔትወርክ ችግር ያጋጠመ ቢሆንም፣ የገንዘብ ኪሳራ እንደማይገጥማቸው ገልጿል፡፡

በከተማዋ የተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎችና በንግድ ተቋማት አካባቢ በተተከሉ የኤቲኤም ማሽኖች ደንበኞች ገንዘብ ለማውጣት ቢሞክሩም፣ ሙከራቸው አለመሳካቱን ከማሽኑ የመረጃ ሰሌዳ እየተገለጸላቸው መሆኑንም እየገለጹ ነው፡፡ ሪፖርተርም ይኼንኑ ችግር በተለያዩ ቦታዎች ተዟዙሮ አይቷል፡፡ በተለይ ደንበኞች ሙከራው እንዳልተሳካላቸው ዓይተው ከሄዱ በኋላ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሞክረው ያልተሳካላቸውን የገንዘብ መጠን ማውጣታቸውን የሚገልጸው መልዕክት ሲደርሳቸው፣  ድንጋጤና ግራ መጋባት ተፈጥሮባቸዋል፡፡

ነገር ግን ከቆይታ በኋላ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ወደ አካውንታቸው መመለሱን የሚያሳይ መልዕክት ከባንኩ እንደሚደርሳቸውም ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይኼንን በተመለከተ መገናኛ፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስና ቦሌ አካባቢዎች የሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች ሪፖርት በሚያደርጉ ደንበኞች ተጨናንቀው መሰንበታቸውን ለማየት ተችሏል፡፡ በአንዳንዶቹ ቅርንጫፎች ደንበኞች በምሬት ከባንኩ ሠራተኞች ጋር ሲጨቃጨቁም ተስተውለዋል፡፡

የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በተወሰኑ ቅርንጫፎች አካባቢ ባሉ ማሽኖች ችግሩ መስተዋሉን አምነው ችግሩ ከኔትወርክ መቆራረጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከቴክኖሎጂው ጋር ለመራመድ በሚደረገው ጥረትም ችግሮች እንደሚከሰቱ ጠቁመዋል፡፡

ችግሩ የተከሰተው በዝውውር (Transfer)  አለመሟላት ምክንያት ቢሆንም፣ በማዕከል ቋት አማካይነት የሚተላለፍ በመሆኑና ጥብቅ ክትትል ስለሚደረግበት፣ ደንበኞች ሥጋት ላይ ሊወድቁ እንደማይገባና በፍጥነት ሊስተካከል እንደሚችል አቶ ኤፍሬም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ደንበኞች እንዲህ ዓይነት ችግር በሚገጥማቸው ወቅት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ቅርንጫፎች ወይም ኤቲኤም ካርዱን ያወጡበት ቅርንጫፍ በመሄድ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባንኩን ነፃ የስልክ መስመር በሆነው በ950 በመደወል ጥያቄ ሊያቀርቡ ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላው አገሪቱ ከ650 በላይ የኤቲኤም ማሽኖች  አሉት፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ከ250 በላይ መትከሉን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች