በዘለዓለም እሸቴ (ዶ/ር)
ሁላችንም ካለንበት አጣብቂኝ ውስጥ መውጫ መንገድ አጥተን፣ ተፋጠን ሰንብተናል። ስንነካከስ እንዳንጠፋፋ በሚያስፈራ ሁኔታ ሁላችንም ግብ ግብ ስንገጥም እዚህ ደረስን። መንግሥት በጉልበቱ ሲገፋበት፣ ሕዝብ በአመፁ ሲዘልቅበት፣ አማራጭ ኃይል በሁሉ አቀፍ ትግሉ ሲዘምትበት፣ አካሄዱ ሁሉ ሲያስፈራ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ያሰኝ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ በሁሉም አቅጣጫ ወደ አምላኩ ከመጮህ አልተቆጠበም። በአራቱም አቅጣጫ አንድነቷንና ብልፅግናዋን በማይወዱ የተከበበች አገር ሆና ሳለ፣ ከውስጥ ደግሞ በነውጥ ስትናጥ ተስፋዋ እየመነመነ ጫፍ ደርሶ ነበር።
ምናልባት ታዲያ የማታ ማታ ፈጣሪዋ ኢትዮጵያን ከምጥ ሊገላግላት፣ ውጥረቷን አርግቦ ሰላምን ሊሰጣት አስቦ ይሆን ዶ/ር ዓብይ እርስዎን ወደ አመራር ያመጣዎት? ካለንበት አጣብቂኝ ለመውጣት ረዥም መንገድ መሄድ እንዳለብን ዕሙን ነው። ዶ/ር ዓብይ ለኢትዮጵያ ዘብ በመቆምና እኛም ለእርሳቸው ዘብ በመቆም ይህን የተስፋ ጭላንጭል ጠላት እንዳያጨናግፍ ሁላችንም የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባናል። አሁን ከፊታችን የተደቀነው ወሳኝ ሰዓት እኛ ተመልካች ሆነን፣ ዶ/ር ዓብይ ደግሞ በፊታቸው ያለውን ፈተና ያልፉ እንደሆነ ለማየትና ብያኔ ለመስጠት በጥርጣሬ ዓይን የምንመለከታቸው አይደለም። ወይም እኛ ሁላችን እሳቸውን የምናዋክብበት ጊዜ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛም ሆንን እሳቸው የመፍትሔው አካል ከመሆን እንዳንጎድል የምንጠነቀቅበት ጊዜ ከምንጊዜውም በላይ አሁን ነው።
በአንደኛ ደረጃ ሕዝብ ካንዣበበት አደጋ አምልጦ በሰላምና በመረጋጋት እንዲኖር ዶ/ር ዓብይ ራስዎን ከአጣብቂኝ መውጫ አድርገው ለሕዝብ የተሰጡ ይሆኑ ዘንድ፣ የተሰጠዎትን የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ አነሳስቶዎት ለኢትዮጵያ ዘብ ይቆማሉ ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ያደርጉ የነበረውን ንግግርዎትንና ሰብዕናዎን፣ አምላክ ወደ ብርሃን አውጥቶ በሕዝቡ ልብ ውስጥ እርስዎን አስቀምጧል። ሕዝቡ ትልቅ ተስፋም እንዲኖረው አድርጓል። እርስዎ ታማኝነትዎን ለመንግሥት ዕድሜ ቅጠላ ሳይሆን፣ ሰሚ ላጣው ሕዝብ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። ለጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣንም ያበቃዎት በቀዳሚነት የሕዝብ ትግል ነውና። በመንግሥት ዘንድ የሕዝብ ጆሮና ዓይን በመሆን የሕዝብ ጠበቃ እንዲሆኑና የሚመሩትን መንግሥት ወደ አዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅነት እንዲያሻግሩ፣ ታሪካዊ ጥሪዎን ይወጡ ዘንድ ተልዕኮዎን ለአንዲትም ደቂቃ መዘንጋት የለብዎትም። ይህንንም ኃላፊነትዎን እንዲወጡ ፋታ ባገኘሁ ይሉ ይሆናል።
ግን ፋታ የሚያገኙት እርስዎ ራስዎ በሚያደርጉት ተግባር ነው። በማስተዋል በመመላለስ ሁለት ነገሮችን ቢያደርጉ ፋታ የሚያገኙ ይመስለኛል። በመጀመርያ የሕዝብን ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መንቀሳቀስን ቸል የማይሉት ነገር ሆኖ ሲገኝ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የምንሄድበትን አዲስ አቅጣጫና ራዕይ እየነገሩንና አድራሻችንን እያሳዩን፣ አንድ ልብ ኖሮን እንደ አንድ ቤተሰብ የምንሄድበትን አካሄድ ለማስጨበጥ የሚተጉ ሆነው ሲገኙ ነው። አባቶች ደማቸውን አፍሰው በመሰዋት ኢትዮጵያን አቆይተው ዛሬ ለዚህች እናት ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ታድለዋል። በተራዎ እርስዎ ራስዎ ለኢትዮጵያ በመኖር፣ ኢትዮጵያን ለሁሉም በእኩልነት የመኖሪያና የማረፊያ አገር እንድትሆን የበኩልዎን ታሪካዊ ድርሻ መወጣት ይጠበቅብዎታል። ሁሉም መልካም ምኞቱንና በጎ ፈቃዱን እንደለገሰዎት በማወቅ ለተሰጠዎት ለዚህ ታላቅ ፀጋ ታማኝ እንዲሆኑ ማስተዋል ይብዛልዎት። በሁሉ ነገር መልካም እንዲሆንልዎት የመላው ኢትዮጵያዊ ፀሎትና ሰላማዊ ትግል እንደማየለይዎት ፅኑ እምነቴ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ኢሕአዴግ ራሱን ለማትረፍ ከዶ/ር ዓብይ የበለጠ መውጫ አያገኝምና ለእሳቸው ዘብ በመቆም ህልውናውን በሀቅ ምርጫ ለማስቀጠል፣ ራሱን ካለው የጊዜው የሕዝብ ጥያቄ ጋር ማጣጣም ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅንነት አገልጋይ ለሆነ ሁሉ የሃይማኖት፣ የጎሳና የፖለቲካ ፓርቲ አባልነቱ ማንነት ውሳኔውን ሳያዛባ በአስተሳሰቡ ምንነት ላይ ብቻ ተደግፎ ፍቅሩን እንደሚለግስ በዶ/ር ዓብይ ምርጫ ምክንያት የታየው ደስታ ያረጋግጣል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብን ቅንነትና ታላቅ ሰብዕና ያሳያል።
እስካሁን መንግሥት የሄደበት አካሄድ ሥልጣንን በጉልበት እንጂ በእውነተኛ ምርጫ አላገኝም ብሎ ያመነ ይመስል ከዴሞክራሲ የተፋታ ነበር። ታዲያ ዛሬ በእነ ክቡር አቶ ለማና ክቡር አቶ ገዱ ሕዝብን የማዳመጥና የማገልገል አስተሳሰብ ራሱን አጥምቆ ቢንቀሳቀስ፣ በእውነተኛ ምርጫ ለሥልጣን የመታደል ዕድል ሊያገኝ እንደሚችል ጭላንጭል እየታየ ነው። የትኛውም በጦር የመጣ መንግሥት እኔ እስከማውቀው ድረስ እንዲህ ያለ የመሸጋገሪያ ድልድይ ከራሱ አብራክ በወጣ ልጅ ዕድል ሲያገኝ አላየሁም፣ ደግሞም አልሰማሁም። በጎም ሆነ ክፉ እያደረገ ለ27 ዓመታት እንደፈለገው ገዝቶ ሲያበቃ፣ እንደ ገና በዴሞክራሲ በመዳኘት በምርጫ ሥልጣኑን ቢያጣ እንኳን እንደ ኢሕአዴግ ህልውናውን ከመጥፋት አስመልጦ ማስቀጠል የሚችልበትን ዕድል አግኝቷል። ታዲያ ለዚህ ምክንያት የሆኑት ዶ/ር ዓብይን በሙሉ ሥልጣን የመምራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት በመረባረብ፣ የውስጥ እንቅፋት የሚሆነውን ሁሉ በማሳመን ሕዝብን ማክበር ይኖርባቸዋል።
በሦስተኛ ደረጃ ተቃዋሚው ኃይል ለኢትዮጵያ አማራጭ ኃይል ለመሆን ዶ/ር ዓብይ ሁነኛ መውጫ ሊሆኑ ብቃት ያላቸው ይመስላሉና ለእሳቸው ዘብ በመቆም፣ ለሰላማዊ ትግል ኃይሉን አጠናክሮና አቀናጅቶ መቅረብ ይኖርበታል። ተቃዋሚው እውነተኛ ምርጫ እንዲዳኘው የሚያስችል የዴሞክራሲ ምኅዳር ቢኖርለት የአመፅ ናፍቆት የለውም። የዴሞክራሲው ምኅዳር እንዲሰፋና እንዲንሰራፋ መድረኩ ክፍት ከሆነ፣ በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች አማራጭ ኃይል ለመሆንም ሆነ ለመተባበር ዕድል ፈንታ ይሰጣቸዋል።
ለዚህም ነው ተቃዋሚ ኃይሎች ዶ/ር ዓብይን ለዴሞክራሲ ጉዞ ከአጣብቂኝ መውጫ ይሆኑ ዘንድ ደጀን በመሆን እውነት ራሷ ይህንን የዴሞክራሲ አካሄድ የሚቃወሙትን እንድትሞግትና እንድትረታ፣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይበልጥ መቀናጀት የሚያስፈልጋቸው። ለማንኛውም የዛሬ ሁለት ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ ከቁጥር በማስገባት እስከዚያው ድረስ ዶ/ር ዓብይ ለምርጫው ፍትሐዊነት ሁሉን እያሳተፉ የለውጥ ዋዜማ ሽታ እስካመጡ ድረስ፣ በትዕግሥትና በመረዳዳት ፋታ መስጠት የግድ ነው።
አሁን ዶ/ር ዓብይን በተመለከተ በሁሉም አማራጭ ኃይሎች ዘንድ የሚታየው በጎ ፈቃድና የእምነት ተስፋ እጅግ የሚያበረታታቸው ይመስለኛል። ይህም መልሶ ለሕዝብ እንዲኖሩ ግፊት እያደረገ የሕዝብ እውነተኛ አገልጋይ እንዲሆኑ ጉልበት ይሆናቸዋል።
ላለፉት 44 ዓመታት በወጀብ ስትናወጥ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ደግሞ በአዲስ መንፈስ መሪዋና ሕዝቡ በፍቅር እጅና ጓንት ሆነው አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትወለድ አገራችንም ለመጀመርያ ጊዜ ዕፎይ የምትልበት ዘመን ይህ ጊዜ ይሁንልን። ይህ መለኮታዊ ዕድል አያምልጠን። ልባችን ለዚህ ውልደት ዘብ ለመቆም ይጨክን! የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን አሰበ። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡