የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይና የውኃ ሀብት ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድቡ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ እንዲሁም የግድቡን አካባቢያዊ ተፅዕኖን በተመለከተ በሱዳን ካርቱም ከመጋቢት 26 እስከ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲካሄድ የነበረው ስብሰባ ያለውጤት ተጠናቀቀ፡፡
ሪፖርተር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ማረጋገጥ እንደቻለው፣ ስብሰባው ሊቋረጥ የቻለው በዓባይ ውኃ ክፍፍል ላይ ከግብፅ በተነሳ ጥያቄ ምክንያት ነው፡፡
በጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በመሪዎች ደረጃ የተሰጠውን መመርያ ለመተግበር የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ኢትዮጵያ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ግብፅ አሁንም እ.ኤ.አ. የ1959 የውኃ አጠቃቀም ስምምነት የውይይቱ አካል እንዲሆን ጽኑ አቋም በመያዟ መሰናክል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ስብሰባውን በቀጣይ ለማካሄድ ስምምነት ቢኖርም፣ መቼ እንደሚካሄድ ግን እርግጠኛ የሆነ የጊዜ ቀጠሮ አልተያዘለትም፡፡