የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የግዢና ንብረት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር በአሥር ሚሊዮን ብር ሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ኤፍሬም ደሳለኝና የግዥና ንብረት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ንጉሤ ታደሰ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ሲሆን፣ ኅዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በድርጅቱ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሲሠሩ የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ሲገባቸው፣ አቶ ገብረ አምላክ በርሄ ከሚባሉ ግለሰብ ጋር በመመሳጠር ግምቱ 8,974,000 ብር የሆነ የመንግሥት ንብረት (ምንነቱ አልተገለጸም) አውጥተው በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ መርማሪ ፖሊስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ ያለምንም ስምምነትና ውል ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ከድርጅቱ ካዝና በማውጣት ለልኳንዳ ነጋዴዎች እንዲከፈል በማድረጋቸው፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄም ታልፏል፡፡