Monday, December 4, 2023

የኢትዮጵያና የኤርትራ የወደፊት ተስፋና የወቅቱ ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ ባደረጉት ንግግር ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታትን ግንኙነት የተመለከተ ነበር፡፡ የ42 ዓመት ዕድሜ ያላቸውና ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው የሚጠሩት ዶ/ር ዓብይ፣ መንግሥታቸው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለውን የፖለቲካ ልዩነት በውይይትና በድርድር ለመፍታት ዝግጁ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ በተመሳሳይም የኤርትራ መንግሥት ተመሳሳይ አቋም እንዲይዝ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ይህ ጥሪ በተላለፈ በሰዓታት ልዩነት የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ አገራቸው ኢትዮጵያ በኃይል የያዘችውን የባድመ ግዛት ካልለቀቀች ውይይትና ድርድር ለማድረግ ዝግጁ አይደለችም ብለዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ልትደራደርና ልትወያይ የምትችለው ኢትዮጵያ የያዘችውን የባድመ ግዛት ስትለቅ ብቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኤርትራን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር የበርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ቀልብ ስበዋል፡፡

ይህን ጉዳይ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ሰጥተው ሲዘግቡትና በርካታ ምሁራን ሲወያዩበት ሰንብተዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ እንደተናገሩት፣ አስመራ ድረስ ሄደው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመነጋገር ዕቅድ ነበራቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለስድስት ዓመታት ቢቆዩም፣ ወደ አሥመራ ሄደው ያቀዱትን ሳያሳኩ ቀርተዋል፡፡ ከኤርትራ መንግሥት ጋር የነበረውን የመጠቃቃትና የመወነጃጀል አባዜ ለማስቀረት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበት የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን ለማስተካከልም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ይህን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታትም ኢትዮጵያ አዲስ ፖሊሲ ልታወጣ ማቀዷን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጹ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን በውይይት ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቢስተዋልም፣ በኤርትራ በኩል በጎ ምላሽ አልነበረም፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በሶማሊያ ውስጥ የመሸገውን አልሸባብ ተብሎ የሚጠራውን ቡድን ኤርትራ ትደግፋለች በማለት ኢትዮጵያ ትወነጅላለች፡፡ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በተደጋጋሚ ጊዜ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ስታስታውቅ ቆይታለች፡፡ ተመድም እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ በኤርትራ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀብ እንደጣለባት ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባላት የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ ለኢትዮጵያ በተለያየ መንገድ ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉ አገሮችን ወዳጅ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በተለይም ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ በቀይ ባህር በኩል፣ በዋናነት ደግሞ በአሰብ ወደብ ላይ የጦር ቀጣና እንዲኖራቸው መፍቀዷን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ በህዳሴ ግድቡ ጉዳይ አንዴ ወዳጅ አንዴ ደግሞ እርስ በርሳቸው ሲጠራጠሩ ታይተዋል፡፡ ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ በቀይ ባህር አካባቢ አስተማማኝ ወታደራዊ የጦር ሠፈር እንዲኖራቸውና ቀጣናው ካለው ፖለቲካዊ ፋይዳ አኳያ በተለያዩ ጊዜያት ወደ አካባቢው ሲሳቡና ሲያማትሩ ተስተውሏል፡፡ ለዚህ ውጥናቸው ማስፈጸሚያ ደግሞ ኤርትራን እንደ ዋነኛ መሸጋገሪያ ድልድይ አድርገው ሲጠቀሙ ታይቷል፡፡

ግብፅ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ሰላም የሰጣት አትመስልም፡፡ ከወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት በፊት የነበሩት መሪዎች ግድቡን በኃይል እናፈርሳለን የሚል መልዕክት ሲያስተላልፉ ነበር፡፡ የዚህ ዛቻና ማስፈራሪያ ዋነኛ መሠረቱና ግብፅ የልብ ልብ የሰጣት ደግሞ ከኤርትራ ጋር ያላት የጥቅም ግንኙነት ሳቢያ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ እርስ በርሳቸው እየተወነጃጀሉና እንደ ጠላት እየተያዩ መኖር ከጀመሩ ሁለት አሠርት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ የፖለቲካ ልዩነታቸውን አስወግደው በመልካም ጉርብትና እንዲኖሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ቢታወስም፣ እስካሁን ፍሬ አላፈሩም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ችግሩ በመነጋገር እንዲፈታና የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ግንኙነት ወደ ቀድሞው ለመመለስ ጥረት ስታደርግ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአንድ ወቅት ለአገራቸው ሚዲያ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ችግሩ በመነጋገር እንዲፈታ ከ70 ጊዜ በላይ ለኤርትራ ጥያቄ አቅርባለች፡፡ ይህ ሁሉ ለኤርትራ መንግሥት ሲቀርብ ግን ኤርትራ ባድመ ካልተመለሰልኝ አልደራደርም የማል ምላሽ መስጠቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የሁለቱን አገሮች የፖለቲካ ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል ፅኑ አቋም አለ፡፡ በኤርትራ በኩልም ይህ አቋም ከዚህ ቀደም እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ያለውን አቋም ግን በውል እንደማያውቁ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አሁንም ቁርጠኝነት ነው እንጂ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ግንኙነት ተቋርጦ እንደማይቀርና አሁን በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት የተጀመሩ ሥራዎች ዕውን እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያደረጉት ንግግር ለሁለቱ አገሮች ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል፡፡ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የአሁኑ ጥሪ በአዲሱ ትውልድ የተደረገ ጥሪ ነው፤› ብለዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥሪዎች ከዚህ በፊትም ሲተላለፉ እንደነበር አስታውሰው፣ የአሁኑን ጥሪ ልዩ የሚያደርገው በአዲሱ ትውልድ የተደረገ በመሆኑ ነው ሲሉ  አስረድተዋል፡፡

ሥልጣን ላይ ያለው የኤርትራ መንግሥት ለረዥም ዓመታት በሥልጣን ላይ እንዲቆይ የሆነበት ምክንያት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ጠላታችን ነች፣ መሬታችንን በኃይል ወራለች፤›› በማለት ለሕዝቡ በመለፈፍ እንደሆነ አቶ ልዑልሰገድ ጠቁመው፣ የኤርትራ መንግሥት የአሁኑን ጥሪ በቀላሉ ይቀበላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ለውጥ ሊመጣና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመደራደር የሚቻለው ኤርትራ በአዲስ ትውልድ መመራት ከጀመረች ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ የሕዝቡ የሥልጣን ባለቤትነቱን ካረጋገጠና አሁን ያለውን መንግሥት ሥልጣን እንዲለቅ ካደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለዚህ ሁሉ ችግር ያበቁን የ1960ዎቹ መሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የትውልድ ለውጥ ካልመጣ በስተቀር በቀላሉ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት የለኝም፤›› ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳደ ደስታ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለውን የፖለቲካ ልዩነት በውይይት ለመፍታት ጥሪ ማድረጋቸውን አድንቀው፣ ‹‹ጥሪው አዲስና እንግዳ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ማለትም አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተመሳሳይ ጥሪ አድርገው እንደበር አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ቸል የሚባል ባለመሆኑ ሳቢያ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ትኩረት ሰጥተው ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ ማድረጋቸው የሚያስመሠግናቸው ነው ብለዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት የእንነጋገር ጥያቄ ቢቀርብለትም ጥሪውን ተቀብሎ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው አቶ ዳደ ጠቁመዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት ተገማች ባለመሆኑና ፕሬዚዳንቱ ነገ ሌላ ውሳኔ ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ላቀረቡት ጥሪ የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ባድመና ሌሎች ግዛቶች ለኤርትራ ካልተሰጡ መነጋገር አንችልም ያሉ ቢሆንም፣ ኢሳያስ ራሳቸው ካልተናገሩ በስተቀር የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገ ፕሬዚዳንቱ በቴሌቪዥን ወጥተው የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩን ምላሽ ጥለው ሌላ ውሳኔ ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ራሳቸው ሰውየው ካልተናገሩ በቀር ማመኑ ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ የሚሆነው ደግሞ የአሁኑ የኤርትራ መንግሥት ተገማች ባለመሆኑ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ፕሬዚዳንቱ ጥሪውን ይቀበላሉ ማለት እንደዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዳደ በሁለቱ አገሮች የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ በደም የተሳሰሩ ሕዝቦች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕዝቦች እየከፈሉት ያለው ዋጋ ትልቅ ነው፡፡ ችግሩ ከዚህ በላይ መቀጠል የለበትም፤›› ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም የኢትዮጵያ መንግሥት በጀመረው ጥረት የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን አስቀምጦ መንቀሳቀስ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካይነት ችግሩን ለመፍታት ጥሪ አቅርባለች፡፡ በኤርትራ በኩል ደግሞ አሁንም ከሕዝቦች መከፋፈል ይልቅ የባድመ ግዛት ያሳሰባት ትመስላለች ሲሉ የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ በየወሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች አገሮች እንደሚሰደዱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአሰብ ወደብ አሁንም ‘ከግመል መጠጫነት’ አልዘለለም ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፡፡ ሁለቱ ጎረቤት አገሮች ከጉርብትናቸው ባሻገር ዜጎቻቸው በደም ጭምር የተዋሀዱ በመሆናቸው፣ ተለያይተው ለመኖር በመገደዳቸው የባሰ ስቃይ ፈጥሮባቸዋል፡፡

ግማሽ ቤተሰብ አዲስ አበባ ግማሽ ደግሞ አሥመራ ውስጥ እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በአስመራ ከተማ ለ21 ዓመታት እንደኖሩ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ በአስመራም ሆነ በአዲስ አበባ ያሉት በደም የተሳሰሩ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአዲሱ ትውልድ አካል ናቸው የሚሉ ወገኖች፣ ከዚህ አኳያ የኤርትራ መንግሥት ለዚህ አዲስ ትውልድ በሰከነና በተረጋጋ መንገድ አገናዝቦ ምላሽ ይሰጣል ብለው ያስባሉ፡፡ ምንም እንኳ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ‘ባድመ ካልተመሰልን አንደራደርም’ የሚል ምላሽ ቢሰጡም፣ ጉዳዩ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በትዕግሥትና ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የኤርትራን መንግሥት በማግባባት ችግሩን መፍታት ይችላል ሲሉም ያክላሉ፡፡

ከእነዚህ መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል የሚማረው ጌቱ ተድላ አንዱ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው ሁለቱ አገሮች በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይችሉ፣ ከሕዝብ ፍላጎት አፈንግጠው አይዘልቁም፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ተነሳሽነቱ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጭምር በግልጽ እየተነገረ፣ የኤርትራ መንግሥት አፈነግጣለሁ ካለ የፖለቲካ ክስረት ነው፡፡ ‹‹ዝርዝር ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ሸምጋይነት እየታየ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ቀጥሎ ሰላም መስፈን አለበት፡፡ ሁለት ደሃ አገሮች ለሌላ ዙር ጦርነት የሚያዳርሳቸው ሀብትም ሆነ የሰው ሕይወት ሊኖር አይገባም፡፡ በዚህ ዘመን ጦረኝነት ላይ ችክ ማለት ኋላቀርነት ነው፤›› ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃ ከልብ እንፈልጋለን፡፡ የበኩላችንን እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሳሩት የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለን ዝግጁነትን እየገለጽኩ፣ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ጥሪ ተስፋ የሰነቀ ቢሆንም፣ ከኤርትራ በኩል ያለው ምላሽ ግን ፈተናውን እንዳያከብድ ሥጋት ያላቸው አሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -