Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቴክኖ ሞባይል በናይጄሪያ አዳዲስ ምርቶቹን ለዓለም ገበያ ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ በኢትዮጵያም አዲሱ ምርት ለገበያ ይቀርባል

በትራንሽን ሆልዲንግስ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥር የሚተዳደረው ቴክኖ ሞባይል፣ በናይጄሪያዋ የባህር ጠረፍ ከተማ ሌጎስ አዳዲስ ምርቶቹን ይፋ በማድረግ በስማርት ስልኮች ብራንድ የደረሰበትን ደረጃ ለአፍሪካ ደንበኞቹ አሳይቷል፡፡

በአፍሪካ ካለው ገበያ እስከ 70 በመቶ የሚደርሰውን ከፍተኛውን ድርሻ በምትይዘው ናይጄሪያ ‹‹ቴክኖ 2018 ግሎባል ስፕሪንግ ላውንች›› በሚል ርዕስ በተካሄደው የአዳዲስ ምርቶች ማስተዋወቂያ መድረክ፣ ‹‹ካሞን ኤክስ›› እንዲሁም ‹‹ካሞን ኤክስ ፕሮ›› የተሰኙትን ሁለት ምርቶች በርካታ ማሻሻያዎችና ቴክኖሎጂዎች አካቶ እንዳመረተና ለገበያ እንዳቀረበ አስታውቋል፡፡

ዳዲሶቹ ካሞን ኤክስና ካሞን ኤክስ ፕሮ ስልኮች፣ በመሠረታዊነት ካስተዋወቋቸው ለውጦች ውስጥ ከዚህ ቀደም በተለቀቁት ስልኮች ላይ የነበረውን የ16 ሜጋ ፒክስል የምስል ጥራት ወደ 24 ሜጋ ፒክስል ማሳደጋቸው ትልቁ ነው። በዳታ ሜሞሪ አቅም 64 ጌጋ ባይት፣ በፕሮሰሰር በኩል 4 ጌጋ ባይት ፍጥነት ያላቸው ሲሆኑ፣ ስልኮቹን ከስርቆትና በሌሎች ሰዎች በቀላሉ እንዳይሰረቁ ወይም መረጃ እንዳይወሰድ ለማድረግ ከጣት አሻራና ከሌሎች የተለመዱ የይለፍ ቁልፍ ሥርዓቶች ይልቅ የስልኮቹ ባለቤቶች ምስልን በመለየት መክፈት የሚቻልበትን የትግበራ ቴክኖሎጂ ማካተታቸው ታውቋል። ስልኮቹ ይፋ በተደረጉበት ወቅት ለጋዜጠኞች  እንደተብራራው፣ ይህንን ቴክኖሎጂ ዕውን ለማድረግ የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን ፊት ማጥናትና በፊት ላይ የሚገኙ የተለያዩ ገጽታዎችን ማካተት ያስፈልግ ነበር። ስልኮቹ ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ለኢትዮጵያ ገበያ ይቀርባሉ ተብሏል። 

ቴክኖ ሞባይል፣ ‹‹ካሞን ኤክስ››፣ የእንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ የሚተዋወቅበት ‹‹ካሞን ሲኤክስ›› ስማርት ስልክ፣ ‹‹ፓንቶም 8››፣ ‹‹ፓንቶም 6 ፕላስ››፣ ‹‹ስፓርክ››፣ እንዲሁም ‹‹ስፓርክ ፕላስ›› የተሰኙትን ሞዴሎች ጨምሮ በየጊዜው እያሻሻለና በአዲስ መልክ በቴክኖሎጂ እያራቀቀ ከሚያወጣቸው ስልኮች ውስጥ ‹‹ካሞን ኤክስ›› የዚህ ዓመት የፀደይ ወራት አዲስ ምርቱ ሆኖ ለመላው ዓለም ቀርቧል፡፡

በአፍሪካ ለገበያ ከሚቀርቡ አሥር ስልኮች ውስጥ ሦስቱ የትራንሽን ወይም የቴክኖ ሞባይል ሥሪቶች ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ምንም እንኳ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ እንደሌሎቹ ታዋቂ ብራንዶች ያለ የገበያ ድርሻ ዝቅተኛ ሆንም በአፍሪካ በጠቅላላው የ30 በመቶ የሽያጭ ድርሻ በመያዝ ነ ሳምሰንግን ያስከትላል፡፡ የሳምሰንግ የአፍሪካ ገበያ ሽያጭ መጠን 22 በመቶ ስለመሆኑም የገበያ አጥኚዎችን ዋቢ በማድረግ በቅርቡ ብሉምበርግ ያስነበበው ጽሑፍ ይጠቁማል፡፡ የአፕል ኩባንያ ምርቶች በአፍሪካ ካላቸው የ12.3 ሚሊዮን ሽያጭ አኳያ እንዲሁም በ60.5 ሚሊዮን ስልኮች ሽያጭ ሳምሰንግን በቅደም ተከተል የሚያስቀምጡት መረጃዎች፣ የቴክኖ ሞባይል ስልኮች አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆነው ትራንሽን ግን ቀዳሚነት ይመድቡታል። ኩንባንያው የመካከለኛው ምሥራቅ ገበያውን ጨምሮ ከ90 ሚሊዮን በላይ ስልኮችን በመሸጥ በአፍሪካም ከፍተኛውን የሽያጭ መጠን በማስመዝገብ  ዳሚው የሽያጭ ባለድርሻ ሆኗል፡፡

በአዲስ አበባ በ280 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነባው ፋብሪካው በየወሩ ሁለት ሚሊዮን የተለያዩ ሞዴል ያላቸውን የሞባይል ስልኮች በመገጣጠም ለገበያ የማቅረብ አቅም አለው፡፡ በዓለም ከ240 ሚሊዮን በላይ የተለያየ ሞዴል ያላቸውን ስማርትና መደበኛ የስልክ ቀፎዎችን እንዲሁም ታብሌቶችን በማምረትና በመሸጥ የሚታወቀው ቴክኖ ሞባይል፣ እ... 2017 ብቻ ከ120 ሚሊዮን በላይ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ መሸጡን አስታውቋል፡፡

... 2018 ሥራ የሚያስጀምረው ፋብሪካ በዓመት የ300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ኩባንያው አስታውቋል፡፡ በቻይና ሼንዜን ከተማ እ... 2006 የተመሠረተውና በ2007 ማምረት የጀመረው  ቴክኖ ሞባይል፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያን በማስቀደም ሁለት ፋብሪካዎችን በመክፈትና የሞባይል ስልኮችን በመገጣጠም ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

በወር፣ በአንድ ፈረቃ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስልኮችን የመገጣጠም አቅም ባላቸው፣ በጎፋ አካባቢና በዓለምገና ከተማ በገነባቸው ሁለት ፋብሪካዎች አማካይነት ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ የኩባንያው ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተጠናቀቀው የ2009 .. 60 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘቱንም አስታውቀዋል፡፡ በዓለምገና እንዲሁም በጎፋ ካምፕ አካባቢ የተገነቡት ሁለቱ ፋብሪካዎች ከ2,000 በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።

ቴክኖ ሞባይል እስካሁን በኢትዮጵያ ከነበረው እንቅስቃሴ ይበልጥ በመስፋፋት በቦሌ ለሚ በሚገኘው የኢትዮ አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ትልቅ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፋብሪካ በወር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ስልኮችን ለገበያ ማውጣት እንደሚችል ኩባንያው ይገልጻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለ4,000 ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል የተባለው አዲሱ ፋብሪካ፣ ወደ ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሌሎችም አገሮች ሲደረግ የቆየውን የ60 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር በማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።

በኢትዮ አይሲቲ መንደር የሚገነባው የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ፣ በቻይና ከሚገኘው ፋብሪካ አኳያ ግዙፉ እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ የቻይናው የማምረት አቅሙ ሦስት ሚሊዮን ስልኮችን እንደሚያመርት የኩባንያው መረጃ ያሳያል፡፡ በጎፋ ካምፕ አካባቢ የተገነባው የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ ከሰባት ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በወር 425 ሺሕ ስልኮችን ገጣጥሞ የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የተገነባው የዓለምገናው ፋብሪካ በበኩሉ በወር 580 ሺሕ ስልኮችን የማምረት አቅም እንዳለው ይታወቃል

ይሁንና ተደጋጋሚ በሚገጥመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ በአቅሙ ልክ ማምረትም ሆነ ወደ ሌሎች አገሮች እንደልብ መላክ አልቻለም። ቴክኖ ሞባይል የሽያጭና ግብይት ዳይሬክተር ፊሊክስ ሜንግ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው ፈተናዎቹን አልፎ በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚጀምርበትና ሌሎች አገሮችንም የሚያዳርስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

በኢትዮጵያ ከመገጣጠም ባሻገር በድኅረ ሽያጭ የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ መደብሮችን የሚያንቀሳቅሰው ቴክኖ ሞባይል፣ በተለይ የሽያጭ መደብሮችን ከነጋዴዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት መሠረት በሚሰጣቸው የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ አማካይት ለመደብሮች ምርቶቹን ያቀርባል፡፡

በኢትዮጵያ እስካሁን የተከፈቱት ሽያጭ መደብሮች በፍራንቻይዝ መልክ የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ፣ በአራት ደረጃዎች እንደሚመደቡ የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስታንዳርድ፣ ስታንዳርድ ኤክስክሉሲቭ፣ ሜጋ ኤክስክሉሲቭ እንዲሁም ፍላግሺፕ የሚባሉ ደረጃዎች ያሏቸውን መደብሮች ለመክፈት የሚስማሙ ነጋዴዎችን ሲያገኝ የምርት ዓይነቶቹም እንደ መደብሮቹ ደረጃና አቅም የተለያየ መጠን ቀርባል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች