Monday, March 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መርማሪ ኮሚስዮን

(ክፍል ሁለት)

በውብሸት አየለ ጌጤ

4. ኮሚሽኑና ደርግ

የመርማሪ ኮሚሽን አዋጅ እንዲረቀቅ ንጉሣዊ ትዕዛዝ ከተሰጠበት ከመጋቢት 16 ቀን 1966 ዓ.ም. አዋጁ እስከደቀበት ሰኔ 8 ቀን 1966 ዓ.ም. ድረስ መለዮ ለባሹን ወክሎ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ የነበረው በኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ ሊቀመንበርነት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ይመራ የነበረው የጦር ኃይሎች ኮሚቴ በመባል የሚታወቀው ነበር። ኮሚቴው የተቋቋመውም መጋቢት 1966 ዓ.ም. ነው።

ኮሚቴው በአዲስ አበባ የሚገኙትን የጦር ክፍሎች እንወክላለን የሚሉ መስመራዊ መኮንኖችንና የበታች ሹማምንትን የያዘ ነበር። ዋናው የዚህ ኮሚቴ ባለቤቶችና ፈጣሪዎች የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንንና የኮሚቴው ሊቀመንበር ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ የአየር ወለድ አዛዡ ነበሩ። ዓላማውም የሕዝቡን ጥያቄዎች መልስ ለማስጠት የሚንቀሳቀስ በማስመሰል ተቀናቃኝ የመሆን አቅም ያላቸውና የመሰላቸውንም በኃይል በቁጥጥር ማድረግ ነው።

የሲቪል ባለሥልጣኖችና የጦር መኮንኖች፣ የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ካቢኔ አባላትን ጨምሮ 24 የቀድሞ ባለስልጣኖች ሚያዝያ 18፣ 192223 እና ግንቦት 23 ቀን 1966 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የመታሰሩ ፈንታቸው የተጀመረው ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን በያዙ በሁለተኛ ወር የመርማሪ ኮሚስዮኑን የሚያቋቁመው ረቂቅ ሕግ ለፓርላማው በቀረበ በወሩ ነው።

የዕርምጃውም ዓላማ በቁጥጥር ሥር የሚውሉትን እስረኞች በመርማሪ ኮሚስዮን እያስመረመሩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴውን ለማቀዝቀዝ፣ ለወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ፋታ በመስጠት ሥልጣኑን በቅጡ ለመቆጣጠር ነበር።

ይሁንና የሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል የኮሚሽን አባላትን መምረጥ አይገባውም ሲል አስቀድሞ በልጅ እንዳልካቸው መንግሥት የተመረጡትን ሰባት የመርማሪ ኮሚሽን አባላት ፓርላማው ባለመቀበሉና የኮሚስዮኑንም ሕጋዊ አቋም የሚሰጠው የድንጋጌው ረቂቅ ለፓርላማው ከቀረበበት ከመጋቢት 27 ቀን 1966 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 8 ቀን 1966 ዓ.ም. ድረስ ሳይታወጅ በመቆየቱ ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለልጅ እንዳልካቸው እንደታሰበው ኮሚስዮኑ ፋይዳ ያለው ጥቅም ሳይሰጥ ቀረ።

ደርግ የሚባለውና አገሪቱን ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ጀምሮ 17 ዓመት የገዛው ወታደራዊ ተቋም በይፋ ራሱን ያስተዋወቀው ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም. ነው። ይኸውም እነ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከታሰሩ ከሁለት ወር በኋላ የመርማሪ ኮሚስዮን በአዋጅ ከተቋቋመ ከሁለት ሳምንት በኋላ መሆኑ ነበር።

ደርግ ከተቋቋመበት ማግሥት ጀምሮ የኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ የጦር ኃይሎች ኮሚቴ ተበተነ። እሳቸውም ተሰወሩ። ደርግም የኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ የጦር ኃይሎች ኮሚቴን ሙሉ ለሙሉ ተክቶ ዕርምጃውንም በዚያው በተከፈተው መንገድ በሦስት ቀን ውስጥ አሥር ከፍተኛ የንጉሠ ነገሥቱ ሹማምንት አሰረ። በዚህም ምክንያት ሐምሌ 15 ቀን 1966 ዓ.ም. ልጅ እንዳልካቸው መኮንንም ከሥልጣን ወርደው በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የመስዋዕት በግ አድርገው አቅርበዋቸው ከነበሩት የቀድሞ ባልደረቦቻቸው ጋር በሦስት ወራት ውስጥ ተቀላቅለው የአስተባባሪው ደርግ እስረኛ ሆኑ። ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማም ተሰውረው ከነበሩበት የንጉሡን መውረድ ምክንያት አድርገው የደስታ መግለጫ ከላኩ በኋላ መስከረም 26 1967 ዓ.ም. እጃቸውን ለደርግ ሰጡ። ዕጣ ፈንታቸውም በእሳቸው በሚመራው የጦር ኃይሎች ኮሚቴ ከአሠራቸው ባለሥልጣኖች ጋር ተቆራኝቶ አረፈው። መርማሪ ኮሚስዮኑ በይፋ ሥራውን የጀመረው ሐምሌ 12 ቀን 1966 ዓ.ም. ደርግ አቅሙን አፈርጥሞ፣ በኅብረተሰብ ውስጥ ጎልቶ ወጥቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ማውረድና በምትኩም ሌላ መሾም በሚችልበት ወቅት ነው።

ይህንኑ አቅሙን መሠረት አድርጎ የኮሚስዮኑን ቢሮ ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር አዙሮ በቅርበት ለመሥራት ጥያቄ አቅርቧል። ለዚህ በኮሎኔል መንግሥቱ በተደጋጋሚ ይቀርብ ለነበረው ጥያቄ ኮሚሽኑ በአጀንዳነት ተወያይቶበት በአብዛኛው አባላት ውሳኔ ጥያቄው ውድቅ መደረጉን በፕሮፌሰር መስፍን ተገልጿል። ደርግ የኮሚስዮኑን ሥራ ለመቆጣጠር ይቻለውም ዘንድ ሻለቃ መርሻ አድማሱን ከምድር ጦር፣ ኮማንደር ለማ ጉተማን ከባህር ኃይል መድቦ ነበር። እንዲያውም ደርግ ሻለቃ መርሻ አድማሱን የኮሚስዮኑ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎም ነበር የሾማቸው። ይሁንና የአየር ወለድ ጦር ክፍል እኒህን ሰው ሙሰኛ፣ ስስታምና ጨቃኝ ናቸው በሚል ሹመቱንም ሆነ ምደባውን አምርሮ ስለተቃወመ የኮሚስዮኑ አባል ሳይሆኑ ቀረ።

የኮማንደር ለማ ጉተማ የኮሚስዮኑ አባል እንዲሆኑ በደርግ የተደረገው ምደባ ተፈጻሚ ሆነ። ከላይ እንደተገለጸው የሥራ አስፈጻሚው የኮሚስዮኑን አባላት እንዳይመርጥ ፓርላማው ያደረገው ክልከላ ዋጋ አጥቶ፣ የጦር ኃይሉ አባላት በአዋጁ በተቀመጠላቸው ኮታ መሠረት ከየክፍላቸው እንዲመርጡ የተሰጣቸው መብት ተጥሶ፣ ደርግ የተባለው በወቅቱ ራሱን ለሥራ አስፈጻሚነት አደራጅቶ የሚንቀሳቀስ አካል ኮማንደሩን መደበ። ኮሚስዮኑ በወሎ ረሃብ ምክንያት ለደረሰው ዕልቂት በኃላፊነት ሊጠየቁ ይገባል ባላቸው 35 የቀድሞ ባለሥልጣኖች ላይ የደረሰበትን ውሳኔ እና የተከሳሾችን ስም ዝርዝር ኅዳር 4 ቀን 1967 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ

መግለጫ አስታወቀ።

     ይህም የኮምስዮኑ መግለጫ በማግስቱ ኅዳር 5 ቀን 1967 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ታትሞ በዝርዝር ወጣ። ከላይ የተገለጸው ጋዜጣዊ መግለጫ ከተሰጠ ከአምስት ቀናት በኋላ ኮሚሽኑ ኅዳር 11 ቀን 1967 ዓ.ም. ለልዩ ጦር ፍርድ ቤት የዐቃቢ ሕግ ጽህፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ኅዳር 6 ቀን 1967 ዓ.ም. በቁጥር ///6/2325 የተጻፈለትን አስታውሶ መልስ ሰጥቷል። በመልሱም በወሎ የደረሰውን ድርቅ እና ረሃብ እንዲሁም እልቂት በተመለከተ ባደረገው ምርመራ መሠረት፤ ከደብዳቤው አባሪ ጋር በተዘረዘሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ተለይቶ የተመለከተው የወንጀል ክስ እንዲቀርብባቸው አስታወቀ። እንደገና ከሁለት ቀን በኋላ ኅዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም. እነዚህኑ ምርመራቸው ተጠናቅቋል የተባሉትን 35 ባለሥልጣኖች በተመለከተ የወንጀል ክስ እንዲቀርብባቸው ኮሚስዮኑ ሌላ ደብዳቤ ለልዩ ጦር ፍርድ ቤቶች ጽሕፈት ቤት በመጻፍ የተከሳሾቹን ስም ዝርዝር አስተላለፈ። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በዚሁ ኅዳር 13 1967 ዓ.ም. ለደርጉ ዘመቻና ጥበቃ መምርያ መኮንንበጣም የሚያስቸኩልየሚል ማሳሰብያ በላዩ ላይ በማስፈር ደብዳቤ ጽፈዋል። ይህ ደብዳቤሰሞኑን የደርግ አባላት ባደረጉት ከፍተኛ ስብሰባበአንደኛ ዙር የስም ዝርዝራቸው ከዚህ ጋር በተያያዘው የቀድሞ ባለስልጣናት ላይ አብዮታዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በአንድ ድምፅ ወስነዋልይላል።

ይህ ለደርጉ ዘመቻና ጥበቃ መምርያ የተጻፈው የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ደብዳቤ ሌተና ጄነራል አማን ሚካኤል አንዶም በዚሁ ቀን እንዲያዙ፣ እንዲሁም በከርቸሌ ግቢ ውስጥ 54 ሰው መቀበርያ የሚሆን ጉድጓድ በዶዘር እንዲቆፈር፣ በመጨረሻም ስማቸው ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ ሆኖበተያያዘው ሰነድ ላይ የተገለጹት 54 የሲቪልና የጦር ባለሥልጣናት ከምሽቱ ሁለት ሰአት ከእስረኞቹ ተለይተው ለብቻ እንዲቆዩና ከሌሊቱ 8 ሰአት ወደ ዋናው ከርቸሌ ተወስደው በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ የሚል ትእዛዝ የያዘ ነው።

በዚህ ትዕዛዝ መሠረትም ኅዳር 14 1967 ዓ.ም. ሌሊት ከኮሚስዮኑ ተመርማሪዎች መሃል በአሥራ አንዱ ላይ እንዲሁም ወደፊት በሌላ ጭብጥ የኮሚስዮኑ ተመርማሪ ሊሆኑ በሚችሉ ሌሎች የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ባለሥልጣኖች ላይ የግፍ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

ከዚህ በላይ በተገለጸው ቀን በደርግ በግፍ የተገደሉት፣ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ሌተና ጀነራል ከበደ ገብሬ፣ ክቡር / ተስፋዬ ገብረእግዚእ፣ ክቡር ደጃዝማች ሰለሞን አብርሃ፣ክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ፣ ክቡር አቶ ሙላቱ ደበበ ፣ክቡር ደጃዝማች ለገሰ በዙ ፣ክቡር ደጃዝማች ክፍሌ እርገቱ፣ ክቡር አቶ ተገኝ የተሻወርቅ እና ክቡር አቶ አበበ ረታ ናቸው።

የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ትእዛዝና የኮሚሽኑን ውሳኔ የያዙት የኅዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም.እነዚህ ሁለት ደብዳቤዎች መገጣጠም አጋጣሚ ይሁን ወይም ሆን ተብሎ የተደረገ ስለመሆኑ ጥናት ሊደረግበት የሚገባ እንጅ በዝምታ ሊታለፍ ሕሊና የሚፈቅድ አይመስለኝም።

5.  የኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸም ከአዋጁ አንጻር

      የአዋጁ ዓላማዎች

የመርማሪ ኮሚስዮንን የአቋቋመው አዋጅ ቁጥር 326/66 በመግቢያው ላይ እንደአሰፈረው ዓላማው በንጉሠ ነገሥቱ የተሾሙ ባለስልጣናት ሥራቸውን እና አገራቸውን በቅን ልቦና እና በትክክል የማከናወን ግዴታቸውን መፈጸም ወይም አለመፈጸማቸውን መመርመር ነበር።

ኮሚስዮኑ፣ አንድ ባለስልጣን ሕገወጥ በሆነ መንገድ ያፈራው ሀብት፣ ያባከነውም የመንግሥት ገንዘብና ንብረት ካለ እንዲሁም በዳኝነትና በአስተዳደር ያደረሰው በደል ቢኖር የመመርመር ኃላፊነት አለበት። እንዲሁም አዋጁ አጥፊ የሆኑት ተለይተው እንዲታወቁና ጥፋተኝነታቸው ሲረጋገጥ በሕግ እንዲቀጡ የማድረግም ዓላማ አለው።

በመጨረሻም አዋጁ ሌላው በመግብያው የገለጻቸው ሊያስፈጽመው የሚገባቸው ሁለት አቢይ ጉዳዮች አሉ። እነሱም በመንግሥት ላይ የሕዝብ እምነት እንዲሰፋ ማድረግና የመንግሥት ባለሥልጣኖችም ሊኖራቸው የሚገባው ከፍተኛ ታማኝነት መኖር አስፈላጊ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።

ጠበቃ የመያዝ መብት

ምርመራውንም የሚያከናውነው በምስጢር፣ አስፈላጊም ሲሆን በግልጽ ነው። የመጀመርያ ደረጃ ምርመራ ሲካሄድ ወይም የአገር ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ይጠበቃል በሚል አባላቱ ሲወስኑ፣ በምስጢር ምርመራ ወይም በዝግ ምርመራውን ያከናውናሉ። የተጨበጠ ማስረጃ ሲገኝ ምርመራውን በግልጽ ወይም በክፍት ያደርጋል። ተመርማሪውም ጠበቃ ሊይዝ እንደሚችል ኮሚስዮኑ መፍቀድ እንዳለበት አዋጁ ይደነግጋል። 1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 52 ይህንኑ ጠበቃ የመያዝ መብትን ደንግጓል።

የመርማሪ ኮሚስዮንን የምርመራ ሒደት የያዙትን መዛግብት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተመጻሕፍት ውስጥ አግኝቼ መርምሬአለሁ። ከእነዚህ የምርመራ ሒደቱን ከያዙት መዛግብት የተረዳሁት፣ ተመርማሪዎቹ ሕገ መንግሥቱና የአዋጁ ድንጋጌ በሚፈቅደው መሠረት ጠበቃ ሳይዙ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡ መሆኑን ነው።

ኮሚስዮኑ በእነዚህ የምርመራ መዝገቦች ላይ ይህን መብት ለተመርማሪዎቹ ማስገንዘቡን የሚያመለክት ምንም የተመዘገበ ነገር አይታይም። ምርመራው በሬድዮ ሲተላለፍም ምንም የጠበቃ ሚና አልተደመጠም። ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ተመርማሪው ጠበቃ ሊይዝ እንደሚችል የተደረገለትን የሕግ ጥበቃና የከለላ መብት በኮምስዮኑ መነፈጉን ነው። ይህም ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመርማሪዎቹ ላይ ኮሚስዮኑ መፈጸሙን ያስረዳል።

መገናኛ ብዙኃንን ስለመጠቀም

ኮምስዮኑ፣ ማንኛውንም ባለሥልጣን ወይም ሰው፣ በመሃላ በተደገፈ ጽሑፍ የራሱን እና የባለቤቱን እንዲሁም ከሌላ ሰው ጋር ያለውን የንብረት ግንኙነት፣ የነበረውን ዋጋና ንብረቱ የሚገኝበትን ስፍራ፣ በዝርዝር እንዲገልጽ የመጠየቅ ሥልጣን አለው። በተጨማሪም ኮምሲዮኑ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1933ዓም ወዲህ ከሚወስነው ጊዜ ጀምሮ ከማናቸውም ምንጭ የነበረውን ገቢና ገቢውን አስመልክቶ የተከፈለውን ማንኛውንም ግብር በዝርዝር እንዲገልጽ መጠየቅም ይችላል።

አንድ ባለሥልጣን የንብረቱን ዋጋና ንብረቱ የሚገኝበትን ስፍራ፣ ገቢና የገቢውን ልክና ገቢውን መሠረት አድርጎ የከፈለውን ማንኛውንም ግብር በዝርዝር እንዲገልጽ ተጠይቆ እምቢተኛ ከሆነ፣ ኮምሲዮኑ ይህንኑ እምቢተኛነት በአዋጁ አንቀጽ 8(5) መሠረት ለሕዝብ የማስታወቅ ሥልጣን አለው።

የኮምሲዮኑ አባላት ለሕዝብ ጥቅም ነው ብለው ሲያምኑም፣ ተመርማሪው ከማናቸውም ምንጭ የነበረውን ገቢና በገቢው መሠረት የተከፈለውን ማንኛውንም ግብር በተመለከተ የተሰጠን መግለጫ አስመልክቶ ለሕዝብ የማስታወቅ ሥልጣን አለው።

እንደሚታወቀው ኮምሲዮኑ ከተመርማሪዎቹ ጋር ያደርግ የነበረውን የምርመራ ሒደት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ትብብር፣ በቴፕ እየተቀረጸ ለሕዝቡ በሬድዮ እንዲሰማ አድርጓል። ይህንንም በማድረግ ዘላቂና ጠቃሚ ትምህርት ለሕዝብ ያተረፈ መሆኑንም ኮሚሽኑ ያምንበታአል። በተጨማሪም ኮምስዮኑ፣ ምርመራውን በሬዲዮ ያስተላልፍ የነበረው፣ ምርመራው የሚያዳምጠው ሕዝብ ለምርመራው የሚረዳ ጥቆማ እንዲሰጥ ለማበረታትና ለወደፊት የመንግሥት ሠራተኞች ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዳለባቸው ለማስገንዘብና ለማስጠንቀቅ ስለመሆኑም ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።

ከሕዝብ ለምርመራው የሚረዳ ጥቆማ ለማግኘትም ሆነ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠያቂነትና ኃላፊነት ለወደፊት ለማስገንዘብና ለማስጠንቀቅ የኮምሲዮኑን ጥያቄና የተመርማሪዎቹን መልስ በሬድዮ እንዲተላለፍ የሚፈቅድ አንቀጽ ኮምስዮኑ ሥራውን በሚያካሂድበት አዋጅ ቁጥር 326/66 አልተካተተም።

ከላይ በአዋጅ ቁጥር 326/66 አንቀጽ 8(5) ከተገለጸው የንብረት ጉዳይ ውጭ የምርመራውን ሒደትም በተለይ የኮሚስዮኑ ጥያቄ የተመርማሪዎቹንም ሆነ የአስረጅዎችን መልስ በሙሉም ይሁን ወይም በከፊል ለሕዝብ የማስታወቅ ሥልጣን ወይም በማናቸውም የመገናኛ ብዙኃን እንዲያስተላልፍ በአዋጁ ሥልጣኑ አልተሰጠውም።

ኮሚስዮኑን ያቋቋመው አዋጅ ቁጥር 326/66 መሠረቱ በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረው 1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ነው። የዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 53 ባለሥልጣኖቹ የኮሚስዮኑ ተመርማሪዎች መሆናቸው ወይም በቁጥጥር ስር መገኘታቸው ይከሰሱ በተባለበት ወንጀል ሥልጣኑ የሆነ ፍርድ ቤት እስከሚያረጋግጥባቸው ድረስ ወንጀለኛ ተደርገው እንዳይታዩ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። የኮምሲዮኑ ጥያቄና የተመርማሪዎቹ መልስ በሬድዮ መተላለፉ የተመርማሪዎቹንም ከፍርድ በፊት ንጹህ ሆኖ በሕግ ፊት የመታየት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ኮሚስዮኑ የምርመራውን ሥራ እንደጀመረ ገና በጥዋቱ የጣሰው ዐቢይ ሕገወጥ ድርጊት ነበር። የዚህ ሕገወጥ ተግባር ያስከተለው ውጤትም ሕዝቡ ተመርማሪዎቹን ከፍርድ ሂደት ውጭም ወንጀለኛ አድርጎ እንዲያያቸው ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።

ይህም የሚያስገነዝበን በመገናኛ ብዙኃን በተለይ በሬድዮ ከፍተኛ አጽንኦት ሰጥቶ የኮምሲዮኑ የማዋከብ ጥያቄና የተመርማሪዎቹ የተሸማቀቀ፣ አንዳንዴም በእንባ በመታናቅ ይሰጡ የነበረው መልስ ይተላለፍ የነበረው ከሕግ ውጭ መሆኑን ነው።

ኮሚስዮኑ የተቋቋመበትን ሕግ ሳይጥስ፣ የመርማሪዎቹን ጥያቄና የተመርማሪዎቹን መልስ በሬድዮ ሳያስተላልፍ፤ ኮሚስዮኑ ግልጽ የሆነ መግለጫ በወቅቱ በነበሩት ጋዜጦች፣ ራድዮና ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ጥቆማ እንዲቀርብለት ኅብረተሰቡን ማበረታት ይችል ነበር።

አዋጁ በደነገገው መሠረት ምርመራው ተካሂዶ፣ በምርመራው መሠረት ሊከሰሱ የሚገባቸው አዋጁ ሥልጣን በሰጣቸው ፍርድ ቤቶች ክስ ተመስርቶባቸው፣ እነሱም የመሰማት መብታቸው ተጠብቆተከራክረው ጥፋታቸው በመጨረሻው ፍርድ ቤት ሲወሰን፣ ያኔ የምርመራውንም አካሄድ ሆነ ፍርዱን በአደባባይ በማውጣት፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠያቂነትንም ሆነ ኃላፊነትን ለወደፊት ለማስገንዘብ ይቻል ነበር።

ምርመራቸው በሬድዮ የተላለፈባቸው ተመርማሪዎች የደረሰባቸው የግፍ እርምጃ በግልጽ እየታወቀ፣ ከአርባ ዓመት በኋላ ከሕዝብ ለምርመራው የሚረዳ ጥቆማ ለማግኘትና የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠያቂነትና ኃላፊነት ለወደፊት ለማስገንዘብም ነው ምርመራውን እናስተላልፍ የነበረው ብሎ ዛሬ መመጻደቅ በሰው ቁስል እንጨት መስደድ ነው።

የኮምሲዮኑ የማዋከብ ጥያቄና የተመርማሪዎቹ የተሸማቀቀ መልስ፣ መርማሪዎቹን በተለይ ቀደም ቀደም ይሉ የነበሩትን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን እና / በረከት ሀብተሥላሴን ሕዝባዊ ደፋርና ጀግና ሲያስመስል፣ ተመርማሪዎቹን በተቃራኒው በጭፍን በዳዮች አድርጎ አሳይቷል። በጊዜው የነበረውን ሕዝባዊ ስሜት ሆን ብሎ ያጋጋለና ያባባሰ፣ የቀድሞ ባለሥልጣኖችን በጅምላ እንዲናቁና እንዲጠሉ ያደረገ ተግባር ነበር።

ከዚህ በላይ የተገለጸውን ገጽታ የያዘው የምርመራው አካሄድ በሬድዮ መተላለፉ ሕዝባዊ አመጹን በየቀኑ በተጋጋለ ሁኔታ ለማስቀጠል የሚያስችል የፕሮፖጋንዳ ጠቀሜታ እንዲኖረው አድርጓል። ይህም በወቅቱ የነበረውን የአብዮቱን ሒደት እንዲጧጧፍ የበኩሉን ፈጽሟል።

በአዋጁ ያልተፈቀደለትን የኮምሲዮኑን ጥያቄና የተመርማሪዎቹ መልስ በመገናኛ ብዙኃን በተለይ በሬድዮ እንዲተላለፍ መደረጉ የምርመራው አካሄድ የፖለቲካ ፍጆታ እንዲኖረው አድርጓል። በዚህም ምክንያት አባላቱ ሰብአዊ መብቶችን የመጠበቅ ግዴታቸውን አልተወጡም፤ ሥራቸውንም በትክክልና ያለ አድልዎ ማከናወን አልቻሉም።

የኮሚስዮኑ አባላት ኮሚስዮኑን የግል ፖለቲካ አስተሳሰባቸውን ማስፈጸሚያ መሣርያ አድርገውታል። ብሔራዊና ሰብአዊ መብቶችን የመጠበቅ ግዴታ ያለባቸው ስለመሆኑ፣ ሥራቸውን በትክክለኛነት ያለአድልዎ ማከናወን እንዳለባቸው፣ ማቋቋምያ አዋጁ አስገዳጅ ድንጋጌ የደነገገው ኮሚሲዮኑን እና አባላቱን ከዚህ አስከፊ ጥፋት ለማዳን ነበር።ይሁንና የምርመራው አካሄድ የሕዝብን ስሜት ለፖለቲካ ጠቀሜታ እንዲያነሳሳ በማድረግ፣ የኮሚስዮኑ አባላት በአዋጁ ተወስኖ የተሰጣቸውን ሥልጣን በማን አለብኝነት ጥሰዋል።

የኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. አረመናዊ ጭፍጨፋ ለደርግ ዘመን የጭካኔ ድርጊቶች የመጀመርያ ምዕራፍ ነው። የኮሚስዮኑ ምርመራ በሬድዮ እንዲተላለፍ ማድረጉ ለዚህ አስከፊ ድርጊት ምንም አስተዋጽ አልነበረውም ለማለት መቻሉን እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም።

ለተመርማሪዎቹ ጥበቃ ማድረግ

ምርመራው የተጀመረ ባለሥልጣን ምርመራው በጅምር እያለና ስለመከሰስ ወይም አለመከሰሱ ከመወሰኑ በፊት ከአገር ሊወጣ አይችልም። ይሁን እና ምርመራው ያላለቀለት ባለሥልጣን ለመንግሥት ሥራ ወይም አስገዳጅ በሆነ ምክንያት ከአገር መውጣት ካለበት፣ ኮሚሲዮኑ በቂ ነው የሚለውን ዋስትና አስቀድሞ እንዲሰጥ ከአደረገ በኋላ ተመርማሪው እንዲሄድ መፍቀድ ይችላል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ተመርማሪው ለአስቸኴይ የመንግሥት ሥራ ወደ ውጭ አገር መሄድ ከአለበት የኮሚሲዮኑ ፈቃድ ሳይጠየቅ ባለሥልጣኑ ወደ ውጭ አገር ሊሄድ ይችላል።

በአዋጁ አንቀጽ 9 በተደነገጉት በእነዚህ ሦስት ንዑስ አንቀጾች ተመርማሪው እንኳን ዋስትና የተነፈገው እስረኛ ሊሆን ቀርቶ ካለው ኃላፊነት ላይ መነሳት ያለበት መሆኑን አይደነግግም። እንዲያውም ተመርማሪው ለኮሚሽኑ ቃሉን የሚሰጠው በሥራ ገበታው ላይ እያለ ሊሆን እንደሚችል ነው ከድንጋጌዎቹ መረዳት የሚቻለው።

እንደሚታወቀው ፓርላማው ኮሚስዮኑን በሚያቋቁመው አዋጅ ላይ ገና እየመከረ እያለ ነው ለምርመራው የተጋለጡት ባለሥልጣናት የታሰሩት። ፓርላማው ይህን ሁኔታ እያወቀ ነው ከዚህ በላይ ያለውን የተመርማሪውን ነጻነት የማይገድብ ድንጋጌ አስፍሮ የሚገኘው። ፓርላማው ለተመርማሪው ይህን ሁሉ ጥበቃ የሚያደርገው ኮሚስዮኑ የተመርማሪውን መብት አጥብቆ ተገንዝቦ፣ የሥራ አፈጻጸሙን በድንጋጌው መሠረት በማከናወን የሕግ የበላይነት ሳይጣስ ምርመራውን እንዲያከናወን ለማድረግ ነበር።

አዋጁ እስከዚህ ድረስ ጥበቃ የሚያደርግላቸው የመርማሪ ኮሚስዮኑ ተመርማሪዎች፣ ምርመራቸው በጅምር እያለና ስለመከሰስ ወይም አለመከሰሳቸው ሳይወሰን ጥፋታቸው ስልጣኑ በሆነው ፍርድ ቤት ሳይረጋገጥባቸው፤ እጃቸው በሰንሰለት እየታሰረ ከኮሚስዮኑ ፊት መቅረባቸውና ምርመራው መከናወኑ አግባብ አልነበረም። እንዲሁም ባለሥልጣናቱ እጃቸው በሰንሰለት እንደታሰረ ወደ ኮሚስዮኑ አዳራሽ ሲገቡና ሲወጡ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ሰድበዋቸዋል፤ አፊዘውባቸዋል፤ ኮሚሽኑ ይህን ክልከላ የማድረግ አቅሙ ነበረው፤ ይሁንና ከለላ አላደረገላቸውም። 

ይቀጥላል

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles