Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሞሮኮ ግዙፍ ኩባንያ በተፈጠሩ በርካታ ችግሮች የተዘጉ አምስት የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ይረከባል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ከ250 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብተው በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን፣ የሞሮኮ ግዙፍ ኩባንያ ኦሲፒ በሊዝ ሊረከባቸው ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዳበሪያ በማቅረብ የሚታወቀውና በኢትዮጵያም በድሬዳዋ ከተማ በ3.7 ቢሊዮን ዶላር አዲስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ውል የገባው ኦሲፒ፣ አምስቱን ፋብሪካዎች በሊዝ ለመረከብ ረቡዕ ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ለመፈረም ቀጠሮ ይዟል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሞሮኮ ኩባንያ አምስቱ ፋብሪካዎች የገጠማቸውን ችግር ከፈታ በኋላ፣ ለአምስት ዓመታት በሊዝ አስተዳድሮ ለዩኒየኖቹ መልሶ ያስረክባል፡፡

ጊቤ ደዴሳ፣ መርከብ፣ እንደርታ፣ መልህቅና በቾ ወሊሶ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ከአካባቢው አርሶ አደሮች ነባራዊ ሁኔታ፣ አፈሩ ከሚፈለገው ንጥረ ነገር በመነሳት ምጥን ማዳበሪያ ለማምረት ፋብሪካ ገንብተው ነበር፡፡

ነገር ግን ለፋብሪካዎቹ ያስፈልጋሉ ተብለው የገቡት ‘ቦሮንና ፈርቲ ኮት’ የተባሉ የማዳበሪያ ዓይነቶች ለፋብሪካዎቹ ሁነኛ ንጥረ ነገር መሆን ባለመቻላቸው፣ ፋብሪካዎቹ በጅምሩ ሥራ እንዲያቆሙ አድርጓል፡፡

ለእነዚህ ማዳበሪያ ፋብሪካዎች 200 ሚሊዮን ብር የወጣ ሲሆን፣ ለፋብሪካዎቹ ግንባታ ደግሞ 250 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ይህ ኪሳራ እንዳለ ሆኖ ለዓመታት ማዳበሪያዎቹን የያዙ ትልልቅ መጋዘኖች ያለሥራ ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡

አቶ ተፈራ የሞሮኮ ኩባንያ ያለሥራ የተከማቹትን ማዳበሪያዎች ወደ ሥራ ማስገባት ከመቻሉም በላይ፣ በሥራው ላይ ላሉት ዩኒየኖች የዕውቀት ሽግግር ያደርጋል ብለዋል፡፡

የሞሮኮው ኩባንያ በድሬዳዋ ከተማ አዲስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ስምምነት ፈጽሟል፡፡ የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በርካታ ስምምነቶች መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ ስምምነቶች ውስጥ በድሬዳዋ ከተማ በ3.7 ቢሊዮን ዶላር በዓመት 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት ያካትታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች