Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሙስና የተጠረጠሩት የኦሮሚያ ባለሥልጣን የተመሠረቱባቸው ክሶች ውድቅ ተደርገው እንዲፈቱ ጠየቁ

በሙስና የተጠረጠሩት የኦሮሚያ ባለሥልጣን የተመሠረቱባቸው ክሶች ውድቅ ተደርገው እንዲፈቱ ጠየቁ

ቀን:

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባልና የክልሉ ገቢዎችና ጉምሩክ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን የማየት ሥልጣን ስለሌለው የተመሠረቱባቸው ክሶችን ውድቅ በማድረግ ከእስር እንዲፈታቸው ጠየቁ፡፡

ተጠርጣሪው ጥያቄውን ያቀረቡት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የመሠረተባቸውን የሙስና ወንጀል ክስ በመቃወም፣ በጠበቃቸው በአቶ መሐመድኑር አብዱልከሪም አማካይነት ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረቡት የመጀመርያ ደረጃ የመቃወሚያ ማመልከቻ ነው፡፡

አቶ ወንድሙ በኦሮሚያ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኛ ሆነው ሲሠሩ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስ በሚመለከት እንደገለጹት፣ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ባለሥልጣን የሙስና ወንጀል በመፈጸም ከተጠረጠረ ወንጀሉ በክልሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር የሚወድቅ ነው፡፡ ይኸም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ በኦሮሚያ መንግሥት ሕገ መንግሥት፣ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅና በሥነ ሥርዓት አዋጁ፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና ማሻሻያዎቹ፣ በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የተገለጸና የተረጋገጠ መሆኑን አንቀጾቹን ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ክስ ሊያቀርብባቸው የሚችለውና ሥልጣን ያለው የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሆኑን ጠቁመው፣ ለፌዴራሉ የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች እንዲሁም ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መከበር እንዳለበት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለተደነገገና የአገሪቱም የበላይ ሕግ ስለሆነ፣ በክልሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር ሊወድቅ በሚችል የሙስና ወንጀል ሥልጣን በሌለው በፌዴራል መቅረቡ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) እና በወ/መ/ሥ//ሥ/ሕ/ቁ 130(2ሠ) መሠረት እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሚፈጸም የሙስና ወንጀል ጉዳይ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን ያለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወይም የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑን የጠቆሙት ተጠርጣሪው፣ ፍርድ ቤቱ ክሶቹን “አልቀበልም” ብሎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) እና በወ/መ/ሥ/ሥ/አ/ቁ 110 መሠረት መመለስ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

አቶ ወንድሙ ጉቦ መስጠትና በሥልጣን መነገድ የቀረበባቸውን ክስ በሚመለከት ባቀረቡት ተቃውሞ እንዳስረዱት፣ የተጠቀሱባቸው ወንጀሎች ተደራራቢ ወንጀሎች ሳይሆኑ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 431 መሠረት አንድ ክስ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ጉቦ በመስጠት ወንጀል መከሰስ ያለበት ውሳኔ ፈላጊ ባለ ጉዳይ ወይም ባለ ገንዘብ ብቻ መሆኑን ያስረዱት ተጠርጣሪው፣ ጉቦ በመቀበል ወንጀል የሚከሰሰው ውሳኔ ሰጪ ወይም ጉዳይ ፈጻሚ የመንግሥት ሠራተኛ መሆኑን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 427 እና 408 በግልጽ የሚያሳዩ ሆኖ ሳለ፣ እሳቸው ውሳኔ ፈላጊ ባለጉዳይ ወይም ውሳኔ ሰጪ የጉምሩክ ሠራተኛ አለመሆናቸውንና የወንጀል ሕግ ቁጥር 427 መሥፈርትን የማያሟሉ መሆናቸውን በመግለጽ መከሰስ እንደሌለባቸው አስረድተዋል፡፡

በሥልጣን መነገድ ወንጀል የሚከሰስ ተጠርጣሪ የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ባለው ሥልጣን ወይም አስመስሎ ባቀረበው ተሰሚነት ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ ስጦታ ወይም ጥቅም የጠየቀ ወይም የተቀበለ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድሙ፣ እሳቸው የቀረበባቸው ክስ “የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኛ ሆኖ ባለው ወይም አስመስሎ ባቀረበው ተሰሚነት ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ ገንዘብ ተቀበለ” ስለማይል፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 414ን እንደማያሟላ አስረድተዋል፡፡

አንድ ድርጊት የሚፈጸመው በጊዜና በቦታ ቢሆንም፣ ግን መቼና በየት ቦታ ድርጊቱ እንደተፈጸመ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ አለማቅረቡን በመግለጽ፣ “ባሕሩ ቢረዳ የጠጠር ማምረቻ ድርጅት”ን ወደ ግል ለማዞር፣ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኛ ለነበሩት አቶ መርክነህ ዓለማየሁ ጉቦ እንደተሰጠና እንደተመሳጠሩ እንደማያሳይ፣ ድርጅቱ የግል ይሁን የማኅበር እንደማያስረዳ፣ ስታር አፍሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከጠጠር ማምረቻው ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው እንደማያስረዳ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በወንጀል ሕጉ 431 መሠረት በግል ተሰሚነት የመነገድ ወንጀል እንጂ፣ በወንጀል ሕግ 427 እና 414 ሥር የተመለከተውን ወንጀል ስለማያቋቁም በወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ 130 (1) መሠረት እንደሚቃወሙ አስረድተዋል፡፡ ክሱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(2) እና በወ/መ/ሥ/ሥ/አ ቁጥር 111 እና 112 መሠረት ግልጽ ሆኖ መቅረብ ሲገባው፣ በመንዛዛቱ የመከላከል መብታቸው እንደሚያጣብብ በመጠቆም ተቃውመዋል፡፡

አቶ ወንድሙ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት መሰብሰባቸውን በሚመለከት የተመሠረተባቸው ክስ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 40 እንደሚቃረን ጠቁመው፣ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ባለሥልጣን ሀብቱ ስለጨመረ ብቻ እንደ ሌባ (ሙሰኛ) መቆጠሩ አግባብ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡፣ ክሳሽ ዓቃቤ ሕግ ከጥርጣሬ በላይ የማስረዳት ግዴታውን አለመወጣቱን ገልጸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ራሱ የማስረዳት ሸክሙን ወደ እሳቸው በማዞር የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ሕግና ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ መርህን የሚቃረንና የሕገ መንግሥቱን የበላይነት የሚሸረሽር መሆኑን በመግለጽ፣ ክሱ ተፈጻሚነት እንደሌለው አብራርተው ተቃውመዋል፡፡

አቶ ወንድሙ ሰፋ ያለና ዝርዝር የክስ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን በሚመለከት ስለቀረበባቸው ክስ ባቀረቡት መቃወሚያ እንዳስረዱት፣ ከሳሽ ገቢያቸውንና አሁን ያላቸውን ሀብት ለየብቻው ደምሮና አቀናንሶ ማወቅ ሲገባው፣ መጀመሪያ ጊዜ ይከፈላቸው የነበረን 889,976 ብር በ19 ዓመታት አባዝቶ ብቻ ማቅረቡን፣ ነገር ግን በሹመትና ዕድገት ያገኙት የነበረውን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አለመጨመሩን፣ የባንክ ወለድንም አለመደመሩንና ሕጋዊ ሀብታቸው መሆኑን አለመግለጹን ጠቁመው፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 419(1)ን ስለሚቃረን ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ በእናታቸው፣ በእህታቸውና በባለቤታቸው ስም ያሉ ንብረቶችን አሥልቶ መክሰስና መቅጣት ስለማይቻል ክሱ የሕጉን ሥርዓትና ፎርም ያልተከተለ መሆኑን አብራርተው እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሀብታቸውን ሕጋዊ አስመስለው ባለማቅረባቸው ክስ የመሠረተባቸው ቢሆንም፣ አቶ ወንድሙ በሙስና የተገኘ ሀብት አለመኖሩን ገልጸው ተቃውመዋል፡፡ ተነጣጥለው የቀረቡባቸው ክሶች በወንጀል ሕግ ቁጥር 419 ሥር አንድ ክስ ሆነው መቅረብ እንደነበረባቸው ጠቁመው፣ ክሶቹን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 130 መሠረት እንደሚቃወሙ በጠበቃቸው አቶ መሐመድኑር አብዱልከሪም አማካይነት ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ያብራራል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...