Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበቆራሊዮ አምሳል

በቆራሊዮ አምሳል

ቀን:

‹‹አሮጌ ጫማ ብልቃጥ ጠርሙስ ቆርቆሮ ያለው›› የሚለውን ለየት ያለ ዘዬ ያለውን የቆራሊዮ ጥሪ ተከትለው ከበረንዳ ጫማ፣ ከመደርደሪያ ጠርሙስ፣ ከጓሮ መዘፍዘፊያና የብረት ቁርጥራጭ ይዘው የሮጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ ቆራሊዮ የበርካቶች የልጅነት ትዝታም ጭምር ነው፡፡ የቅባት ጠርሙስ በ30 ሳንቲም ሸጠው ብስኩት ገዝተው የበሉ ብዙ ናቸው፡፡ አይጠቅሙም ተብለው የተጣሉ ቅራቅምቦዎች ሳይቀሩ ለቆራሊዮ ዋጋ አላቸው፡፡ በሥራ ብዛት ቀለሙ ወደ አፈርማነት የተቀየረ ቱታቸውን እንደነገሩ ለብሰውና ከየቤቱ ለቃቅመው የሚገዟቸውን ኮተቶች በጀርባቸው በሚይዙት ማዳበሪያቸው ሸክፈው በየጉራንጉሩ ሲዞሩ ቆራሊዮዎችን የማያውቃቸው የለም፡፡

አገልግሎታቸውን የጨረሱ ቁሳቁሶችን ዳግም ወደ ሥራ የማስገባት (ሪሳይክል) ጅማሮ በየጉራንጉሩ በሚዞሩ በቆራሊዮዎች ጥሪ በ‹‹አሮጌ ጫማ ብልቃጥ ጠርሙስ ያለው›› ማስታወቂያ እንደሆነ ይወሳል፡፡ ከተጀመረ አሠርታት ያለፉ ቢሆንም በኢትዮጵያ ምን ያህል የሪሳይክል ባህል ዳብሯል የሚለው ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ብቅ ብቅ የሚሉ ወጣቶችና ድርጅቶች የፈጠራ ሥራዎችን አገልግሎታቸውን በጨረሱ ቁሳቁሶች የማስጌጥና የማሳመር ነገር ይዘው ሲወጡ ይታያል፡፡

በተለያዩ ባህላዊ ጌጦች ወዳሸበረቀው ወደ ወይዘሪት ሚስጥር ጎሳዬ ሱቅ ሲገቡም ይህንኑ ያስተውላሉ፡፡ በሱቁ የአገልግሎት ጊዜያቸውን በጨረሱ ቁሳቁሶች በቀንድና በሸክላ የተሠሩት የግድግዳና የጠረጴዛ ማስጌጫዎች በመልክ በመልኩ ተደርድረዋል፡፡ ቀጨኔ በሚገኙ የእጅ ባለሙያዎች ያሠራቻቸው ቄንጠኛ ማሰሮዎች በእጅ የተሠሩ መሆናቸውን ለማወቅ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ቀለም ቅቡና አጠቃላይ መዋቅሩ ማሰሮዎቹ ከባሕር ማዶ የገቡ ያስመስላቸዋል፡፡ የቅል ስባሪዎች፣ የፕላስቲክና የመስታወት ቁርጥራጮች ሳይቀሩ በኅብረ ቀለም አሸብርቀው በቆሻሻ ፋንታ ማስጌጫ ሆነዋል፡፡ የአካባቢ ጤና በማቃወስ የሚታወቁ ፌስታሎች ሳይቀሩ ቅንጡ የግድግዳ ጌጥ ሆነዋል፡፡

- Advertisement -

የዚህ ፈጠራ ባለቤት ሚስጥር ወደዚህ ሥራ ከገባች ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡፡ ወደ ሥራው የገባችው በአጋጣሚ ሲሆን፣ ክስተቱን ምን መሥራት እንደምፈልግና ለምን እንደተፈጠርኩ ያወኩበት አጋጣሚ ስትል ትገልጸዋል፡፡ ልጅ እያለች የነበራት ምኞት ከሌሎቹ የዕድሜ እኩዮቿ በተለየ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መሆን ነበር፡፡ ያላትን የሥዕል ችሎታ የተመለከቱ አርክቴክትነት ጥሪዋ መሆኑን ሲነግሯት ደግሞ ርዕሰ መምህርነቱን ትታ አርክቴክት እሆናለሁ ብላ ነበር፡፡ ዲግሪዋን የያዘችው ግን በኮምፒውተር ሳይንስ ስለነበር ሁሉንም ትታ በተማረችበት ሙያ የምትቀጥል መስሏትም ነበር፡፡ የሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እስክትሆን ድረስ ትክክለኛ ጥሪዋን አላወቀችውም ነበር፡፡

‹‹አዲስ የተጋቡ ጓደኞቼ ቤታቸውን ዲኮር ያደርጉ ነበር፡፡ በጣም በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮችን ከውጭ የገቡና በውድ ዋጋ በሚሸጡ ዕቃዎችን ሲገዙ አየሁ፡፡ ያ አጋጣሚ ምን ማድረግ እንደምፈልግ ያወቅኩበት ነበር የምትለው ሚስጥር ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን መተካት የሚችሉ የራሷን ሥራዎች የመሥራት ውሳኔ ላይ የደረሰችበት አጋጣሚ ትናገራለች፡፡

ፍላጎቷን ለይታ ካወቀች በኋላ ሁሉም አጋጣሚዎች አዲስ ነገር መሥራት የሚያስችላትትን መንገድ ያሳዩዋት እንደነበር ‹‹መተኛት እስኪያቅተኝ ድረስ አዳዲስ ሐሳቦች ይመጡልኛል፤›› ስትል ያደረባትን መነሳሳት ትገልጻለች፡፡

ወደ ሥራው ለመግባት ያስፈልጋት የነበረውን መነሻ ገንዘብ ለማግኘቱ ከሰው አልጠየቀችም አልያም ዕቁብ አልሰበሰበችም፡፡ በተማረችበት ሙያ ለአንድ ድርጅት ተቀጥራ መሥራት ጀመረች፡፡ ጥቂት ሠርታ መነሻ የሚሆናትን ካጠራቀመች በኋላ ወደ ራሷ ሥራ ገባች፡፡ ነገሮችን ግን ቀላል አልነበሩም፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል የሥዕል ትምህርት ሥልጠና ወስዳለች፡፡ በዚህ መሠረታዊ የሥነ ጥበብ ዕውቀት መቅሰም ችላለች፡፡

ነገር ግን ቄራ ሄዳ ሽታው የማያስቀርበውን ቀንድ ከትሉና ከወረረው ጉንዳን ለይቶ ማውጣትና እንዴት አሰማምሮ ጌጥ ማድረግ እንደሚቻል የምታውቀው አልነበራትም፡፡ የነበራት ነገር ሁሉንም እንድትሞክር የሚገፋፋትት ህልሟ ብቻ ነበር፡፡ ‹‹ቄራ ሄጄ ቀንድ ስገዛ የሚሆነኝን እኔው መራርጬ ነው የምወስደው፡፡ ሽታው በጣም ከባድ ነው፡፡ ትል የያዘ ቀንድ ሁሉ ያጋጥማል፤›› የምትለው ምሥጢር አንዱን ቀንድ በአምስት ብር ገዝታ በቀላሉ አሽሞንሙና ጌጥ የምታደርገው መስሏት ነበር፡፡

ከባድ ልፋት እንዳለው የተረዳችው ከቀንድ ባህላዊ ቁሳቁሶችን የሚሠሩ ባለሙያዎችን በቀላሉ ማግኘት ሲያቅታትና ካገኘቻቸውም በኋላ ያቀረበችላቸውን አዲስ ሐሳብ ለመቀበል ሲቸገሩ ነበር፡፡ ምንና እንዴት ማድረግ እንዳለባት የሚነግራትም አልነበረም፡፡ ስለዚህም ራሷን ኦንላይን ለማስተማር ወሰነች፡፡ ይህም ቀላል አልነበረም፡፡ ቀንዱን ጌጥ ለማድረግ አንድ ዓመት ያህል ፈጀባት፡፡ ልፋቱ በዝቶባት ትታው ነበር ነገር ግን ተስፋ አልቆረጠችምና እንደገና ትግል ገጠመች፡፡

የቅድመ ማዘጋጀት ሥራውን የሚያግዟት ሌሎች ባለሙያዎችም አገኘች፡፡ ከዚያም ነገሮች መንገድ መንገዳቸውን ያዙላት፡፡ የተማረችበትን ሙያ ትታ በሌላ መሰማራቷን ብዙዎች ከእብደት ነበር የቆጠሩት፡፡ ያበረታቷት የነበሩት አባቷ ነበሩ፡፡ የመጀመርያ ሥራዎቿን የገዟት ደንበኛዋም አባትየው ነበሩ፡፡ የመጀመሪያ ሁለት ሥራዎቿን በ5000 ብር ነበር፡፡ ‹‹ይህን በዚህ እሸጣለሁ ብዬ ዋጋ አላወጣሁለትም ነበር፡፡ ለነገሩ የትኛው ምን ያህል እንደሚያወጣም በውል አላውቅም ነበር፡፡ ለእኔ ግን ትልቅ ሞራል ሰጠኝ፡፡ በ5000 ብሩ የተለያዩ የጎደሉኝን ነገሮች አሟላሁበት፤›› ትላለች ጅምሯን ስትገልጽ፡፡

እንዲህ ያማረ ሱቋ ገብተው ሐሳቧን ደግፈው አመስግነው ከሚገዟት ውጪ ያፈሰሰችበትን ጉልበትና ጥበብ ከምንም ሳይጨምሩ ‹‹ፌስታል አይደል ቀንሰሽ ሽጪ›› የሚሏት ያጋጥሟታል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በዚህ ሙያ የመቀጠል ተስፋ እንዳለ፣ አጠቃላይ የማኅበረሰቡ ምላሽም ጥሩ እንደሆነ የምትናገረው ሚስጥር ‹‹ማኅበረሰቡ አይገዛኝም አያበረታታንም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ጥሩ ነገር ሠርተን እንዲገዛን ማስገደድ ነው ያለብን እንጂ እንዲያበረታታን ያልወደደውን ነገር መግዛት አለበት የሚል እምነት የለኝም፤›› ትላለች፡፡

በተመሳሳይ የሪሳይክል ቢዝነስ ዘርፍ የተሰማራችው ሃና ሽፈራው በጋዜጣና በሌሎች በቀለማት ባሸበረቁ የወረቀት ምርቶች የሴቶች ቦርሳ፣ ሰሃን፣ ማሠሮ፣ የአበባ መትከያ፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቅርጫቶችና የመስታወት ፍሬሞችን ትሠራለች፡፡ በየቢሮውና በየእልፍኙ ለሚጠራቀመው አታካች የወረቀት ምርቶች መፍትሔ የዘየደችው ሃና በዚህ ሥራ የተሰማራችው ለሙያው ብቁ የሚያደርጋትን ዝግጅት ትምህርት ቤት ገብታ አግኝታ አይደለም ለዚህ የበቃችው፡፡ በኢንተርኔት መረብ ላይ በሚገኙ ቪዲዮዎች በመታገዝ ነው፡፡ ወደ ሥራው ከገባች ሁለት ዓመታት ያህል እንዳስቆጠረች ትናገራለች፡፡

መሰንበቻውን በሚሌኒየም አዳራሽ በተከፈተው የንግድ ዓውደ ርዕይ የምታዘጋጃቸውን በወረቀት የተሠሩ ምርቶች ይዛ ተገኝታለች፡፡ በወረቀት የተሠሩ የቆሎ ማቅረቢያ ሰሃኖቿ ባለሙያ እመቤት በስንደዶ ጥብቅ አድርጋ የሰፋችው ስፌት ይመስላሉ፡፡ የአንገት ጌጦችና ቄንጠኛ ኮፍያም ትሠራለች፡፡ በቀጫጭኑ ቆራርጣ የምታዘጋጀውን ወረቀት በኮላ አጣብቆ በቫርኒሽ አሳምሮ ለገበያ ማቅረቧ የብዙዎችን ትኩረት እንድትስብ ያደረጋት አጋጣሚ ነው፡፡ ዓውደ ርዕዩን የሚጎበኙ ሁሉ ወደ ሃና መደብ ገብተው ዕቃዎቹን እያገላበጡ የሚያዩት ፍጹም በሆነ ደስታና አድናቆት ነው፡፡ ያመጣቻቸውን ዕቃዎች ከፊሉን ሸጣ የጨረሰችው ብዙም ሳትቆይ ነው፡፡

እንደ ሚስጥርና ሃና ያሉ በሪሳይክል የሥራ መስክ የተሰማሩ ወጣቶች ቆሻሻ ሁሉ መወገድ እንደሌለበት፣ ይልቁኑ ቀደም ሲል ከተፈጠረለት ዓላማ የበለጠ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል ያሳያሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ፕላስቲክ የውኃ ጠርሙሶችን በመልክ በመልካቸው ሰካክቶ ቤት መገንባት፣ አጥር ማዘጋጀትና መልሶ ለሌሎች ተግባራት እንዲውል ማድረግ እየተለመለደ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ከቆራሊዮ ተነስቶ እዚህ የደረሰው የሪሳይክል መስክ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በአካባቢ ፅዳትና ጤና ላይ የሚኖረው ፋይዳም የጎላ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ እርጥቡን ቆሻሻ ለባዮማስ፣ ደረቁን ደግሞ እንደዚህ ለተለያዩ ተግባራት ማዋል ከተቻለ እንደ ቆሼ ያሉ የቆሻሻ መጣያዎችን ወደ የሀብት ክምር የሚቀየሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...