Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርወዲያም ምሥጋና ወዲህም መልካም ምኞት እንኳን ደስ ያለን!

ወዲያም ምሥጋና ወዲህም መልካም ምኞት እንኳን ደስ ያለን!

ቀን:

የዶ/ር ዓብይ አህመድ የኢትዮጵያ መሪ መሆን ለዓመታት (ለዘመናት) የኢትዮጵያ ትልቁ ብሔረሰብ ከፍተኛ የሆነ የሥልጣን ተካፋይ ሳይሆን ቀርቷል ሲባል የነበረው ሃሜት ካማስቀረቱም በላይ፣ ለ27 ዓመታት ያህል እጅግ የተበላሸውን ኢትዮጵያዊ አንድነት መልሶ በማምጣት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ባይ ነኝ፡፡ የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በትክክል የሚከበሩበት አገር ከመመሥረትም አንፃርና የፍትሕ ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራት፣ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ ፕሬስ የሚከበርባትና የሚደነቁባት አገር በሀቅ በመገንባት በኩል እንዲሁም ካኮረፉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የትጥቅ ትግልን ምርጫቸው ያደረጉትንም አካቶ፣ በውጭ አገሮች ያሉ ጠቅላላ ስለኢትዮጵያ ያገባናል ይመለከተናል የሚሉ ኢትዮጵያውያኖችንም ሁሉ በግልጽ በማነጋገር፤ ከኤርትራ ጋርም ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር በመደራደር ረገድ ለእነዚህና መሰል ቁልፍ የአገራችን ችግሮች መልስ የሚሰጡን መሪ ዕውን ዶ/ር ዓብይ አህመድ ይሆኑ ይሆን? ማን ያውቃል ፈጣሪ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያችንን እንዲታደጉ ከምዕራብ የአገራችን ክፍል ጅማ አጋሮ የተላኩልን መሪ ቢሆኑስ? አምላክ ይርዳን፡፡ ዶ/ር ዓብይ አህመድ ስማቸው ራሱ ትልቅ ትርጉም ያለው ይመስላል፡፡ ምናልባትም ሁለቱን የአገራችንን ትልልቅ ሃይማኖቶች የሚወክሉ መሆናቸው ይሆን? ብቻ ከየትኛውም ብሔረሰብ ይምጡ የምንም ዓይነት ሃይማኖት ተከታይ ይሁኑ ኢትዮጵያዊያኖችን በእኩልነት፣ በፍትሕ፣ በፍቅር፣ በአክብሮት እንዲያስተዳድሩን ፈጣሪ ይርዳቸው ነው የምንለው፡፡ ኢትዮጵያ አገሬ ለአፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ለነፃነታቸው በመሟሟት፣ በመዋጋት፣ አፍሪካውያኖችን በማሰባስብ ረገድ ያላትን ወርቃማ ስም በፖለቲካ በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ እንዲሁ ወርቃማ ስም እንዲኖራት፣ አርዓያም ትሆንልን ዘንድ ለዶ/ር ዓብይ አህመድ አደራ እንበላቸዋ፡፡

‹‹አንቺም በሃይማኖትሽ እኔም በሃይማኖቴ፣››

መኖር እንችላለን አይጠበንም ቤቴ፡፡ ያለው ያ ምትሃተኛው ቴዲ አፍሮ ኦሮሞም ይሁን ትግሬ፣ ጉራጌም ይሁን አማራ፣ ወላይታም ይሁን ሱማሌ፣ ጋምቤላም ማለቱ እኮ ነው፡፡ ሁላችንንም በእኩልነት በፍትሕ በዴሞክራሲ የሚመራን መሪ ካገኘን ኢትዮጵያችን ትበቃናለች፡፡ የኦሮሞም ሕዝብ ‹‹በቁመቱ ልክ ሥልጣን ይገባዋል›› የሚሉት ዶ/ር መረራም ዛሬ መልስ ሳያገኙ የሚቀሩ አይመስለኝምና ተመስገን ማለት ነው፡፡ ይኼው ጊዜው ደረሰና የአገራችን ፕሬዚዳንት፣ የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአገሪቱ አፈ ጉባዔ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወዘተ…እንዲያውም ‹‹ከቁመቱም በላይ›› ሥልጣንን በመገኘቱ እንኳን ደስ ያለን! መልካም የሥራ ጊዜ ለዶ/ር ዓብይ! የተዳፈነው ኢትዮጵያዊነት ይለምልም! አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ለአምስት ዓመታት ያህል መርተውን በሰላም ወደ ቤተ መንግሥት እንደገቡት ሁሉ፣ በሰላም ከቤተ መንግሥት መውጣታቸውም ትልቅ አርዓያነት ያለው የሠለጠነ መሪ ተግባር በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ እስካሁን ላገለገሉንም እናመሰግንዎታለን፡፡ መልካም እረፍት ይሁንልዎ እንላለን፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያ!

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከዓድዋ ድልድይ)

***

የሥራ ሰዓት ለሥራ!

አዲስ አበባ ውስጥ በመንግሥት፣ በግል፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረን በመሥራት የምንተዳደር የዕለት ገቢያችንን፣ የቤተሰቦቻችንን ጉሮሮ ወጪ የምንደጉም በርካታ ሰዎች አለን፡፡ ይኼ ማለትም ከግልና ቤተሰብ ኑሮ ማሸነፍ አልፎ የአገር፣ የከተማ፣ የድርጅት ዕድገት ላይም ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የሰዓት አጠቃቀማችን የሥራ መግቢያ፣ የሥራ መጀመርያ፣ የሥራ መጨረሻና ከሥራ መውጫ ሕግና ሥርዓቶች በየቦታው በየድርጅቱ በየመሥሪያ ቤታችን የተለያየ ቢሆንም፣ የተወሰነና ስንቀጠር ጀምሮ የተስማማንበት ደንብና ሥርዓት  በተለይ ሰዓት ማክበርን በተመለከት ይኖራል፡፡ ይኼንንም ልናከብር የውዴታ ግዴታ ግድ እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እንደ አየሩ ሁኔታ ሥራ መግቢያ፣ ሥራ መጀመርያና መጨረሻ እንዲሁም ከሥራ መውጫ ሰዓታችን እያየንና እየሸረሸርን ስንገባ ስንወጣ እንገኛለን፡፡ ይኼንን ለማለት ያስቻለኝን አጋጣሚዎች ምናልባት ልብ ካልተባለ ተብሎም እንደዋዛ ታልፎ ከሆነ ለመጠቆም ወድጄ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በግል ጉዳዮቼ ምክንያት የመንግሥት፣ የግል ድርጅትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጎብኝቻለሁ፡፡ በስታትስቲክ የተደገፈ ማስረጃ ባይኖረኝም በተለይ፤

  1. በመንግሥት መሥሪያ ቤት (በክልል ቢሮዎች ጽሕፈት ቤቶች) በተለየ መልኩ በፊርማ ምክንያት ብዙዎቹ 15 እስከ 30 ደቂቃ (በጥሩ ግምት) ሰዓት አይከበርም፡፡ ሥራ መጀመርያ (መግቢያ አይደለም) ሁለት ሰዓት ከሆነ በአብዛኛው 230 መግባት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እስከ 300 ሰዓት ድረስም ሥራ ላይ አይገኙም፡፡
  2. በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለምሳሌበኢትዮጵያ አየር መንገድበብቸኝነት ሊጠቀስ በሚችል ሁኔታ መግቢያ ሰዓት፣ ሥራ መጀመርያ፣ ሥራ ማጠናቀቂያና መውጫ ሰዓት በትክክል 95 በመቶ ይከበራል፡፡ የሥራ ሰዓት ለሥራ ብቻ ይውላል፡፡ ለሻይ ለወሬ ለምሳ ለመሳሰሉት በሚል የሚባክን ጊዜ የለም፡፡ ይኼ ለምን ሆነ የሚለውን ከድርጅቱ መረዳት፣ ምሳሌ መውሰድ፣ ትምህርት ማግኘት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ከኢትዮጵያ ውጭ ባለ የአስተሳሰብና የአሠራር መዋቅር የሚራመድ ድርጅት ነው ቢባል በተለይ በሥራ ሰዓት አጠቃቀም ላይ ማጋነን አይሆንም፡፡
  3. ከግል ድርጅቶች የግል ባንኮች 2 ሰዓት ገብቶ 11 ሰዓት መውጫ ይላል፡፡ ነገር ግን የፊርማ ሥርዓቱ ባህላዊ በመሆኑ የተነሳ ሥራ ሲገባ ጨርሶ እስኪወጣ ድረስ እንደው በትንሹ 30 ደቂቃ ከድርጅቱ የሥራ ሰዓት ይሰረቃል፡፡ ኢንሹራንስ ሌሎች ሌሎችም እንዲሁ ነው፡፡ ሦስተኛ ደረጃ የግል ድርጅቶች ስንመለከት የተለመደው ሰዓት ያለማክበር የሥራ ሰዓትን ለሥራ ያለማዋል፣ ሥራን በሰዓቱ ጠንቅቆ ለደንበኛ ያለማስከበር የድርጅቱን ድክመት (Weak Point) ወደ ደንበኛ ባለጉዳይ ማስተላለፍ የተለመደ ሆኖ ይገኛል፡፡ ምሳሌ በአፓርታማ ግንባታና ሽያጭ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ አንድ ድርጅት ጋር የግንባታ ውል ተዋውዬ የመጀመርያ ቅድመ ክፍያ ከፍያለሁ፡፡ ያም ሆኖ በየምክንያቱ ጉዳይ ለማስፈፀም እመላለሳለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታም ድርጅቱ ሠራተኞችን የሥራ ሰዓት አጠቃቀም ለመታዘብ ችዬ ነበር፡፡ የሥራ መጀመርያ ሰዓት 230 ነው፡፡ ነገር ግን እስከ 250 ድረስ ተሟልቶ ሥራ ላይ ያለመገኘት የተለመደ ይመስላል፡፡ እንደታዘብኩት ከሆነ አለቆች በጊዜ ይገባሉ፡፡ ሌሎች ከደንበኛው ጋር ቀጥተኛ ግኑኝነት ያላቸው ሠራተኞች ግን አርፍደው ከገቡም በኋላ ቀድሞ የተገኘ ደንበኛ (በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የከፈለ ደንበኛ) ጉዳዩ ተፈፅሞ በጊዜ የሚሸኝበት መንገድ የሚፈለገው መብቱን የሚያውቅና የሚጠይቅ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ሌላ ጊዜ ተመልሶ እንዲመጣ ሊነገረው የሚችልበት አጋጣሚ በጣም በርካታ ነው፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር ወቅታዊ ክፍያ በየወቅቱ CPO ይከፈላል፡፡ ዋናውንክፍያ ደረሰኝ ቢሮ ድረስ ወስዶ የመስጠት የደንበኛው ግዴታ ሲሆን፣ የከፈለበትን የሪል ስቴቱን ደረሰኝ (ወዲያው አይደርስም) በሌላ ጊዜ ተመልሶ መውሰድ ያለበት ያውም ከሌላ ቅርንጫፍ መሰብሰብ የደንበኛው ግዴታ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ከቦታ ቦታ መመላለስ በዚህ በኢንተርኔት ዘመን አፓርታማ ስንገዛ የማናስበውና ከሆነ በኋላ የሚያሰለች ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ በሰዓት ባለመግባታቸውና ቀልጣፋ አገልግሎት ባለማግኘት የራስን ጊዜ ማቃጠል ደግሞ ሌላ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው፡፡ ለመሆኑ ደንበኛውም እኮ በሥራ ሰዓት ሥራ ቦታ ላይ መገኘት ግዴታ እንዳለበትና በየምክንያቱ መመላለስደንበኛውንም የሥራ ሕይወት የሚያውክ መሆኑ መታወቅ አልነበረበትምን?
  4. መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች 90 በመቶ የሥራ ሰዓት ይከበራል፡፡ በሥራ ላይ የመገኘትና ሥራ የመፈፀም ልምድም ጎልቶ ይገኛል፡፡ ሌላው በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሰዓት መቆጣጠሪያ ማሽን አለ፡፡ ነገር ግን ማሽኙን ተከታትሎ ቁጥጥርና እርምጃ የማድረጉ ነገር የሌለ ስለሆነ ሰዓት የማክበሩ ነገር የተረሳ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በደንብ ሊጤን የሚገባው ነገር ሰዓት ተከብሮ ወደ ሥራ ገበታ ከተገባ በኋላ ሥራ ሳይጀመር የሚባክነውየሚጠፋው ሰዓት ጉዳይ ይሆናል፡፡

በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኛ ወደ ሥራ ሲገባ በሰዓት መቆጣጠሪ ማሽን ላይ ካርዱን ያስገባል፡፡ ወደ ሻይ ቤት ከሄደም ካርዱን ይመታል፤ ከሻይ ሰዓት በኋላም ካርዱን ይመታል፤ ከሥራ ሲወጣም ካርዱን ይመታል፤ ይኼን ዓይነት አሠራር የሰዓት መቆጣጠሪያ ማሽኑ ከሒሳብ ክፍል ጋር የተያያዘ ስለሆነ በሻይ ቤት ረጅም ጊዜ እንዳይጠፋ ለማድረግ ተብሎ ይመስለኛል፡፡

በሌሎች መሥሪያ ቤቶች ደግሞ አለቆችና የክፍል ኃላፊዎች በጊዜ ገብተው በር ላይ በመቆም ሠራተኞች በጊዜ እንዲገቡ ለማበረታታትና ይሉኝታ ለማስያዝ ሲሞከርም አይቻለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ የሥራ ሰዓትን በተገቢው ሥራ ላይ እንዲውል የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በውጭ አገር ኖረው የተመለሱ ሰዎች ሥራ በሥርዓት የሚሠራው ውጭ አገር አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኤሽያና የመሳሰሉት አገሮች ነው ይሉናል፤ እውነትም ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ወይም የተማረ ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ተቀጥሮ ሰዓት ሳያከብር ኖሮ ወደ ውጭ አገር ሲሄድ ሰዓት አክባሪና ትጉህ ሠራተኛ ይሆናል፡፡ ለምን?

ለምን የሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያው ውስጥ የሞላ፣ የደላና የተትረፈረፈ ሥራ ሠርቶ መኖር የሚቻልበት ሆኖ አይደለም፡፡ እውነታው የምንሠራበት ድርጅት (ቀጣሪ) ለሚከፍለን ደመወዝ የሚመጥን ሥራ እንድንሠራ የሚያስገድድ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ነው፡፡ ሥራ ካልተሠራ ሳንቲም የማይገኝ መሆኑን፣ ለእያንዳንዷ ክፍያ የሚጠበቅ ሥራ መኖሩ ቢለመድና ቢያስገድድ ይኼ ሁሉ መዝረክረክ ባልኖረ ነበር፡፡ ኧረ ለመሆኑ አንዳንድ ጊዜ እኮ ህሊና ከአለቃና ከአሠሪ በላይመውቀስ እረፍት ማሳጣት ነበረበት፡፡

ሠራተኛው ዓላማውን እንዳይስትና የመጣበትን ጉዳይ ውጤት እንዲያስመዘግብ፣ የድርጅቱን ሰዓት በአግባቡ እንዲያውል ዝንፍ የማያደርግ የሥራ ባህልን የሚስያከብር ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይላል፡፡ ሥርዓት መዘርጋት ሲጀምር ሥራ በሰዓት መግባትና መውጣት፣ውጤታማነት ባህል ይሆናል፡፡

(ታዛቢ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...