Thursday, March 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አንገት ከመድፋት መውጣት የሚቻለው ሕዝብ ሲደመጥ ብቻ ነው!

መሰንበቻውን መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ከሕዝብ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት ነው፡፡ የጉብኝታቸውና የውይይታቸው ዓላማ በመስከረም 2010 ዓ.ም. በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ያደረሰው ጥፋት ነው፡፡ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የሞቱበት፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉበትና ከፍተኛ የአገር ሀብት የወደመበት ግጭት ከሁለቱም ወገኖች አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ከቀዬአቸው አፈናቅሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንደገለጹት፣ ግጭቱ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠና የሁሉንም ወገን አንገት ያስደፋ የሽንፈት ታሪክ ነው፡፡ ይህንን አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ በፍጥነት ዘግቶ በሁለቱ ሕዝቦች ይሁንታ ላይ  የተመሠረተ የጋራ መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል፡፡ ለዚያ አሳፋሪና አውዳሚ ግጭት መንስዔ የነበሩ ምክንያቶችና ቆስቋሾች ጥርት ብለው መታወቅ ይገባቸዋል፡፡ የኦሮሞና የሶማሌ ተወላጆች ለዘመናት ተሳስበውና ተደጋግፈው የሚኖሩ፣ ግጭቱ በተከሰተም ጊዜ እርስ በርስ ከለላ የተሰጣጡና የጥፋቱን መጠን የቀነሱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ያሸመቁ ሴረኞች ግን አሳፋሪውን ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ከእንደዚያ ዓይነቱ የውርደት ተግባር መላቀቅ ይገባል፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡

በማኅበረሰቦች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በውኃ፣ በግጦሽ መሬትና በመሳሰሉ ጉዳዮች ችግሮች ሲፈጠሩ የአገር ሽማግሌዎች በነባሩ ባህልና ልማድ መሠረት ሲፈቱ ይታወቃል፡፡ ይህንን የመሰለ የግጭት አፈታት ሥርዓት ባለበት አገር ውስጥ ፖለቲከኞች ጣልቃ እየገቡ ግን ብዙ ጊዜ ደም ፈሷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ ሕዝቡ ባህል ባደረገው የግጭት አፈታት ሥርዓት የበደለውን እየገሰፀ፣ የተበደለውን እንዲካስ እያደረገ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራዎች የሚገኙ ወገኖችም የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው ከመሆኑም በላይ፣ ተጋብተውና ተዋልደው አብረው የሚኖሩ መሆናቸውም የታወቀ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ሕዝቡ  ምንም ዓይነት ጠባሳም ሆነ ቁርሾ የለውም፡፡ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ተጠርቶ ውይይት ቢደረግ እርስ በርሱ እየተላቀሰ አብሮነቱን ያረጋግጣል፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋ ያለው ሕዝብ መሀል የሚረጨው መርዝ ነው መፍትሔ የሚያስፈልገው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱና ውይይቱ ሲጀመርም ይህ ጉዳይ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከሕዝብ የተሰወረ ምንም ነገር የለም፡፡

በታሪክ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያውያን መካከል ለግጭት የሚጋብዝ አጋጣሚ ተፈጥሮ አያውቀውም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ገዥዎች ምክንያት ግጭቶች እንዳጋጠሙ ይታወቃል፡፡ ይሁንና አንድ ሕዝብ በሌላው ላይ ተነስቶ የበላይ ለመሆንም ሆነ፣ በሌሎች ፍላጎቶች ምክንያት ይህ ነው የሚባል ግጭት አልተከሰተም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚታወቀው አገሩን ከተስፋፊዎችና ከወራሪዎች ሲጠብቅ ነው፡፡ በገዥዎች የተለያዩ በደሎች የደረሱበት ሕዝብ እርስ በርሱ እየተደጋገፈና እየተሳሰበ፣  ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር እዚህ ዘመን ደርሷል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አስጠብቆ ለዓለም ተምሳሌት የሆነ ሕዝብ፣ በብሔርም ሆነ በሃይማኖት ሊከፋፍሉት ያሰቡትን ሁሉ ሴራቸውን ሲያከሽፍ ኖሯል፡፡ ልዩነቶቹን ጌጥ አድርጎ አንድነቱን ኃይል ያደረገው ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ የሚያዳምጠው ቢያገኝ፣ ከፍተኛ አርዓያነት ያለው ትምህርት በውስጡ አምቆ ይዟል፡፡ አሁንም ከጠባብነትና ከትምክህተኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ይህንን ጨዋ ሕዝብ ማዳመጥ ከተቻለ አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ይህ ሕዝብ ከአኩሪ ባህሎች፣ ልማዶችና ወጎች በተጨማሪ አስገራሚ አገር በቀል ዕውቀት አለው፡፡

የአገሪቱ ፖለቲከኞች በእህልና በቂም በቀል ከተበከለ የጥላቻ ፖለቲካ ተላቀው ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ ሊጓዙ ይገባል፡፡ የአሻጥርና የሴራ ፖለቲካ ግቡ ሥልጣን ጨምድዶ ይዞ ሕዝብን ነፃነት ማሳጣት ነው፡፡ ለዕልቂትና ለውድመት መዳረግ ነው፡፡ የትናንቱን አሳፋሪ ውርደት ላለመድገም የሚቻለው ከተንኮልና ከአሻጥር መላቀቅ ሲቻል ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ የአጋሮቹ፣ እንዲሁም በተቃውሞ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች በቅጡ ማሰብ ያለባቸው ለአገር ነው፡፡ ከአገር በላይ ለሥልጣን ቅድሚያ መስጠት አደገኛ መሆኑ በሚገባ ታይቷል፡፡ ይህ አስተዋይ ሕዝብ ደግሞ ከአገሩ በላይ የሚያስቀድመው የለም፡፡ ባልበሰለ የፖለቲካ አመራርና በሥልጣን ጥመኝነት በመናወዝ የሚፈጸሙ ድርጊቶች የሚጎዱት አገርን ነው፡፡ የሕዝብንም ሕይወት ያመሰቃቅላሉ፡፡ ይህ ጨዋ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ያስፈልገዋል፡፡ በአገሩ ጉዳይ ዋነኛ ባለቤት በመሆኑም መከበር አለበት፡፡ ማንም ጉልበተኛ እየተነሳ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱን መግፈፍ የለበትም፡፡ አቅምና ብቃት በሌላቸው መመራት አይገባውም፡፡ ከምንም ነገር በላይ ፍላጎቱ መከበር አለበት፡፡ መደመጥ አለበት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል የጀመሩትን ጉዞ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡ እሳቸው ካደረጓቸው ንግግሮች መገንዘብ እንደተቻለው ለሕዝብ ልዩ ትኩረት እንደሚያደርጉ ነው፡፡ ይህ ልዩ ትኩረት ተጠናክሮ በተለይ ዜጎች በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹባቸውና ለአገራቸው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱባቸው መድረኮች በስፋት እንዲከፈቱ፣ የሐሳብ ነፃነትን የሚፈታተኑና መብቶችን የሚገድቡ አላስፈላጊ ድርጊቶች በፍጥነት እንዲገቱ፣ ከዚህ ቀደም በፍርኃት የተሸበቡ ዜጎች እንዲደፋፈሩ፣ እንዲሁም በአገሪቱ የበለጠ መነቃቃት እንዲፈጠር የሚያግዙ ተግባራት እንዲጀመሩ መደረግ አለበት፡፡ በሕግ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች በኃላፊነት ስሜት የመሰላቸውን እንዲያንፀባርቁ፣ በየትኛውም የአገሪቱ ሥፍራ በመዘዋወር ሀብት እንዲያፈሩና የፍትሕ የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጅምሮች ይታዩ፡፡ አገር በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር እየተመራች ዜጎች እኩልነት እንዲሰማቸው፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የሐሳብ ገበያው የበለጠ እንዲደራ፣ ሕገወጥነት እንዲመክን፣ ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ፣ በሥልጣን መባለግ ልጓም እንዲበጅለትና ተጠያቂነት የአገር ባህል እንዲሆን ጥርስን ነክሶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ስሜት መነሳሳት ከተቻለ ሕዝብ ደጀን ይሆናል፡፡ ሕዝብ ይደመጥ፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ነበረች፡፡ በዓለም አደባባይ አንገቷን ያስደፏት ረሃብ፣ ተመፅዋችነት፣ ኋላቀርነትና የመሳሰሉትን ተረት ማድረግ አያቅትም፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የተበላሸው ገጽታዋም መስተካከል ይችላል፡፡ ለዚህ ቀና ሐሳብ ስኬት ሲባል አገርን ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ ሰሞኑን በግልጽ እንደተነገረው፣ በቅርቡ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከድርጅታቸው አመራሮች ድጋፍ ማጣታቸው ያሳምማል፡፡ አገር የሚመራ ሰው ልሥራ ሲል አላሠራ ማለት በአገር ላይ መቀለድ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያልቻሉትና ለሦስት ዓመታት የዘለቀ ነውጥ የተፈጠረው በዚህ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁለገብ ድጋፍ ማድረግ ይገባል፡፡ ዳር ላይ ቆሞ መተቸት ሳይሆን መልካሙን ነገር ሁሉ ማመላከትና ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ ከእሳቸውም ሆነ ከሚያዋቅሩት ካቢኔ ብቻ ከመጠበቅ ድጋፍ ማድረግ ይቅደም፡፡ አደናቃፊነት ለአገር አይበጅም፡፡ የሕዝቡን ስሜት በማንበብ ለአገር ውለታ መሥራት ግን ያስከብራል፡፡ አንገት ከመድፋት መውጣት የሚቻለው ሕዝብን በማዳመጥ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

በደራ ወረዳ ከ100 በላይ ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከ100 በላይ...

‹‹መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት ባለመጠበቁ  መንግሥት ነኝ የማለት ልዕልና የለውም›› የፖለቲካ ፓርቲዎች

የወለጋ ዞኖች በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲተዳደሩ ተጠየቀ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...