Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመመገቢያ ልኳንዳ ቤቶች አደረጃጀት ይታወቃል?

የመመገቢያ ልኳንዳ ቤቶች አደረጃጀት ይታወቃል?

ቀን:

አቶ በቀለ አበበ ባለልኳንዳ (የሥጋ ነጋዴ) ናቸው፡፡ ልኳንዳ ቤቱም የሚገኘው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት አካባቢ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ንግድ ሥራ ላይ ከተሠማሩ ከ40 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት ከዚሁ ችርቻሮ በሚገኘው ገቢ ነው፡፡ አቶ በቀለን ያገኘሁዋቸው ለሁለት ወራት የተዘጋውን ልኳንዳ ቤት ከፋፍተው ሲየፀዳዱ፣ መስኮቶቹና በሩን የውስጥ ግድግዳውንና ጣሪያውን በነጭ ቀለም ሲያስውቡ ነው፡፡

ሥጋውን እየከተፉ የሚቸረችሩበትንና ሚዛን የሚያስቀምጡበትን ጠረጴዛ እንዲሁም አጥንት የሚፈልጡበት ወይም የሚጨፈጭፉበት ጉቶ መሳይ እንጨት በውኃ የታጠበ ሲሆን፣ ደጃፉ ሲሚንቶ ለብሷል፡፡ እያንዳንዳቸው 100 ሻማ የሆኑ ሁለት አምፖሎች የጣሪያው ኮርኒስ ላይ ተንጠልጥለዋል፡፡ የጤና ምርመራ አድርገው እንደሆነ ጠይቀናቸው የጤና መረጃ እንዳላቸው ሠራተኞቻቸው ግን ይህን መሠል መረጃ ሳይዙ ሥራ እንደማያስጀምሩዋቸው ነግረውናል፡፡

አቶ ታደሰ ኦርዶፋ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ነክ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የምግብ፣ የመጠጥ፣ ጤና ነክ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች የኃይጅንና አካባቢ ጤና አጠባበቅ ብቃት ማረጋገጫ ቁጥጥር ንዑስ የሥራ ሒደት አስተባባሪ ናቸው፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ ልኳንዳ ቤቶች በተሻለ ሁኔታ ፅዳቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ባለፉት ሁለት ወራት ተነግሯቸዋል  በየክፍለ ከተሞች የሚገኙ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችም በሁኔታው ላይ ጠበቅ ያለ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንዲያከናውኑ ተደርጓል፡፡

በልኳንዳ ቤቶች ላይ የሚካሄደው የጤና አጠባበቅ ቁጥጥር ሥራ ተግዳሮት አልተለዩትም፡፡ አንደኛው የልኳንዳ ቤቶች አደረጃጀት ዘመናዊነት ሳይላበሰ ልማዳዊ መሆን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የተጠናከረ በቂ የሆነ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አለመከናወኑ ነው፡፡፡

ሁሉም ልኳንዳ ቤቶች የተቋቋሙት ለዚሁ ሲባል በተሠሩት ቤቶች ሳይሆን ለመኖሪያና ለሌላም አገልግሎት የተዘጋጁ ቤቶችን በመጋራት ወይም በረንዳውን ከለል አድርጎ በመስኮት በኩል መቸርቸር ነው፡፡ የሥጋውም አቀማመጥ መሰላል በሚመስል በእንጨት ርብራብ ላይ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ሥጋው ለብክለት እንዲጋለጥ ያደርገዋል፡፡ በንፁህ አየር እጥረትም የተነሳ ደርቆ መልኩን ሊለውጥ እንደሚችል ነው አስተባባሪው የተናገሩት፡፡

ባለሥልጣኑ ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት የልኳንዳ ወይም የሥጋ ቤቶች ማሟላት ያለባቸውን መሠረታዊ የኃይጂናና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ መሥፈርት አዘጋጅቷል፡፡ ከመሥፈርቱም መካከል ሥጋ ቤቱ በሌላ የንግድ ዘርፍና አለመያዙ ወይም ሌላ ተደራራቢ ንግድ አለመካሄዱ፣ ልኳንዳ ቤቱ ውስጥ የቁርጥ ሥጋና ጥብስ የመሳሰሉትን የምግብ ዝግጅት አለማከናወኑ ለተጠቀሰው ንግድ ዘርፍ ደረጃ ድርጅታዊ ብቃት የተሟላ መሆኑን መረጋገጥ የሚሉ ይገኙበታል፡፡

ከዚህም ሌላ ድርጅቱ ከመኖሪያ ቤት ጋር ያልተያያዘ መሆኑን መረጋገጥ እንዳለበት፣ ከመኪና ማቆሚያ፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከአቧራና ከመሳሰሉ በካይ ነገሮች 100 ሜትር የራቀ፣ ግቢው ውኃ ከሚቋጥር ጉድጓድና ጎርባጣ ቦታዎች፣ አላስፈላጊ ከሆነ ቁጥቋጥና ሳር የፀዳ መሆኑ በአጠቃላይ የድርጀቱ ንፅህና የተጠበቀ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

እንዲሁም ክፍሎቹ በቂ የአየር ዝውውር (የወለሉን 10 በመቶና ከዚያ በላይ ስፋት ያለውና ተከፋች የሆነ) እና የብርሃን ሁኔታ (ማንኛውም ማየት የሚችል ተጠቃሚ የክፍሉን አራቱንም ጥጎች ያለ ምንም ችግር ማየት የሚቻል ከሆነ ወይም ያለምንም ችግር የራሱን እጅ ጽሑፍ ማንበብ የሚችል ከሆነ) ሊኖረው ይገባል፡፡

ወለሉ በሸክላ/ሴራሚክ የተነጠፈ ወይም በሲሚንቶ ሊሾ የሆነ ወይም ከፕላስቲክ ታይል የተነጠፈ ታጣቢና በቀላሉ ሊፀዳ የሚችል፣ ያልተሰነጣጠቀ ወይም ያልተቦረቦረ፣ እንዲሁም ግድግዳው ያልተሰነጣጠቀ፣ ለተባዮች መሸሸጊያ ያልሆነና እስከ 2 ሜትር ከፍታ ድረስ በሴንቴቲክ ቀለም የተቀባ፣ ጣሪያው ኮርኒስ ያለውና ነጭ ሴንቴቲክ ቀለም የተቀባና ፅዳቱን የተጠበቀ፣ የክፍሉ ስፋት ቢያንስ 3 ሜትር፣ በ3 ሜትር መሆን አለበት፡፡

ድርጅቱ ከማዘጋጃ ቤት የቧንቧ ውኃ ወይም አግባብ ባለው አካል ተመርምሮ ለሰው ልጅ ጥቅም እንዲውል የተረጋገጠ የጉድጓድ ወይም ከሌሎች ምንጮች የተገኘ ውኃ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህም ሌላ የሥጋ ማስቀመጫው ሥፍራ የቀዝቃዛው መጠን ከ18 እስከ 22 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሆነና ከዝንብ፣ ከበረሮ፣ ከአይጥና ከሌሎች ነፍሳቶች ለመከላከል የሚያስችልና ለዕይታ ግልጽ የሆነ ፍሪጅ መኖር አለበት፡፡

ንፅህናቸው የተጠበቀና የማይዝጉ ሜንጦዎች ዝግጅት፣ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ከፕላስቲክ ወይም ከብረት የተሠራ ክዳን ያለውና በእግር ሲረገጥ የሚሠራ ማጠራቀሚያና በቀላሉ መፅዳት የሚችል መሆንና የእሳት አደጋ ማጥፊያም፣ የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ መስጫም፣ በክፍሉ ዝንብ የሚይዝ (ፍላይ ትራን) መኖር አለበት፡፡

ሠራተኞች ቢያንስ በየስድስት ወሩ ሊታደስ የሚችል የጤና መረጃ፣ ነጭ የሥራ ልብስ ጋዎን፣ ሽፍን ጫማ፣ ቆብ ከነቅያሬው ሊኖራቸው እንደሚገባ የግል ንጽሕናቸው የተጠበቀ መሆን ይገባዋል፡፡

የመፀዳጃ ቤቱ ስፋት ቢያንስ 1.2 ሜትር በ1.2 ሜትር የሆነና ከፍታው 2.4 ሜትር ሲሆን፣ አጠገብም የእጅ መታጠቢያ ሊኖረው ይገባል፡፡ በድርጅቱ አገልግሎቶች በሚሰጥባቸው ቦታዎች ማጨስ ክልክል ሲሆን ‹‹ሲጃራ ማጨስ ክልክል ነው›› የሚል ጽሑፍ በየክፍሎቹ በግልጽ መለጠፍ አለበት፡፡

እያንዳንዱ ልኳንዳ ቤት የየብቃት መረጋገጥ የምስክር ወረቀት፣ የሠራተኞች የጤና ምርመራ ካርድ፣ የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ የተወገደባቸውና ለሥጋ ሕጋዊ የሆነ የቄራ ደረሰኝ ሊኖረው እንደሚገባ መሥፈርቱ መጠቆሙን አስተባብረው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...