Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተስፋ የሚያደርጉ ትጉሃን ናቸው!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ሰነበታችሁ ወገኖቼ፡፡ ‹መሰንበት ደጉ ብዙ አሳየን› የሚለው አገርኛ አባባል ጥልቅ የሆነ እሳቤ እንዳለው ሲነግረኝ የሰነበተው ምሁሩ የባሻዬ ልዩ ነው፡፡ የዕድሜ ባለፀጋው አባቱ ባሻዬ ደግሞ፣ ‹‹ዕድሜ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በፆም የፍስክ ላበሉን፣ በመልካም ንግግራቸው ጮማ ላስቆረጡን፡፡ ያውም ከቤተ መንግሥት ሆነው…›› እያሉ ደስታቸውን ያለመጠን እየገለጹ ነበር የሰነበቱት፡፡ ልጃቸውም ቢሆን፣ ‹‹እነሆ ድርብ ትንሳዔ የምናከብርበት ዘመን ነው፤›› በማለት ሲቦርቅ ነበር፡፡ ውዷ ማንጠግቦሽ እንዲህ ስትብነሸነሽ ዓይቻት አላውቅም፡፡ መቼም ከፖለቲካው እጅግ የራቀች ናት ብዬ የማስባት ማንጠገቦሽ፣ ‹‹በርካታ ኢትዮጵያዊያንን አገኘሁ፤›› ስትለኝ፡፡ ንግግሯ አስገርሞኝ፣ ‹‹ወይ ማንጠግቦሽ አገሩ የመላው ኢትዮጵያዊያን አይደለም እንዴ?›› አልኳት ሐሳቧን በደንብ እንድታብራራልኝ በመጓጓት፡፡ ሰሞኑን እንዴት እንዳማረባት ልገልጠው አልችልም፡፡

ወዳጆቼ ልብ በሉልኝ መቼም ፆመኛ ነኝና በዚህ በታላቁ ፆም ቀናት ትንንሾቹ ፆሞችም ላይ ቢሆን አልነካትም፡፡ ምክንያቱም እሷ ሁሉንም አፅዋማት ስለምትፆም፣ እኔ ባልፆም እንኳን ለእሷ ስል እችለዋለሁ፡፡ እዚህ ታላቁ ፆም ላይ ግን ሁላችንም ተስማምተን ነው የምንፆመው፡፡ የምንጿጿመው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታዲያ በሌሊቱ አንዳች ጋኔል በጆሮዬ እየመጣ፣ ‹‹ፆሙን አፍርስ አፍርስ፣ እቀፋት… እቀፋት›› ይለኛል፡፡ በዚህኛው ፆም ላይ ይኼ ወቅት እየጠበቀ የሚመጣ ጋኔል ለዘመናት ሽሬው የማላውቀውን ጾም እንድሽረው እየወሰወሰኝ ነበር፡፡

የእኔ ውድ ማንጠግቦሽ የጎረምሳነት ጉልበቴን ያንበረከከኝ ጀግና ናት፡፡ ከውስጥ በመልካም ሰብዕና ታንፃ የተሠራች፣ ከውጭም ቢሆን ጠቢብ አንጥረኛ ተጨንቆ የሠራት ውብ፡፡ ሁለመናዋን ለአፍታ ሰከን ብዬ ስመለከታት ደግመህ ደጋግመህ አግባት፣ ደግመህ ደጋግመህ አወድሳት፣ በፍቅርህ ላይ ፍቅርን ጨምር ይለኛል፡፡ ዛሬ ደግሞ ይባስ ብላ ፖለቲካኛ ሆናልኛለች፡፡ ምን ያንሳታል? ወርቅ ብርቅ በሆነበት ዘመን አምላኬ የሰጠኝ እንቁዬ ናት ማንጠግቦሽ፡፡ ማንጠግቦሽዬ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን አገኘሁ ያለችውን ሐሳብ እንዲህ በማለት አብራራችልኝ፡፡

‹‹ከተማው ውስጥ ወደ ገበያም ዞር ዞር ባልኩበት ወቅት በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ተገናኘሁ፤›› ብላኝ እርፍ፡፡ እኔም ተገርሜ የኢትዮጵያ ዋና ከተማና መዲና በምትባል አዲስ አበባ ውስጥ እየኖርን፣ ‹‹በርካታ ኢትዮጵያዊያንን አገኘሁ ማለት ምን የሚሉት ፍልስፍና ነው?›› አልኳት፡፡ መቼም ይኼንን ሐሳብ ሌላ ሰው ቢሆን ያነሳው እኔም የባሻዬ ልጅም ተባብረን፣ ‹‹ቅዥታም! ቅዥትህን ወደዚያ ሄደህ አራምድ›› በማለት ነበር የምናባርረው፡፡ ከማንጠግቦሽ ዘንድ ሲመጣ ግን ቅዥቱ ፍልስፍና ይባላል፡፡ ስካር የሚመስል ሐሳብ ደግሞ ማስተዋል፡፡ ማንጠግቦሽ ናታ! የቤታችን መሠረት የመፅናቱ አንደኛው ምክንያት ይኼም ነው፡፡

የእሷ አስተሳሰብ ግን ቅዥት አልነበረም፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ መዲና በምትባል አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ኢትዮጵያዊነት መሰንበቻውን ዘረኝነት ገኖ ቆይቶ ነበር፡፡ በእውነቱ ማንጠግቦሽ እንዴት እንዳስተዋለችው ተገርሜያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ እኔ ታላቁ ምስክር ነኝ፡፡ ለሥራ በዞርኩባቸው አካባቢዎች ሁሉ ዘርን መሠረት ያደረጉ መጠጥ ቤቶች፣ ዘርን መሠረት ያደረጉ ሠፈሮች፣ ዘርን መሠረት ያደረጉ መዝናኛ ሥፍራዎችን ተመልክቻለሁ፡፡ ታዲያ እነዚህ ስማቸውን እዚህ ጋር የማልጠራላችሁ ሠፈሮች ስትሄዱ አንድ ብሔር ገዝፎ፣ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ኮስምኖ ታገኛላችሁ፡፡ ስለዚህ ምናልባት በኢትዮጵያዊነታችሁ የማትኮሩ ምስኪን ከሆናችሁ፣ ምነው ከዚህ ብሔር በተፈጠርኩ ብለው ሊያስቡም ይችላሉ፡፡ ዳሩ ግን እውነታው የባሻዬ ልጅ አዘውትሮ፣ ‹‹ከኢትዮጵያዊነት የሚገዝፍ ብሔር ሊኖር አይገባም፤›› የሚል ፅኑ አቋም አለው፡፡

ይበልጥ ያስገረመኝ ይኼ ጉድ በአንዳንድ ቦታዎች ብቻ ተወስኖ የቀረ ይመስለኝ ነበር፡፡ እንደዚህ ታች ድረስ ወርዶ እነማንጠግቦሽ ሠፈር ድረስ ያንጎዳጉዳል ብዬ ገምቼም አላውቅም ነበር፡፡ ማንጠግቦሽ ምን አለች? ‹‹ዘረኝነት እንደ ቫይረስ ነው፡፡ የተማረና ያልተማረ አይመርጥም፤ ወንድ፣ ሴት፣ ሕፃን፣ አዋቂ አይለይም፡፡ መልኩንና ባህሪውን እየቀያየረ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ የመሰንቀር ምትሃታዊ ባህሪ አለው፤›› በማለት ስለአስከፊነቱን በገባት መንገድ የገለጠችው፡፡

ባሻዬም ቢሆኑ የማንጠግቦሽ ሐሳብ በጣም ነበር ያስደሰታቸው፡፡ ‹‹በመዲናችን እየጠፋ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ዳግም ልደቱንና ትንሳዔውን እያገኘ ነው፤›› በማለት አብራሩ፡፡ የባሻዬም ልጅ እንደ መቀለድ እያለ፣ የአባቱን ሐሳብ ደገፈላቸው፡፡ ‹‹ይኼንን ትንሳዔ ለየት የሚያደርገው ዘረኝነት ከምድራችን ተወግዶ ኢትዮጵያዊነት ገኖ የምናከብረው መሆኑ ነው፡፡ ይኼንን ትንሳዔ ድርብ ትንሳዔ ብለን ልንሰይመው እንችላለን፡፡ አንድም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት በመሆኑ፣ ለመላው ክርስቲያኖች የፈንጠዚያና የደስታ በዓል ነው፤›› እያለ ሲያስረዳ ባሻዬ ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ እንዲህም በማለት ወሬውን ቀጠሉለት፡፡

‹‹እኔ እኮ እንዲያው የአባትህን እምነት ዘመናዊ ነኝ ብለህ በማሰብ አሽቀንጥረህ የጣልከው መስሎኝ ነበር፤›› በማለት በግርምት አትኩረው ተመለከቱት፡፡ እሱም ቢሆን የአባቱን እምነት የሚጥል ዓይነት ሰው ስላልነበረ፣ ‹‹አባቴ ሆይ በመስቀል ላይ የተሠራውን ታላቅ ሥራ የምዘነጋ ሰው አድርገህ እንዳታስበኝ፡፡ በባህሪው አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ብሎ በመስቀል ላይ የተንጠለጠለበትን የባሪያን መልክ የያዘበትን፣ የተተፋበትን፣ የተናቀበትን፣ የሞተበትን፣ ሞቶም ያልቀረበትን፣ ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን የተነሳበትን ይኼንን ሁሉ እኮ ከሕፃንነቴ ጀምሮ ስታስተምረኝ ነው ያደግኩት፡፡ እንዴት ብዬ ልዘነጋው እችላለሁ?›› በማለት የአባቱን ልብ አሞቀ፡፡ ባሻዬም፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ምንም አያሰጋኝም፣ ዋናውን ይዘኸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን መጨመር እንኳን አይከብድህም፤›› በማለት ለልጃቸው ያላቸውን አድናቆትና አክብሮት ገለጹለት፡፡

ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ እንዳለችው በርካታ ኢትዮጵያውያን በዝተውልናል፡፡ ይኼንን የትንሳዔ በዓል ባሻዬ እንደሚሉት ሸማ ደረብ አድርጎ ድርብ ፋሲኪ ማክበር ነው፡፡ በተለይም የዘረኝነትን አስከፊ ገጽታ ያየ ሁሉ በዘረኘነት እንደ ቀልድ የተጀመሩ አድመኝነቶችና ቡድንተኝነቶች የት እንደ ደረሱ መቼም እዚህ ለማንሳት አልሞክርም፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እነሆ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊነታቸው የሚመኩባት ኢትዮጵያ እየተፈጠረች ነው፤›› በማለት ሲያስረዳ አድምጬዋለሁ፡፡ አክሎም፣ ‹‹በመታወቂያዬ ላይ ያለውን ብሔሬን ፈራሁት፣ ኢትዮጵያዊነቴን የሚቀማኝ ስለመሰለኝ፤›› በማለት ፈርቶ የማያውቀው የባሻዬ ልጅ ፍርኃቱን አጫውቶኝ ነበር፡፡

እኔም ብሆን ቀስ ብዬ መታወቂያዬን አወጣሁና ‹‹ብሔር›› የሚለውን ተመለከትኩትና ፈራሁት፡፡ ምክንያቱም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ የምወደውና የምኮራበት ብሔር ቢኖረኝም፣ ኢትዮጵያዊነቴን ልቀማህ ካለኝ ግን ጥንቅር ብሎ ገደል ይግባ እላለሁ፡፡ ለዘሬና ለዘር ማንዘሬ የማወርሰው ሀብት ቢኖር ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ነው፡፡ የባሻዬ ልጅ ሁልጊዜም ቢሆን ለልጄ የምነግረው ሚስጥር አለ ብሎ እንዲህ ሲል አጫውቶኛል፡፡ ‹‹ልጄ ሆይ ይኼንን ትልቅ ሚስጥር በልብህ ጽላት ውስጥ አሳድር ለልጅ ልጆችህም አብስር፡፡… አባቴ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ እኔንም ኢትዮጵያዊ አድርጎኛል፡፡ አንተም ኢትዮጵያዊ ሁን፤›› እለዋለሁ ብሎኝ ነበር፡፡

አንዴት ያለች ድንቅ ምክር ናት፡፡ ወዳጆቼ እኔም ብሆን ለልጄ ከዚህ የተለየ ምክር የለኝም፡፡ እንደዚህ ነው የምለው፣ ‹‹ልጄ ሆይ ዘርህ ኢትዮጵያ ነው፣ ብሔርህም ኢትዮጵያዊ፣ አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ፡፡ የአንተ ጠላት ይኼንን እውነት ሊንድብህ የመጣው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ጠላት የለህም…›› ብዬ ይኼንን ታላቅ ሀብት ነው ማውረስ የምፈልገው፡፡

ወደጆቼ እናንተም ብትሆኑ ለልጆቻችሁ የምታወርሱትን እንድታሰላስሉ የቤት ሥራ እየሰጠሁ ወደ መሰናበቻዬ ልቃረብ፡፡ በዚህ ድርብ የትንሳዔ በዓል ጮማ ሳይበዛ፣ ለጤና በመጠንቀቅ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከዳር እስከ ዳር በማስተጋባት የምታሳልፉበት በዓል እንዲሆን ከልብ የመነጨ ምኞት ሳልገልጥ አላልፍም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ የሚል ነገር አበዛሁ መሰለኝ? ምን ላድርግ ዕድሜ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአንዲት ከአርባ ደቂቃ በማትበልጥ ንግግራቸው እኮ ነው ከ30 ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን ያስገቡት፡፡ ታዲያ እኔ በእሳቸው ብወጣ ምን ይገርማል? ይኸው እኔም ለእናንተ መልሼ እያወጣሁ ነው፡፡ ዘረኝነትን ዘርተን መቼም ፍቅርን አናጭድም ኢትዮጵያዊነትንም ስንዘራ መልሰን የምናጭደው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ እናም ባሻዬ እንደሚሉት ዘርን ማስተካከል ነው፡፡ ወዳጆቼ አሁን በጥቂቱም ቢሆን የተረዳችሁኝ ይመስለኛል፡፡ አሁን የማትረዱኝ ደግሞ ቆይታችሁ ትረዱኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ተስፋ የሚያደርጉ ትጉሃን ናቸው፡፡  አሁንም ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! መልካም ትንሳዔ! መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት