የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት ሰባተኛ ዓመት በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ የተከበረው መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር። ግንባታው 65 በመቶ የደረሰው ግድቡ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ የመነጨውን ኃይል የሚያከፋፍሉ ከ35 በላይ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊና ማከፋፈያ ግንባታዎችም እየተካሄዱ መሆናቸውን ያመለከቱት በክብረ በዓሉ የተገኙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ ባለ140 ሜትር ከፍታና 1180 ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የግድቡ ዐቢይ ክፍል ከሚያስፈልገው 10 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ ሙሌት ውስጥ 90 በመቶ መጠናቀቁን እንዲሁም 22 ሚሊየን ሜትር ኪዩቢክ ቁፋሮ መከናወኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል። በዓባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተው ግድቡ ከመነሻው 5250 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ቢታሰብም በሒደት ወደ 6450 ሜጋ ዋት ማደጉ ታውቋል። ፎቶዎቹ የግድቡን የአሁን ገጽታና በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙትን በከፊል ያሳያል፡፡
- ፎቶ በታምራት ጌታቸው