ቅዳሜ መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሶማሌ ክልል ያቀኑት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አጋጥሞ የነበረው ግጭት ‹‹ያልተገባ፣ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠና የሁላችንንም አንገት ያስደፋ የሽንፈት ታሪካችን ነው፤›› በማለት ከኅብረተሰቡ ለተወከሉ የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ከሁለቱም ክልሎች በርካታ ዜጎች ለሕልፈት የተዳረጉበትን፣ በርካቶች ለአካል ጉዳት የተጋለጡበትንና ከ700 ሺሕ በላይ የተፈናቀሉበትን ግጭት በዕርቀ ሰላም እንዲቋጭም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ጋር በመሆንም፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳንና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ዑመር እጅ ለእጅ በማያያዝ፣ የተፈጠረው ጠባሳ ፈጥኖ እንዲሽር ከልብ መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዕርቀ ሰላም ጉዞና ኤርትራ
ከስድስት ወራት በፊት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት፣ ከሁለቱም ክልሎች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ቀጥፏል፡፡ ከ700 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችም ተወልደው ካደጉበት ቀዬ እንዲፈናቀሉ፣ እስካሁንም ያፈሩትን ጥሪት ተነጥቀው በመጠለያ ድንኳኖች ሕይወታቸውን እንዲገፉ ምክንያት ሆኗል።
ድርጊቱ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጭፍን መጠቃቃት መሆኑ በርካቶችን ያሳዘነ፣ ኢትዮጵያውያን በሚታወቁበት ለዘመናት ተገንብቶ የዘለቀ አብሮነት ላይ ይህ ትውልድ በታሪኩ የሚያኖረው አሉታዊ ጠባሳ እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል።
ይህንን የታሪክ ጠባሳ መፋቅ ባይቻልም እንዳይሰፋና ለቀጣይ አብሮነት ሳንካ እንዳይሆን፣ ቀደም ብሎ በመንግሥት ሲጠራ የነበረው ዕርቅ በተለያዩ ምክንያቶች መደናቀፋ ደግሞ ሥጋት ፈጥሮ ነበር።
በፈቃዳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትርነት የለቀቁትን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲተኩ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የመረጣቸው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከሳምንት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ የዕርቅና የይቅርታ ነው፤›› ብለው ነበር።
ይህንን በተናገሩ በስድስተኛው ቀን ቅዳሜ መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የዕርቅ ጉዞ ወደ ሶማሌ ክልል በማድረግ የሁለቱ ክልሎች አመረረሮችን በዕርቅ አስተቃቅፈው፣ ቃል አስገብተውና ከሁለቱም ክልል ብሔረሰቦች የተወከሉ ነዋሪዎችን አነጋግረው በስኬት ተመልሰዋል።
የተፈጠረው ግጭት ‹‹ያልተገባ፣ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠና የሁላችንንም አንገት ያስደፋ የሽንፈት ታሪካችን ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በግጭቱ ሁለቱም ወገን ተሸናፊ እንደነበሩም ተናግረዋል።
ሁለቱ ሕዝቦች ደስታንና መከራን ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበሉ ማሳለፋቸውን የረጅም ዘመናት አብሮነትም መለያቸው እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል ያለው ወሰን አስተዳደራዊ መለያ ከመሆን ባለፈ የልዩነት መነሻና የግጭት ምክንያት እንዴት ሆነ ብለዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል የነበረው የአንድነት መንፈስ ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣና የመፍትሔው አካል እንዲሆን፣ የተፈጠረው ችግር ከዚህ በኋላ ውሎ ሳያድር በማያዳግም ዕርቀ ሰላም እንዲቋጭም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
‹‹ጠባሳው ፈጥኖ እንዲሽር ችግሩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝበት ዳርቻ ድረስ ባለን አቅም ሁሉ በርትተን በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል፤›› ብለዋል፡፡
ሁለቱን ሕዝቦች ያጋጨው ያልተገባ ክስተት በፍጥነት በዕርቀ ሰላም እንዲፈታ፣ ከሁለቱም ክልሎች የተናቀሉ ዜጎች በፍጥነት ወደነበሩበት መልሶ የማቋቋም ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ ክልሎችና ሌሎች የፌዴራል መንግሥት አመራሮች የታደሙት የዕርቅ ኮንፈረንስ ባልተለመደ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በስተቀር፣ የክልሎቹ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ ያልተስተዋለበት ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ኡመር ዓሊ የሶማሌ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በፍፁም ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዘመናት የኖረ፣ ከኦሮሞ ብሔር ጋር ደግሞ በተለየ ሁኔታ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት በመተሳሳርና ድንበር በመጋራት ለዘመናት አብሮ የዘለቀ መሆኑን አውስተዋል።
ሁለቱ ሕዝቦች የተሳሰሩበት ገመድ በጦርነትና በተደጋጋሚ ድርቅ ተመትቶ አለመበጠሱን አስታውሰው፣ ከዚህ በተፃራሪ ከወራት በፊት ቤተሰብ በሆኑት የሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል የተከሰተውን ግጭት፣ እንዲሁም ያስከተለውን ዕልቂትና መፈናቀል ማስቆም እየተቻለ ማስቆም ባለመቻላቸው ፀፀት እንደሆነባቸው ተናግረዋል። ይህንን ጠባሳ ለማሻርና ለመሻገር እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።
በተመሳሳይ በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል የነበረውን ግጭት ‹‹ውርደታችን ነው!›› ብለውታል።
‹‹ዛሬ በደረስንበት ደረጃ የእውነት መተሳሰቡ ቢኖር ለአርብቶ አደሮቻችን የምንኖርባት መሬት አላጠረችንም። ስንቱን ተጠቅመንበት ነው ዛሬ ድንበር የምንጋፋው? ላልሠራንበት ነገር ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ለማጥፋት፣ ደም ለማፍሰስ፣ ንብረት ለማውደም ምክንያት መሆን የማይገባቸው ነገሮች ምክንያት ሆነው ይኼንን የሚያህል ጥፋት ሲያደርሱ ለእኛ ውርደት ነው! ውርደት ነው!›› ብለዋል።
‹‹የተፈጠሩ ችግሮች ሁላችንንም ያሳዘኑንና የጎዱን ቢሆንም፣ የተፈጸመውን ጥፋት ማስተካከል ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኔ እንደ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትነቴ በኦሮሞና በሶማሌ መካከል ለሰላምና ለአብሮነት በሚደረገው ማናቸውም ሥራ ውስጥ ቅድሚያ ሰጥቼ እንደምሠራ በእናንተ ፊት ቃል መግባት እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ወንድም ሶማሌዎችን የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትን ጣልቃ መግባት ሳልጠብቅ፣ በራሴና በግሌ ኃላፊነት ወስጄ ወደ ቀድሞ ቦታቸውና ቤታቸው እንዲመለሱ አደርጋለው፤›› ሲሉ በይፋ ቃል ገብተዋል፡፡
የመጀመርያ የዕርቅ ጉዞዋቸውን በዚህ መልኩ ያጠናቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ተመሳሳይ ዓላማ ያነገበ ጉዞ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በአምቦ፣ በመቐለ፣ በሐረርና በስተመጨረሻም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የሚደረገው እንደሆነ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአገር ውስጥ የጀመሩት የዕርቅ ጉዞን ካጠናቀቁ በኋላ በቀጣይ የሚሰጡት ትኩረት ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ላለፉት 20 በላይ ዓመታት የተቋረጠውን ግንኙነት እልባት እንዲያስገኝ መሥራት እንደሚሆን፣ በባዕለ ሲመታቸው ላይ ካደረጉት ንግግር መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን፡፡ የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ፣ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይህንን ጥሪ ባሰሙበት ወቅት ከፓርላማው አባላት የድጋፍ ጭብጨባ ተሰምቷል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛው የሥልጣን አካል ከሆነው የአገሪቱ ፓርላማም ይሁንታ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የኤርትራው መዳረሻ ይሳካ ይሆን?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የዕርቅ ጥሪውን ለኤርትራ መንግሥት ከማቅረባቸው ከሁለት ወራት በፊት በእጅጉ የሚመሳሰል የዕርቅ ፍላጎት ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አንደበት ተደምጧል፡፡ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2018 ከኤርትራ ጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ‹‹ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ዳግም ለመገናኘትና ለመሥራት ዝግጁ ነን፤›› ብለው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝባችም ስለመጪው ዕጣ ፈንታቸው በድጋሚ ገምግመው ሊወስኑ እንደሚገባ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ‹‹ያለፉት 20 ዓመታት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች ኪሳራ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡
በዚህ ንግግራቸው ያልተለመደ አቋም ያሳዩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በዚህ ብቻ አላቆሙም፡፡ የሚከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ በሁለቱ በደም የተሳሰሩ ሕዝቦች ግንኙነት ደግሞ መጀመር እንደሚገባው በአፅንኦት ጠቁመዋል፡፡
የሁለቱ ጎረቤትምና ቤተሰብ ሕዝቦች መንግሥታት የዕርቅ ፍላጎት መገጣጠም የመነጨው በአካባቢው ልዩ ጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች ተመልካች በመሆን ዕጣ ፈንታቸውን ለሌሎች እየሰጡ መሆናቸውን ማስተዋል በመቻላቸው እንደሆነ፣ በአንድ የደኅንነት ትንተና ተቋም ውስጥ የሚያገለግሉና ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ ባለሙያ ይገልጻሉ፡፡
በቀይ ባህርና በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን የመቆጣጠር ወይም ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የመፍጠር ግብግብ እያካሄደ መሆኑን ያስታወሱት እኚህ ባለሙያ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች፣ ኢራን፣ ቱርክና ኳታር በዚህ አካባቢ እየተራኮቱ መሆናቸውን፣ እስራኤልም ግብግቡን በዓይነ ቁራኛ እየተመለከተች እንደሆነ ተንታኙ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ግብግብ ውስጥ ጂቡቲ የጦር መናኸሪያ ከመሆን የባህርና የመሬት ወደብ ኪራዮችን እያጋበሰች ሲሆን፣ ኤርትራና ኢትዮጵያ በአካባቢው ከያዙት ስትራቴጂካዊ ቦታ እንዲሁም ኢትዮጵያ ካላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት አንፃር ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተንታኙ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት የዕርቅ ፍላጎት ግፊት የመነጨው ከአካባቢው ሁኔታ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ፍላጎት ወደ ጥሩ አጋጣሚ ይቀይሩታል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡
እርሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጥሪ ተከትሎ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ለሚዲያዎች በሰጡት አስተያየት፣ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከባድመ ጦሯን አስወጥታ ስምምነቱ ተግባራዊ ካልሆነ ዕርቅ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡ ይህም በሁለቱ አገሮች መሪዎች የተዘራውን ተስፋ እንዳጨለመው፣ የባድመ ጉዳይም የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ቤተሰባዊ ግንኙነት ላይ ሳንካ መሆኑን እንደሚቀጥል ከተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች እየተደመጠ ነው፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የግጭት ተንታኝ አቶ ዳደ ደስታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያቀረቡትን የዕርቅ ጥሪ እንደሚያደንቁ፣ ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት ተገማች የሆነ ባህርይ ስለሌለው ጥሪውን እንዴት እንደሚቀበለው በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ያነሱት የባድመ ይዞታ ጉዳይ፣ በኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እስካልተነሳ ድረስ አምነው እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡
‹‹በሁለቱ አገሮች የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ በደም የተሳሰሩ ሕዝቦች ለጉዳት መዳረግ የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ሕዝቦቹ እየከፈሉት ያለው ዋጋ ትልቅ ነው፡፡ ችግሩ ከዚህ በላይ መቀጠል የለበትም፤›› ሲሉ አቶ ዳደ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡