Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየድሬዳዋ አስተዳደር አዲስ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ ነው

የድሬዳዋ አስተዳደር አዲስ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ ነው

ቀን:

  • አዲሱ የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር መስመርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከተማዋን እያነቃቃ ነው

ለረዥም ዓመታት ዕድገቷ ተገቶ የቆየችው የድሬዳዋ ከተማ አዲስ የተዘረጋው የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመርና በመገንባት ላይ ያለው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሕይወት እየዘራባት በመሆኑ፣ አዲስ የከተማ ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ላይ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አብደላ አህመድ ሙሜድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተማዋ ለጂቡቲ ወደብ ባላት ቅርበት የባቡር መስመርና ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የሚገኝባት በመሆኑ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተብላ ተመርጣለች፡፡ አዲሱ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ወደ ሥራ መግባቱና በመገንባት ላይ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ አብደላ፣ በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ተጠናቆ ማምረት ሲጀምር ከፍተኛ የሰው ኃይል ሥራ ፍለጋ ወደ ከተማዋ የሚመጣ በመሆኑ ከተማዋ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባታል፡፡

በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ ከተማ ሕዝብ ብዛት 500,000 ሲሆን፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ በጥናት ተገምቷል፡፡ ‹‹የሕዝብ ብዛት እየጨመረ ሲመጣ የቤት፣ የውኃና ሌሎች መሠረታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል፡፡ ይህን ችግር ለመቋቋም ከተማዋን ማስፋት፣ መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶች መገንባትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማሟላት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አዲስ የከተማ ማስተር ፕላን ለማዘጋጀት ወስኗል፡፡ አስተዳደሩ የከተማ ፕላን ክለሳ ጽሕፈት ቤት እንዳቋቋመ አቶ አብደላ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ አቅራቢያ የደረቅ ወደብ ግንባታ በመካሄድ ላይ ሲሆን (ድሬዳዋን ከጂቡቲ የሚያገናኘው)፣ የድሬዳዋ-ደወሌ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡

የመጀመርያው የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ከተዘረጋ በኋላ የተቆረቆረችው የድሬዳዋ ከተማ የመጀመርያው የከተማ ማስተር ፕላን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው የተሠራላት፡፡ ሁለተኛው በ1986 ዓ.ም.፣ ሦስተኛው በ1998 ዓ.ም. ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ አሁን በመዘጋጀት ላይ ያለው አራተኛው ማስተር ፕላን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ልዩ የኢንዱስትሪ ዞን 165 ሔክታር ቦታ ላይ የተንጣለለ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አዲስ የሚገነባው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ 4,200 ሔክታር ላይ ሲሆን፣ የግንባታው የመጀመርያ ክፍል በቅርቡ ተጠናቆ እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ ኃይሉ ወደ ሥራ ሲገባ ለ60,000 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ፕላን ክለሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢንያም ገብረተንሳይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የከተማው አስተዳደር የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በማቋቋም በመጀመርያ ዙር በመደበው ስምንት ሚሊዮን ብር ጽሕፈት ቤቱ በመስከረም 2010 ዓ.ም. ሥራውን ጀምሯል፡፡ የፕላን ጥናትና ዝግጅቱ በአጠቃላይ ወደ 30 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚፈጅ ይገመታል፡፡

አቶ ቢንያም ለሪፖርተር እንደገለጹት የድሬዳዋ ከተማ ስፋት 94.5 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ በአዲሱ ማስተር ፕላን ወደ 214 ካሬ ኪሎ ሜትር ያድጋል፡፡ የከተማዋ ሕዝብ ብዛት በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ያድጋል ተብሎ መገመቱን የገለጹት አቶ ቢንያም፣ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር መሸከም የሚችሉ መሠረተ ልማት፣ መሠረታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማሟላት የግድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ማስተር ፕላን የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚካሄድበትን ቦታ፣ የንግድ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ማዕከላት፣ እንዲሁም የመንገድ ግንባታ የሚካሄድበትን ቦታዎች ለይቶ እንደሚያስቀምጥ ጠቁመዋል፡፡ በመንግሥት ለሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ለሪል ስቴት አልሚዎች ቦታ እንደሚዘጋጅ የገለጹት አቶ ቢንያም፣ የውኃ አቅርቦት መስመርና የፍሳሽ ማስወገጃ ንድፍ በማስተር ፕላኑ እንደሚካተት አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከዓለም ባንክ በተገኘ 600 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በማካሄድ ላይ ነው፡፡ የማስተር ፕላኑ ጥናት የሚያተኩረው በከተማዋ መሠረተ ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ኩነቶች በጥናቱ እንደሚካተቱ አቶ ቢንያም ተናግረዋል፡፡

በደርግ ዘመን በኮንትሮባንድ ንግድና በምድር ባቡር እንቅስቃሴ ትታወቅ የነበረችው የድሬዳዋ ከተማ የተከሰተውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ፣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ በወሰደው ጠንካራ ዕርምጃና የምድር ባቡር እንቅስቃሴ በመገታቱ ከተማዋ ለረዥም ዓመታት እንዳንቀላፋች፣ ነዋሪዎቿም ለስደት መዳረጋቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ይመሰክራሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በድሬዳዋ የተገነቡ የሲማንቶ ፋብሪካዎች፣ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመርና በመገንባት ላይ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ እስትንፋስ እየዘሩባት እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...