Wednesday, March 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ የምትደምቀው በልጆቿ አንድነት ነው!

ኢትዮጵያ ታሪካዊ አገር ናት ሲባል ያለፈችባቸው ዘመናት ውስብስብ እንደነበሩም መዘንጋት አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩን ነፃነት ለማስከበር ያደረጋቸው ተጋድሎዎች፣ ለመብቱና ለነፃነቱ ያደረጋቸው ፍልሚያዎች፣ የማንነትና የሐሳብ ብዝኃነት ባለመስተናገዳቸው ሳቢያ የተፈጠሩ ግጭቶች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሥልጣኔዋ ተለያይታ ለድህነትና ለተመፅዋችነት የተጋለጠችበት አሳፋሪ ውርደት የታሪኳ አካል ናቸው፡፡ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በአንድነት በመመከት አንፀባራቂ ታሪክ ያላትን ያህል፣ በእኩልነትና በሰላም ለመኖር ባለመቻሉ ምክንያት በርካታ ቅራኔዎችና ፍትጊያዎች የተደረጉባት ናት፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረችው፣ በሕዝቧ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት መሆኑን ግን መቼም ቢሆን መዘንጋት አይቻልም፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ የጋራ እሴቶቹን አስከብሮ በአንድነት የኖረው ደግሞ ለአገሩ በነበረው ወሰን የሌለው ፍቅር ነው፡፡ በዚህ ዘመን የአስተዋዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተምሳሌታዊነትና አገር በቀል ዕውቀት በማከል፣ ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነቷ ለመመለስ ይህ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የምትደምቀው በልጆቿ አንድነት ነውና፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ያመለጡንን መልካም አጋጣሚዎች በቁጭት እያስታወስን፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ የመሥራት ትልቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ አገር የምትገነባው በመላ ልጆቿ ያልተቆጠበ ተሳትፎ ስለሆነ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ለሚረከቡ ትውልዶች መሠረት መጣል የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተሰብ የአገር መሠረት እንደመሆኑ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በአገር ፍቅር ስሜት ማነፅ አለባቸው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ኅብረተሰቡ፣ ወዘተ. በየደረጃው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ አገርን የመምራት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ደግሞ በሕግ የበላይነት የምትተዳደር አገር እንድትኖርና ትውልዱ በሥርዓት እንዲታነፅ፣ አርዓያነት ያለው ተግባር ይጠበቅበታል፡፡ ከቤተሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ባሉ መስተጋብሮች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በአገር ፍቅር ስሜት ከተንቀሳቀሱ፣ የአገር ልማት የጋራ ይሆናል፡፡ እኩልነት ይፈጠራል፡፡ ፍትሐዊነት የአገር ወግና ባህል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይደምቃል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በበዓላት፣ በሐዘንና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮቻቸው ለሰንደቅ ዓላማቸው ቀናዒነታቸውን ማሳየታቸው እንግዳ አይደለም፡፡ ሰንደቅ ዓላማው የትስስራቸውና የአንድነታቸው ምልክት ነው፡፡ ከዚህ ምልክት ጀምሮ በአጠቃላይ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለመስማማት መቀራረብና መነጋገር አለባቸው፡፡ አንድነት ልዩነትን ያከበረ የጋራ መስተጋብር ስለሆነ፣ ከምንም ጉዳይ በፊት በአገር የጋራ ጉዳዮች ላይ መነጋገርና መደማመጥ የአገር ባህል መሆን አለበት፡፡ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት የሚኖረው በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት መቀራረብ ሲቻል ነው፡፡ የዴሞክራሲ ችግኝ ተኮትኩቶ እንዲፀድቅ ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ይገባል፡፡ ሐሳብን ማጣጣል ወይም መደፍጠጥ ጤነኛ ባለመሆኑ፣ ሐሳቦች በነፃነት እንዲወዳደሩ ዕድል መስጠት ተገቢ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን የሚያግባባ አማካይ መፍጠር ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ከእኔ በላይ ላሳር ብሎ መኮፈስና ለለውጥ መሰናክል መሆን ለአገር አይጠቅምም፡፡ የፖለቲካ ትግሉ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን የሚችለው፣ የአስተዋዮቹን ኢትዮጵያዊያን ባህሪ መላበስ ሲቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትደምቀው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትጉሃን ቅን ልጆቿ መዘናጋት የለባቸውም፡፡

መቼም ቢሆን ስህተት ያጋጥማል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ከስህተት መማር ነው፡፡ ለጠባብ ፖለቲካዊ መስመር ብቻ ሲባል አገርን ዘንግቶ ሥልጣንን የሁሉም ነገር ግብ ማድረግ፣ ውድቀት እንጂ ዕድገት አያመጣም፡፡ ይህ ዓይነቱ ስህተት ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ የንፁኃን ወገኖቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ብዙዎችን ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ዳርጓል፡፡ መጠኑ የማይታወቅ የአገር ሀብት አውድሟል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ስህተት በመማር አገርን ማሰብ ይገባል፡፡ ከኢሕአዴግ ጀምሮ በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖች በሙሉ፣ ከስህተታቸው በመማር ኢትዮጵያን የማዳን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከሥልጣን በፊት አገር ትቅደም፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብና ይህች ታሪካዊት አገር ሊከበሩ ይገባል፡፡ ይህ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ መደመጥ አለበት፡፡ ፖለቲካ በጥበብ እንጂ በነሲብ አይመራም፡፡ በሴራ የትም አይደረስም፡፡ በአስመሳይነትና በአድርባይነትም ፈቀቅ አይባልም፡፡ ከዘመኑ ትውልድ የመጠቀ አስተሳሰብና ፍላጎት ጋር መራመድ አለመቻልም ፋይዳ የለውም፡፡ ያለፉት ስህተቶች ታርመው ኢትዮጵያን ማድመቅ ይገባል፡፡ የወቅቱ የሕዝብ ፍላጎት ይኼ ነው፡፡

ስሜታዊነት በምክንያታዊነት ካልተገራ አገር እንደሚያተራምስና ሕዝብንም ቀውስ ውስጥ እንደሚከት ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡ ተወደደም ተጠላም ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት አገሪቱ ገጽታዋን እየቀየረች መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ በተለይ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶች የበለጠ ጎርምተው አገር ወደፊት እንድትገሰግስ መሠረት ጥለዋል፡፡ ይህ በሕዝብ ተሳትፎና ፍትሕዊ ተጠቃሚነት ታጅቦ የበለጠ መቀጠል አለበት፡፡ ሕዝቡ የልማቱ ባለቤት የሆነበት ዕድገት ደግሞ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ያግባባል፡፡ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚታየው የሚያንገሸግሽ ፈተና ግን ብዙ የቤት ሥራ አለበት፡፡ ይህ ፈተና ብዙዎችን ለመከራ ዳርጓል፡፡ ምክንያታዊነት እንዲጠፋና ስሜታዊነት እንዲስፋፋ ዕገዛ አድርጓል፡፡ በዚህም ሳቢያ አገር ታውካለች፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት መቀልበስ አለበት፡፡ ከስሜታዊነት የፀዳ በምንያታዊነት የሚመራ ትውልድ የሚቀረፀው፣ በመግባባት ላይ የተመሠረተ መቀራረብ ሲኖር ነው፡፡ ይህ መቀራረብ ውጥረቶችን ከማርገብ በላይ ዘለቄታ ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ያመጣል፡፡ ዜጎች በቅንነት ለአገራቸው እንዲተጉ ያነሳሳል፡፡ ኢትዮጵያም የበለጠ ትደምቃለች፡፡

ከኢትዮጵያችን ረዥሙ የነፃነት ዘመን፣ ከሕዝቡ አንድ ላይ ለአገሩ ዘብ ከመቆምና መስተጋብር፣ ከኅብረ ብሔራዊነትና አሁን እያጋጠመ ካለው መልካም ዕድል መነሻነት አዲስ ታሪክ ለመሥራት መነሳት ይገባል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሕዝብ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ የኢትዮጵያ እውነተኛ የከፍታ ዘመን እንዲረጋገጥ፣ ሕዝባችን በሰላምና በነፃነት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ፣ የሐሳብ ልዩነቶች በነፃነት እየተደመጡ አገር የዴሞክራሲ ጮራ እንድትሆን፣ ከአሳፋሪውና ከአሸማቃቂው ድህነት ለመገላገል፣ ዜጎች ከስደት ይልቅ በአገራቸው በመረጡት ሥፍራ እየኖሩና እየሠሩ ሀብት እንዲያፈሩ፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ወለል ብሎ ተከፍቶ አማራጭ የሚሆኑ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲኖሩ፣ ከግላዊና ቡድናዊ ጥቅሞች ይልቅ የአገር ጥቅም የበላይ እንዲሆን፣ በሕግ የበላይነት ሥር ፍትሕ ለሁሉም በእኩልነት እንዲዳረስ፣ ከተስፋ መቁረጥ ይልቅ ብሩህ ተስፋ እንዲኖር፣ ወዘተ. አጽንኦት መስጠት ይገባል፡፡ በተለይ የአገሪቱ ልሂቃን ከአሰልቺውና ከኋላቀሩ የፖለቲካ ገመድ ጉተታ በመላቀቅ አገራቸውን ያስቀድሙ፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ የሚፈልጉ ዜጎች እንዲህ ማሰብ ሲጀምሩ ትደምቃለች፣ ታብባለች!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...

ዘምዘም ባንክ ለሴቶችና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ

ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን በማስተዋወቅ ቀዳሚ የሆነው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...