በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የልዑካን ቡድን ቅዳሜ መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ድንበር አካባቢ ላይ ተከስቶ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ወደ ጅግጅግ አቅንቷል፡፡
የሶማሌ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ እድሪስ እስማይል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ ከልሉ አመራሮች ጋር ይወያያሉ፡፡
በሁለቱ ክልሎች የድንበር ግጭት ምክንያት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ከኦሮሚያ ክልል መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ በድንበር ግጭቱ ምክንያትም የበርካቶች ሕይወት አልፏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ጅግጅጋ ያደረጉት ጉዞ የመጀመሪያው ከቢሯቸው ውጪ ያደረጉት የሥራ እንቅስቃሴ ነው፡፡