Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሚድሮክ አጥሮ የያዛቸው ቦታዎች ካርታዎችን ማምከን እንደሚዘገይ ተገለጸ

ሚድሮክ አጥሮ የያዛቸው ቦታዎች ካርታዎችን ማምከን እንደሚዘገይ ተገለጸ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ተረክበው ሳያለሙ ለዓመታት አጥረው ያስቀመጡ ድርጅቶች ካርታ እንደሚመክን መመርያ ቢተላለፍም፣ በተለይ በአጠቃላይ 54 ሔክታር ስፋት ያላቸው 11 ቦታዎችን የያዘው ሚድሮክ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ያላለሙበትን ምክንያት ማስረዳትና ማሳመን የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ስላልሆኑ አፈጻጸሙ እንደሚዘገይ ተመለከተ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት በአዋጅና በመመርያው መሠረት ባለፈው ዓመት መጨረሻ፣ 120 ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች እስከ ኅዳር 2010 ዓ.ም. ወደ ግንባታ እንዲገቡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡ በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሠረት 66 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ሲገቡ 16 ያህሉ ወደ ግንባታ ባለመግባታቸው ውላቸው ተቋርጧል፡፡

ሚድሮክና የዲፕሎማቲክ ተቋማት የያዟቸው 29 ቦታዎች ውል ተቋርጦ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ጽሕፈት ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ የከተማው አስተዳደርና የጠቅላይ ሚኒስተር ጽሕፈት ቤት ከመከሩ በኋላ በመርህ ደረጃ ካርታ ማምከኑ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርጋሞ ሀማሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተላለፈው መመርያ መሠረት የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች ሳይገነቡ አጥረው የያዟቸው ቦታዎች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡

‹‹ነገር ግን የሚድሮክ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ ቢሰጥም ባለቤቱ ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ለአገር ባለውለታ እንደመሆናቸው፣ በአሁኑ ወቅት በመሬቶቹ ላይ ያላቸውን አቋም መግለጽ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ፣ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ አፈጻጸሙ እንዲዘገይ ተደርጓል፤›› በማለት ለጊዜው ውሳኔው ተግባራዊ እንደማይሆን አቶ ሀርጋሞ አመላክተዋል፡፡

ሚድሮክ ወሎ ሠፈር አደባባይ የሚገኙ ሁለት ቦታዎች፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ካዛንችስ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አጠገብ፣ ሸራተን ማስፋፊያን ጨምሮ 11 ቦታዎች በድምሩ 54 ሔክታር ስፋት ያላቸው ቦታዎችን ይዟል፡፡

ሚድሮክ ከ18 ዓመት በፊት ፒያሳ በሚገኘው ቦታው ላይ እስከ 50 ፎቅ ከፍታ ያለው ሕንፃ የመገንባት ዕቅድ ነበረው፡፡ ቦታው ለግንባታ አስቸጋሪ ነው በማለት አራት ወለል ያለው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ለመገንባት የዲዛይን ለውጥ ተደርጎ ነበር፡፡

በሜክሲኮ እስከ 37 ወለል ያላቸው መንትያ የገበያ ማዕከላት መገንባት ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ቦታው ታጥሮ ለዓመታት ተቀምጧል፡፡

በካዛንቺስም እንዲሁ በቀድሞ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን 15 ወለል ከፍታ ያለው ሕንፃ ለመገንባት አቅዶ ቦታ የያዘ ቢሆንም፣ ከመሠረት ቁፋሮ የዘለለ ግንባታ አልተካሄደም፡፡

የሸራተን አዲስ ማስፋፊያ ከ31 ሔክተር በላይ ከሰው ንክኪ ነፃ ተደርጎ የተቀመጠ ቢሆንም ለዓመታት ታጥሮ ይገኛል፡፡

በቦሌ  ወሎ ሠፈር አካባቢ አራት ሕንፃዎችን ለመገንባት የወሰዳቸው ቦታዎች ላይ ሁለት ሕንፃዎችን ሲያጠናቅቅ ሁለቱ አሁንም በጅምር ቀርተዋል፡፡

እነዚህ ቦታዎች በሕግና መመርያ መሠረት በወቅቱ አለመልማታቸው፣ ከኅብረተሰቡ የሚቀርበው ቅሬታም እየተባባሰ በመምጣቱ ጥቅምት 2010 ዓ.ም. የሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብነት ገብረ መስቀል፣ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በተገኙበት ጉብኝትና ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት አቶ አብነት የነበሩ ችግሮች መፈታታቸውን፣ 23 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን በመግለጽ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸው ነበር፡፡

አቶ አባተ በበኩላቸው በአስተዳደሩ በኩል የነበሩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተፈተዋል ብለው፣ ስለዚህ ሚድሮክ ወደ ግንባታ መግባት እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡ ግንባታ የማይጀምር ከሆነ የውል ማራዘሚያ እንደማይደረግና ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...