Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአነጋጋሪዎቹ የመቅደላ ቅርሶች

አነጋጋሪዎቹ የመቅደላ ቅርሶች

ቀን:

መሰንበቻውን ከ150 ዓመታት በፊት በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በእንግሊዝ ሠራዊት ከመቅደላ አምባ የተዘረፉት ቅርሶች ‹‹ኢትዮጵያ ፍላጎቱ ካላት ለረዥም ጊዜ በውሰት ልንሰጥ እንችላለን›› የሚለውን የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየምን መግለጫ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንደማያውቀው አስታውቋል፡፡

ሙዚየሙ መግለጫውን የሰጠው ከመቅደላ የተወሰዱት ቅርሶች በእንግሊዝ በሚገኘው ቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ለአንድ ዓመት ለተመልካች ክፍት ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡

     የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደማርያም መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ቅርሶቹን በተመለከተ፣ ‹‹መንግሥት ከሙዚየሙ ጋር ያደረገው ምንም ዓይነት ውይይት፣ ድርድር፣ ሐሳብ ልውውጥ የለም፡፡ እኔም ከሚዲያ ነው የሰማሁት፤›› ብለዋል፡፡ የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ኃላፊቅርሶቹን ዐውደ ርዕይ  በከፈቱበት ጊዜ ያነሱት ‹‹የግል ሐሳብ እንጅ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም አይደለም፤›› ብለዋል። አሁንም በርካታ ቅርሶች በውጭ አገሮች የሚገኙ በመሆኑ ቅርሶችን የማስመለሱ ሒደት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ ቅርሶቹ ለዕይታ መቅረባቸው የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና ወግ ለዓለም ከማስተዋወቁ ባለፈ ‹‹ለዕይታ የቀረቡት ቅርሶች የኢትዮጵያ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል፤›› ከማለት ግን አልተመለሱም፡፡

የአፄ ቴዎድሮስን መስዋዕትነት ተከትሎ በ1868 .ም. ከመቅደላ አምባ የተዘረፉት ቅርሶች በተለይ 500 በላይ የጽሑፍ ቅርሶች፣ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች፣ የንጉሣውያን የወርቅ ዘውዶችና ጌጣ ጌጦች፣ እንዲሁም አሥር የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ታቦታት በእንግሊዝ የተለያዩ ሙዚየሞች ከመገኘታቸውም በተጨማሪም በርካታ ቅርሶች በግለሰብ እጅ እንደሚገኙ ይታወቃል።

የተዘረፉትን ቅርሶች ለማስመለስ ባለፉት መንግሥታት ከተደረጉት ጥረቶች ባሻገር ‹‹አፍሮሜት›› የሚባለው የመቅደላ ቅርስ አስመላሽ ተቋም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ጥቂት ቅርሶች መመለሳቸው ይታወቃል፡፡ ከሦስተኛው ሚሌኒየም ዋዜማ  ጀምሮ በቀድሞው ፕሬዚዳንት አማካይነት የመቅደላ አምባ ቅርሶች እንዲመለሱ ለእንግሊዝ መንግሥት በደብዳቤ ተጠይቋል፡፡

በእንግሊዝና በተለያዩ የአውሮፓ ሙዚየሞች፣ አብያተ መጻሕፍትና በግለሰቦች እጅ የሚገኙ በርካታ ቅርሶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት ባጭሩ አጠራሩ ዩኔስኮን ጨምሮ በቅርስ ማስመለስ ዙሪያ የተደነገጉ ዓለም አቀፍ ሕጎች እገዛ እንደሚሰጡ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በመግለጫቸው ‹‹ኢትዮጵያውያን ፈቅደውና ወደው በስጦታ መልክ ቅርሶቹን ስላልሰጡ አሁን ያለው የእንግሊዝ ትውልድ 150 ዓመታት በፊት የተፈጠረውን ስህተት በማረም የኢትዮጵያን ሀብቶችን መመለስ ይገባዋል፤›› ሲሉም አሳስበዋል።

መንግሥት ቅርሶችን ለማስመለስ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ሌሎች አካላት በሒደቱ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ለማመቻቸት አፍሮሜትን እንደገና ለማደራጀት አገራዊ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሙዚየሙ ባለፈው ዓርብ በከፈተው ዓውደ ርዕይ በመቅደላ ውጊያ በጄኔራል ናፒር የሚመሩ የእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው የተወሰዱ የዕደጥበብ ውጤቶች በወርቅ የተለበጠ ዘውድ፣ የንጉሣዊ ቤተሰብ አልባሳት፣ የወርቅ ጽዋዎችና ሌሎችንም  አቅርቧል።

ከነፍስ ኄር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጋር በመሆን አፍሮሜትን የመሠረቱት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የኢትዮጵያን ቅርሶች የሚያሳየው ዓውደ ርዕይ መከፈቱን በአዎንታዊ መልኩ እንደሚዩት ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ተናግረዋል። ‹‹ሙዚየሙ በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተዘረፉና በእንግሊዝ የሚገኙ ቅርሶቻችን ለሕዝብ ዕይታ የሚበቁበት አጋጣሚ በጣም አናሳ ነው። ስለዚህ ለሕዝብ ዕይታ መቅረባቸው ኢትዮጵያውያንንም ሆነ የኢትዮጵያን ወዳጆች ደስ ያሰኛል ብዬ እገምታለሁ፤›› ማለታቸውን ቢቢሲ በድረ ገጹ ገልጾታል፡፡ ጨምረውምእነዚህ ቅርሶች እንዲመለሱ ለመሞገትም ቢሆን ለረዥም ጊዜ በብድር ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ በጣም መልካም ነው። ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ ወይም ደግሞ ለቅርስ ጥበቃ የተለየ መነሳሳት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደስተኛ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ፤›› ማለታቸውንም አልሸሸገም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኃይለ ሚካኤል አበራ (ዶ/ር) በበኩላቸው ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የሚደረገውን ጥረት አካል እንደሆነና ደረጃ በደረጃ ወደዚያ የሚወስድ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ዘረፋው እንዴት ነበር?

   ‹‹የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ›› በሚል ርዕስ ጥናት ያከናወኑት ግርማ ኪዳኔ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ካጠፉ በኋላ የመቅደላ አምባን የወረሩት እንግሊዞች የፈጸሙትን ዝርፊያ በዝርዝር አቅርበውታል፡፡ እንዲህም አሉ፡-  

‹‹እንደ እንግሊዝ ጦር አዛዦች አባባል ተልዕኮአቸው የእንግሊዝ እስረኞችን ለማስፈታት ነበረ፡፡ ከዚህ የተልዕኮ ሽፋን በስተጀርባ ግን ዓላማቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ቅርሶች ለመዝረፍ ጭምር መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡ ሪቻርድ ሆምስ የተባለው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ከእንግሊዝ ጦር ጋር አብሮ እንዲመጣ መደረጉ ለዚህ የዘረፋ ተግባር መከሰት እንደነበረ፤ ግልጽ ነው፡፡

‹‹የመጀመርያው ዘረፋ ቡድን ያተኮረው በሟቹ ንጉሥ ሬሳ ላይ ነበር፡፡ የአንገት መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፣ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው የወሰዱ ለመሆኑ በታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡

‹‹ሁለተኛው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው የቤተ መንግሥት ሕንፃ በመድፈር ነበር፡፡ ንጉሡ በሕይወታቸው ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም የሰበሰቡአቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ መጻሕፍትን እንደዚሁም በአሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግሥት ሰነዶችንና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀሩ ዘርፈዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶችና ማኅተም፣ በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለው ታላቁ መጽሐፍ ይገኙባቸዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ማዕድ ቤት ውስጥ በመግባት ሃያ እንሥራ የሚሆን የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ዘርፈው ከመጠን በላይ ሰክረው ነበር፡፡ ከዘረፉዋቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል፡፡ ብዙ ቅርሶች ጥለዋል፣ ሰባብረዋል፣ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል፤ አልባሳትንም ሸካክተዋል፡፡

‹‹የሦስተኛው የዘረፋ ቡድን ከወሰዳቸው መካከል ከወርቅ የተሠራ የአቡነ ሰላማ አክሊል ወይም ዘውድ ጫማና ቀበቶ፣ ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጽዋዎች፣ ከወርቅ የተሠራ በአንገት ላይ የሚጠልቅ የአፄ ቴዎድሮስ የሰሎሞን ኒሻን እንደዚሁም ንጉሡ ሲነግሡ ለብሰውት የነበረው የማዕረግ ልብስ ይገኙባቸዋል፡፡

‹‹አራተኛው ቡድን ከዘረፋቸው መካከል የተለያዩ ጋሻዎች፣ ከነዚህ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተውና የፊታውራሪ ገብርዬ ጋሻ፣ ልዩ ልዩ ጦሮችና ጎራዴዎች፣ ያሸበረቁ የፈረስ ዕቃዎች፣ በተጨማሪም የቴዎድሮስ እስረኞች የታሰሩበት የእግር ብረት ይገኙበታል፡፡

‹‹አምስተኛውና የመጨረሻው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው አፄ ቴዎድሮስ በየአገሩ ሲዘዋወሩ ያርፉበት በነበረው ድንኳናቸውና ይጠጡበት በነበረው ዋንጫቸው፣ የማንነቱ ባልታወቀ የፈረስ ልባብ ላይ ነበረ፡፡ ወታደሮቹ በዚህ ሳይገቱ የደረሱበትን መንደር በማሰስና እያንዳንዱ ቤት ውስጥ በመግባት ተመሳሳይ ዘረፋ ከማካሄዳቸውም ባሻገር ከተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች የተገኙትን መንፈሳዊ ሥዕሎችና እንደዚሁም ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ ታቦቶችን ሳይቀሩ ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ጀምሮ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፡፡

‹‹አብዛኛዎቹ በዘረፋ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ወታደሮች አስተሳሰብ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት እንጂ ለዕቃዎቹ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስነት እንዳልሰጧቸው መገመት አያዳግትም፡፡ ለምሳሌ ሪቻርድ ሆምስ የብሪትሽ ሙዚየም ኤክስፐርትና አርኬዎሎጂሲት ከአንድ በዘረፋ ላይ ተሰማርቶ ከነበረ ወታደር ከወርቅ የተሠራውን የአቡነ ሰላማን የዘውድ አክሊልና የወርቅ ጽዋ በላዩ ላይ በግዕዝ እንደሚከተለው የተጻፈበትን ‹‹ዝንቱ ጽዋ ዘወሀብዋ ዳግማዊ ኢያሱ ወብእሲቱ ወለተ ጊዮርጊስ ለቅድስት ቁስቋም ከመ ትኩኖሙ መድኃኒተ ሥጋ ወነፍስ›› ወደ አማርኛ ሲተረጐም- ይህ አፄ ኢያሱ ብርሃን ሰገድ ለቁስቋም ቤተ ክርስቲያን ያበረከቷቸውን ሦስት ኪሎ የሚመዝኑ የቁርባን ጽዋዎች›› ማለት ሲሆን እነዚህንም በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ እንደሸጠላቸው ይነገራል፡፡

‹‹ጄኔራል ናፒየር የወታደሮቹን አስተሳሰብ መነሻ በማድረግ በመቅደላና በአካባቢዋ የተዘረፉት የባህልና የታሪክ ቅርሶቻችን በሙሉ በጨረታ እንዲሸጡ ወሰነ፡፡

ጨረታውን የተሳካ ለማድረግ ገላጣ በሆነችው ደላንታ ሜዳ እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ ቅርሶቹን ከመቅደላ ወደ ደላንታ ለማድረስ በአሥራ አምስት ዝሆኖችና ከሁለት መቶ በላይ በሚሆኑ አጋሰሶች ተጠቅመዋል፡፡ ይህም የሚነግረን የቱን ያህል ብዛት ያላቸው ቅርሶች ተዘርፈው እንደነበረ ነው፡፡

‹‹ደላንታ እንደደረሱም የተለያዩ ስጋጃዎች ሜዳው ላይ እንዲነጠፉ ተደረገ፡፡ በስጋጃዎቹ ላይ ቅርሶች በየዓይነታቸው ተደርድረው ለጨረታ ተዘጋጁ፡፡ አጫራችም የሚሆን መኰንን ተመረጠ፡፡ ለሽያጭም ከቀረቡት ዕቃዎች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር ይገኝበት ነበር፡፡ ጨረታው ከተጀመረ አንስቶ እስካለቀበት ጊዜ ድረስ በማንም ሊሸነፉ ያልቻሉት ቀደም ሲልም ገና ከአገራቸው ሲንቀሳቀሱ ገንዘብ አስታቅፈዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ተሸኝተው የነበሩት የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሚስተር ሪቻርድ ሆምስና እንዲሁም ከወታደሮቹ በኩል ኮሎኔል ፍሬዘር ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ፣ አፄ ቴዎድሮስ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ይይዙት የነበረው በብርና በወርቅ ያሸበረቀ ጋሻ የጨረታው መነሻ አሥር ዶላር ሆኖ እስከ ሁለት መቶ ዶላር በመድረስ ኮሎኔል ፍሬዘር የጨረታው አሸናፊ በመሆን ሊገዛው ችሏል፡፡ ጨረታው ለሁለት ቀናት ያህል ከተካሄደ በኋላ ከሽያጭ የተሰበሰበውን አምስት ሺሕ ፓውንድ ወታደሮቹ እንዲከፋፈሉት ተደረገ፡፡

‹‹ምንም እንኳ ጄኔራል ናፒየር ባዘዘው መሠረት በመቅደላ ተሰብስበው የነበሩት ሁሉ ቅርሶች ለጨረታ ቀርበው ነበር በማለት ለማስመሰል ተሞከረ እንጂ፣ አንዳንድ ባለሀብቶች በተለይም ሲቪሎችና ኦፊሰሮች ራሱ ጄኔራል ናፒየር ሳይቀር ቀደም ብለው ጨረታው በይፋ ከመጀመሩ በፉት ለየራሳቸው ያከማቹአቸው ቅርሶች በብዛት እንደነበሩ ድርጊቱ ካለፈ በኋላ ሊታወቅ ችሏል፡፡ ለምሳሌ ለጨረታው ካልቀረቡት ቅርሶች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶች፣ የክብርና የማዕረግ ልብሶቻቸው፣ በሺሕ የሚቆጠሩ የብራና መጽሐፎችና የቴዎድሮስ ማኅተም፣ የአቡነ ሰላማ የወርቅ አክሊል፣ በብር ያሸበረቀ ጋሻ፣ በክብረ በዓል ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል የቴዎድሮስ ከበሮና የመሳሰሉት ከሌሎች ንብረቶች ጋር ከመቅደላ ቤተ ክርስቲያን አጥር ግቢ በነበሩት ጎጆዎች ውስጥ ታምቀው እንደነበር ይነገራል፡፡

‹‹በተለይም ከአቡነ ሰላማ መቃብር ላይ ተፈጽሞ የነበረውን የስርቆት ወንጀል አስመልክቶ ሲናገርበጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መቃብር ድረስ በመሄድ መቃብሩን አውጥቶና ሰብሮ ብዙ ሺሕ ዶላር ሊያወጣ የሚችል ከአልማዝ የተሠራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበር ነው፤ሲል በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡

‹‹የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሠራ አክሊልና የቁርባን ጽዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ላይ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሆልምስ በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበር ቀደም ሲል ተጠቅሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዞች ድል አገኘን ብለው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የተጠቀሱትን ሁለት ቅርሶች ሪቻርድ ሆልምስ ከኮሎኔል ፍሬዘር፤ ከኮሎኔል ሚልወርድና ከኮሎኔል ካሜሩን ጋር ለብሪትሽ ሙዚየም በሁለት ሺሕ የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲሸጥላቸው ... ጁላይ 1 ቀን 1868 አቅርበውት እንደነበር የደብዳቤ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

‹‹በሽያጭም ሆነ ወይም በስጦታ መተላለፋቸው ለጊዜው ባይታወቅም በአሁኑ ጊዜ ከመቅደላ የተወሰዱት ቅርሶች በእንግሊዝ አገር ሙዚየሞች ውስጥ በአመጡአቸው ሰዎች ስም ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በጻፈው ‹‹ ፕሬስተር ጆን›› ተብሎ በሚጠራው መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ተርጓሚዎቹና አዘጋጆቹ ሀንቲንግፎርድና ቤክንግሃም እንደጠቀሱት በብሪትሽን ሙዚየም ውስጥ ‹‹ሆልምስ ኮሌክሽን›› እየተባሉ የሚጠሩ አሥር ታቦቶች ከመኖራቸውም በላይ ብዛታቸው ከአንድ ሺሕ በላይ የሚደርስ የኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፍ መጽሐፎች በተጠቀሰው ሙዚየም ውስጥ ተደርድረው ይታያሉ፡፡

ግርማ ኪዳኔ በማጠቃለያቸው የኢትዮጵያ ሀብቶች በተለያዩ ሥፍራዎችና ሙዚየሞች ውስጥ በግለሰቦችም እጅ ጭምር የሚገኙ መሆናቸው መታወቅ እንዳለበት፣ ይህ ሁኔታ የተጠቃለለ ኢንቨንተሪ ለመሥራት አስቸጋሪ ቢያደርገውም ጥረቱ መቀጠል እንደሚኖርበት ከሃያ ስምንት ዓመት በፊት አሳስበው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...