የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ኩባንያ ሳዑዲ ስታር የግብርና ልማት ድርጅት በደርግ መንግሥት ዘመን የተገነባውን አልዌሮ ግድብ ከመንግሥት ቢረከብም፣ በመስኖ ማልማት የቻለው 350 ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ የተቀረውን ስድስት ሺሕ ሔክታር መሬት በዝናብ ለማልማት የተሞከረ መሆኑ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ ግን ከመንግሥት የተረከበው አሥር ሺሕ ሔክታር ሲሆን፣ 3,650 ሔክታር ለእርሻ ዝግጁ አልተደረገም፡፡
ሳዑዲ ስታር የግብርና ልማት ድርጅት በጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት አኙዋ ዞን አቦቦ ወረዳ አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ሩዝ ለማልማት መሬት ተረክቧል፡፡ ሳዑዲ ስታር ይህንን መሬት በ2001 ዓ.ም. ሲወስድ ከመሬቱ ጋር አልዌሮ ግድብን ጨምሮ ተረክቧል፡፡
ነገር ግን ወደ እርሻ የሚወስዱት ካናሎች ጂአርሲ በተባለ ኩባንያ ተጀምረው ሳይጠናቀቁ በመቅረታቸው ልማቱ በዕቅዱ መሠረት ሊካሄድ አልቻለም፡፡ ሳዑዲ ስታር ከደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ወጥቶ በሆራይዘን ፕላንቴሽን ሥር እንዲደራጅ ከተደረገ በኋላ በጅምር የቀረው የካናል ቀደዳ በድጋሚ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ጅምሩ ገና በሒደት ላይ በመሆኑ እስካሁን በሌላ አቅጣጫ በተዘረጋ ካናል መልማት የቻለው 350 ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡
የሆራይዘን ፕላንቴሽን ኮሙዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ከማል መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተጀመረውን 21 ኪሎ ሜትር የካናል ቀደዳ በማጠናቀቅ 1,400 ሔክታር መሬት በዚህ ዓመት በመስኖ ለማልማት ታቅዷል፡፡
‹‹ወደ ልማት የገባነው በመስኖ የተደገፈ ምርት ለማምረት ነው፡፡ ጋምቤላ ክልል ዝናብ የሚጥል በመሆኑ መሬቱ ፆሙን ከሚያድር የቀረውን መሬት በዝናብ ለማልማት እየሠራን ነው፤›› በማለት አቶ ከማል ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ሼክ አል አሙዲ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በመነጋገር፣ ወደ ሩዝ ምርት ሲገቡ በጋምቤላ ክልል ብቻ በአጠቃላይ 300 ሺሕ ሔክታር መሬት የማልማት ዕቅድ ነበራቸው፡፡ በደርግ ጊዜ ለጥጥ ልማት እንዲሆን የተገነባው አልዌሮ ግድብም ለዚህ ልማት እንዲውል መንግሥት ወስኗል፡፡
በዚህ መሠረት መጀመርያ አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ተሰጥቷቸው በሒደት የሥራ አፈጻጸሙ እየታየ ቃል የተገባው 290 ሺሕ ሔክታር መሬት ይፈቀዳል የሚል ሐሳብ በመንግሥት በኩል ቢኖርም፣ የኩባንያው የሥራ አፈጻጸም አነስተኛ በመሆኑ ቃል የተገባው መሬት እስካሁን አልተፈቀደም፡፡
ሳዑዲ ስታር በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልል ለማካሄድ ላቀደው የግብርና ልማት እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት የማድረግ ዕቅድ ነበረው፡፡
ሼክ አል አሙዲ ጋምቤላ ላይ ለጀመሩት ለዚህ እርሻ ልማት 80 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የካተርፒለር ብራንድ የሆኑ የተለያዩ ግብርና ማሽኖች ግዥ ፈጽመዋል፡፡ ነገር ግን ለኩባንያው የወጣው ወጪና ኩባንያው እያካሄዳቸው ያሉ ሥራዎች እንደማይጣጣሙ ይነገራል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢወጣም፣ እየካሄደ ያለው ሥራ ማንኛውም ገበሬ ሊሠራ በሚችለው ደረጃ ነው በማለት አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡
ሳዑዲ ስታር ሩዝ አልምቶ በአብዛኛው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የመላክ ዕቅድ ያለው በመሆኑ፣ ሩዝ ለማቀነባበር ሁለት ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ፋብሪካዎቹ በጋምቤላና በቢሾፍቱ ከተሞች እንደሚገኙ አቶ ከማል ገልጸዋል፡፡ ሳዑዲ ስታር ከተመሠረተ ሰባት ዓመታት ቢሞሉትም፣ እስካሁን ከሙከራ የዘለለ ምርት እንዳላመረተ ታውቋል፡፡
የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ከዓመት በፊት ለቀድሞው የግብርና ለአሁኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ፣ የኩባንያው የሥራ አፈጻጸም ደካማ መሆኑንና ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ጠይቀው ነበር፡፡
አቶ ጋትሉዋክ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው በዚህ ዓመት ያሳየው የሥራ አፈጻጸም የተሻለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ተጀምረው የቀሩ ካናሎች በድጋሚ እየተገነቡ መሆኑንም አቶ ጋትሉዋክ ጠቁመዋል፡፡
ኅዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓልን የሚያስተናግደው የጋምቤላ ክልል፣ የሳዑዲ ስታር ፕሮጀክትን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያስጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡