የዘንድሮ የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል (ፋሲካ) በኢትዮጵያና በምሥራቅ አውሮፓ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ መጋቢት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተገኙበት ተከናውኗል፡፡ የፋሲካ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው አገሮች መካከል ሩሲያ አንዷ ነች፡፡ በሩሲያ የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜቪዴቭም እንዲሁ በትልቁ በመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካቴድራል በዓሉን አሳልፈዋል፡፡ በሰርቢያም እንዲሁ በተመሳሳይ የተከበረ ሲሆን፣ በዓሉን አስመልክቶ ከሃይማኖት አባቶች በሰርቢያና ኮሶቮ መካከል ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ የተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በኪሮብ ከተማ በተከበረው የፋሲካ በዓልም የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፓርሼንስ በቮሎዲሚስኪ ደብር በመገኘት በዓሉን አሳልፈዋል፡፡ የክርስትና እምነት መነሻ በሆነችው ኢየሩሳሌምም ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በቅዱሱ ሥፍራ ተገኝተዋል፡፡ የቅዱስ እሳት (የሆሊ ፋየር) ዝግጅትን ለማየትም በቅዱስ መካነ መቃብር ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው ነበር፡፡ ቢያንስ 7,000 የሚሆኑ በቤተክርስቲያኑ የተገኙ ምእመናን ጧፍ (ሻማ) አብርተው ነበር፡፡ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይከወን እንደነበር የሚነገርለት ጧፍ የማብራት ሥነ ሥርዓት በተለያዩ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ አገሮች ዘንድ በስፋት ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረትም ኢየሩሳሌም የበራው ጧፍ ወደ ተለያዩ አገሮች የተሠራጨ ሲሆን፣ ጧፎቹ ለዚህ ጉዳይ ተብለው በተዘጋጁ ልዩ አውሮፕላኖች ነው በየአገሩ የተላኩት፡፡ ፎቶዎቹ የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን አከባበር ያሳያሉ፡፡
* * *