Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የታኅሣሥ ንቅናቄ የተጀመረው ንጉሠ ነገሥቱን በመጥላት ሳይሆን ኢትዮጵያ እንድትሻሻልና ከሌላው ጋር እኩል እንድትሆን በማሰብ ነው››

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ ገመዳ፣ የቀድሞው የክብር ዘበኛ ጦር አካዴሚ የመጀመርያው ተመራቂ

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ ገመዳ በክብር ዘበኛ ጦር አካዴሚ ሠልጥነው ከወጡ የመጀመርያው ዙር ተመራቂዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ መታሰቢያነቱ እሳቸውን ጨምሮ የአካዴሚው የመጀመርያ ኮርስ የጦር መኰንኖች የሆነና ታሪካቸውን የሚያወሳ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በኮሪያና በኮንጎ ዘምተው ዓለም አቀፍ ግዳጃቸውን በድል አድራጊነት ተወጥተዋል፡፡ ኮሪያ ዘምተው ከተመለሱ ሲስተር የመቶ አለቃ ብርቅነሽ ከበደ ጋር ተጋብተው አራት ልጆችና አምስት የልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የአካዴሚውን መቋቋም፣ በአጠቃላይ የቀድሞው የክብር ዘበኛን እንቅስቃሴና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ጄኔራል መኰንኑን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሮአቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የክብር ዘበኛ ጦር አካዴሚ መቼ እንደተቋቋመና እንዴት እንደተቀላቀሉ ቢያስረዱን፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- የክብር ዘበኛ ጦር አካዴሚ የተቋቋመው የጣሊያን ወራሪ ጦር በጀግኖቹ የኢትዮጵያ አርበኞች ድል ተመትቶ ከአገራችን በወጣ ማግስት ማለትም በ1933 ዓ.ም. ነበር፡፡ አካዴሚውን በማቋቋም ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት በወቅቱ የክብር ዘበኛ አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ናቸው፡፡ መምህራኑም ስዊድናውያን መኰንኖች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መኰንኖች መካከል የአካዴሚው ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ቴክ ኦሊ ናቸው፡፡ ከእኔ ጋር የነበሩ የመጀመርያው ኮርስ ተሳታፊዎች 120 ዕጩ መኰንኖች ነበርን፡፡ ለሥልጠና የመጣነውም ከትምህርት ቤታችን ተመልምለን ሲሆን፣ ምልመላ ከተካሄደባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል ተግባረ ዕድ፣ ተፈሪ መኰንን፣ ዳግማዊ ምኒልክ፣ መድኃኔ ዓለም ትምህርት ቤቶችና ሌሎቹም ይገኙባቸዋል፡፡ ስንመለመል ለምን እንደሆነ አልገባንም ነበር፡፡ በመኪና ጭነውን ክብር ዘበኛ ሰፈር አወረዱን፡፡ እንደወረድንም ያመጣናችሁ በክብር ዘበኛ ውስጥ በዕጩ መኰንንነት እንድትማሩ ነው አሉን፡፡ ወዲያውኑ የሕክምና ምርመራ ተደረገልን፡፡ ቀጥሎ የለበስነውን አስወለቁን፣ ፀጉራችንን ላጩንና በላያችን ዲዲቲ ነፉብን፡፡ አንዱ ሌላውን ለመለየት እስኪቸገር ድረስ ነጭ ሆነን ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ዲዲቲው እየጠፋ ሲመጣ መተዋወቅ ጀመርን፡፡ ከዛም ያወለቅነው ልብስ ተጥሎ በምትኩ አዳዲስ አልባሳትን ሰጡን፡፡ ከዚያም በስዊድን መኰንኖች አማካይነት ትምህርታችን ጀመርን፡፡ ለሦስት ዓመታት ያህል ትምህርቱን በሚገባ ከተከታተልን በኋላ በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ተመረቅን፡፡ በአካዴሚውም ታሪክ የመጀመርያዎቹ ተመራቂዎች እኛ ነን፡፡ ትምህርቱን የጀመርነው ቅድሚያ በሦስት የመቶ ከተደራጀን በኋላ ነው፡፡ አደረጃጀቱም ቁመትን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ አጫጭሮቹ ሦስተኛ የመቶ፣ መካከለኞቹ ሁለተኛ የመቶ ሲሆኑ እኔን ጨምሮ ረጃጅሞቹ አንደኛ የመቶ በሚል ተደልድለን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሥልጠናው ወቅት በተፈጸመ ስህተት ወታደራዊ ቅጣት ተፈጽሞባችሁ ያውቃል፡፡ ከተፈጸመም በምን ምክንያት እንደሆነ ቢያብራሩልን፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- አንድ ቀን ሩጫ ነበር፡፡ እሮጠን ውለን ተመልሰን ስንመጣ ምግባችን ተዘጋጅቶ ጠበቀን፡፡ ለመመገብ ሥርዓቱን ጠብቀን ወደ ምግብ አዳራሹ ገባን፡፡ ገብተን በየጠረጴዛችን ላይ ስንቀመጥ ሳህን ላይ የተቀጠው ማካሮኒ ከአንድ ዳቦ ጋር ነው፡፡ በጣም ደክሞናል፡፡ ወዲያውኑ ምግቡን አትብሉ የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ይህንን ነገር ከመካከላችንም ማን እንደተናገረ አናውቅም፡፡ ሁሉም ዝም ቁጭ ብሎ ብቻ ሳህኑን ማየት ሆነ፡፡ ከዛ ተረኛው ሄዶ ለትምሀርት ቤቱ ኃላፊያችን ነገረ፡፡ ኃላፊያች ደግሞ የሚኖረው በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ እንደተነገረውም ወዲያውኑ ወደ ምግብ አዳራሹ መጥቶ እየዞረ ተመለከተን፡፡ ተመልሶም ቆመና አምስት ደቂቃ ሰጥቼያችኋለሁና ብሉ አለን፡፡ ዝም አልን፡፡ የተባለው ደቂቃ ሲደርስ ውጡና በየአልጋችሁ ሄዳችሁ ተሠለፉ አለን፡፡ በታዘዝነውም መሠረት ወጥተን ቆምን አስተማሪዎቻችን ተጠሩ፡፡ ከዛ በኋላ እንደገና ውጡና ተሰለፉ ተባልን፡፡ ከዛም ከቀኑ ሰባት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ተኛ፣ ተነስ፣ ቁጭ በል እያሉ ካደቀቁን በኋላ እንደገና እንድንሰለፍ አደረጉን፡፡ ከተሰለፍንም በኋላ ወደ ግብር ቤት ግቡ አሉን፡፡ ገባንና አንበላም ያልነውን ዝንብ ሲያርፍበት የዋለውን መኮሮኒ እንክት አድርገን በላን፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ጦር ሠፈራችን ተመልሰን በማግስቱ አለቆቻችን መጥተው አነጋገሩን፡፡ የጎደለውን ነገር እናሟላለን ብለው ቃል ገቡልን፡፡ በጉቡትም ቃል መሠረት ምግባችን ላይ ትንሽ የሥጋ ጥብስ ታክሎበትና ተስተካክሎ ቀረበልን፡፡ ያቺ ቅጣት ሥርዓት ለእኛ ትልቅ ትምህርት  ሰጥቶና ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ማወቅ ያለብን መሆኑን አስገንዝቦን አልፏል፡፡

ሪፖርተር፡- ለሥልጠና ከገበችሁት መካከል ስንቶቹ ተመረቁ? ከተመረቁትስ መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉት ስንት ናቸው? ያለፈውን ታሪክ ለመጪው ትውልድ ለማቆየት ምን ዓይነት ሥራስ ተከናውኗል?

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- ለሥልጠና ከገባነው መካከል የተመረቅነው 118 ነን፡፡ ከተመራቂዎችም መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያለነው ስምንት ብቻ ነን ከእነዚህ መካከል እኔን ጨምሮ አራታችን በአገር ውስጥ፣ የቀሩት አራቱ ደግሞ አሜሪካ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ቤት ውለዋል ወይም የአልጋ ቁራኛ ሆነዋል፡፡ በደህና ጊዜያቸው ለአገራቸው አኩሪ ገድል ፈጽመዋል፡፡ የሚመጣውን ደግሞ በፀጋ መቀበል ግዴታ ነው፡፡ በተረፈ የቀድሞውን ታሪክ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የክብር ዘበኛን ጦር አካዴሚና በአጠቃላይም የሠራዊቱን እንቅስቃሴ የሚያመላክቱ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ተዘጋጅተው በኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ሙዝየም እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ መጻሕፍቱን ካዘጋጁትም መኰንኖች መካከል ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ ገመዳ፣ ሜጀር ጄኔራል ነጋ ኃይለ ሥላሴ፣ ብርጋዴር ጄኔራል መልኬ ጌታሁን፣ ብርጋዴር ጄኔራል ታምራት ተሰማ፣ ኮሎኔል ይልማ ተሾመ፣ ኮሎኔል ቃለክርስቶስ ዓባይ ይገኙባቸዋል፡፡ በተለይ ኮሎኔል ቃለክርስቶስ ክብር ዘበኛ በ1953 ዓ.ም. ያካሄደውን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ወይም የታኅሣሥ ግርግር እየተባለ የሚጠራውን ንቅናቄ እንዲሁም ኢትዮጵያ በኢጣልያ መወረርን አስመልክቶ የጻፏቸው ሁለት መጻሕፍት አድናቆትን ያተረፉ ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ ኮሎኔሉ የክብር ዘበኛ የዘመቻ መኰንን ስለነበሩ ግርግሩን በሚገባ ጽፈውታል፡፡

ሪፖርተር፡- የጦር አካዴሚው የመጀመርያው አዛዥ ሌተና ጄኔራል ቴክ ኦሊ ከሠልጣኞች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ለኢትዮጵያ የነበራቸው ፍቅር እንዴት ይገለጻል?

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- ትምህርት ቤት ስንገባ ሦስት የመቶ አዛዦች ሻምበሎች ነበር፡፡ የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ሻለቃ ቴክ ኦሊ በኋላ ሌተና ኮሎኔል ከዛም ሌተናል ጄኔራል ነበሩ፡፡ ኃላፊው ጥሩ አዛዥ መኮንን ነበሩ፡፡ ስውዲኖች ለኢትዮጵያ ብዙ ውለታ የዋሉ ናቸው፡፡ ውለታቸውም በወታደራዊ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በትምህርትና በጤና ዘርፎችም ጭምር ነው፡፡ ሲያስተምሩንም ዕውቀታቸውን አይቆጥቡም፡፡ በተለይ ጄኔራል ኦሊ ሲያስተምሩን ‹‹እቺ አገራችሁ ነች ጠብቋት፣ የምትማሩትም እቺን አገር ልትጠብቁ ነው፤›› ይሉን ነበር፡፡ በየገጠሩም እየወሰዱን አገሪቷ ምን ያህል ለምለም እንደሆነች እዩ ይሉን ነበር፡፡ እኛንም ልጆቼ እያሉ ይጠሩን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የቆይታ ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በ1953 ዓ.ም. የታኅሣሥ ግርግር ተከሰተ፡፡ ብዙ የክብር ዘበኛ መኰንኖችም ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡ ጄኔራል ኦሊ ከፍቅራቸው የተነሳ ባለቤታቸውን ልጆቼ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አጣርተሽ ነይ ብለው ከስዊድን ጋዜጠኞች ጋር ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው፡፡ ባለቤትየውም ለሁለት ወራት ያህል በየእስር ቤቱ እየተመላለሱ መኰንኖችን ሲጠይቁና ብዙም ዕርዳታ ሲያበረክቱ ከቆዩ በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ እስከዚህ ድረስ ነው ፍቅራቸው ጄኔራል ኦሊ ለክብር ዘበኛ ጦር አካዴሚ ብቻ አይደለም የሠሩት፤ ጄኔራል ሙሉጌታ ቺፍ ኦፍ ስታፍ (ኤታ ማዦር ሹም) ሆነው ወደ ጦር ኃይሎች ሲሄዱ ጄኔራል ኦሊና ሌሎችንም የስዊድን መኰንኖችን ይዘው በመሄድ ጦር ሠራዊትን በማደራጀትና በማዋቀር ሥራ ላይ እንዲሳተፉ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ክብር ዘበኛ ኮሪያ በዘመተበት ወቅት እህቶቻችንም ከወንዶች ወንድሞቻቸው ጋር እኩል ዘምተው ዓለም አቀፍ ግዴታቸውን እንደተወጡ ይታወቃል፡፡ እነዚህ እንስቶች እነማን እንደሆኑ፣ እንዴት እንደዘመቱና በአሁኑ ጊዜ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ቢገልጹልኝ፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- ከእኛ ጋር ኮሪያ ዘምተው ዓለም አቀፍ ግዴታቸውን የተወጡት ሲስተር ምክትል የመቶ አለቃ ብርቅነሽ ከበደ እና ሲስተር ሻምበል አስቴር አያና ናቸው፡፡ ሁለቱም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ለመጀመርያ ጊዜ በነርስነት ካሠለጠናቸው አሥር ነርሶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በኮሪያ ልሳነ ምድር ግዳጃቸውን በአኩሪ ሁኔታ ከፈጸሙ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ከሁለቱም ነርሶች መካከል ሲስተር ሻምበል አስቴር አያና ሊካሳ የተጠቀሰውን ማዕረግ ከተሰጣት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ኮንጎ ዘምታ ተመልሳለች፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ የእናት ባንክ አቃቂ ቅርንጫፍ የሚገኘውን ባንክ በስሟ ተሰይሟል፡፡ የእነሱና የአባታቸው ስሞች ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት ሲስተሮች ነበሩ፡፡ ይህም ሁኔታ ሰዎች ግራ እንዲጋቡ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሲስተር ሻምበል አስቴር አያና ሊካሳ አልሞቱም አሜሪካ ይገኛሉ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አሜሪካ የምትገኘው ሲስተር አስቴር አያና ብሩ የምትባል ናት፡፡

ሪፖርተር፡- ክብር ዘበኛ እንዴት ተቋቋመ? ማን ነው የማቋቋሙን ኃላፊነት ወስዶ የሠራው?

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- ክቡር ዘበኛ የተቋቋመው በ1909 ዓ.ም. ነበር፡፡ ነገር ግን በዘመናዊነት፣ የተደራጀውና በሠለጠኑ መኰንኖች መመራት የጀመረው ከፋሺስት ጣሊያን ወረራ በኋላ ማለትም በ1933 ዓ.ም. ነው፡፡ የተቋቋመውም ለንጉሡና ለንጉሣውያን ቤተሰቦች ጠበቃነት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ያቋቋሙትና የመጀመርያው ዘመናዊ ክብር ዘበኛ አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ናቸው፡፡ እኚሁ ጄኔራል መኮንን የተማረ የጦር መሪ ለማፍራት የሚያስችለውን የክብር ዘበኛን ጦር አካዴሚ አቋቋሙ፡፡

ሪፖርተር፡- ብልህነታቸውን እንዴት ይገልጹታል?

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- የፋሺስት ጣሊያን ወራሪ ጦር በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ ድል ከተመታ በኋላ ጅግጅጋ አካባቢ ሰፍሮ የነበረው የእንግሊዝ ጦር ሐርጌሳን ጨምሮ የሰፈሩበትን ቦታ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፡፡ ለዚህም የሰጡት ምክንያት የግጦሽ ቦታዎች ናቸው የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ከብዙ ውይይት በኋላ ጦሩ ከጅግጅጋ ለቆ እንዲወጣና ቦታውም በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲተዳደር ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ከክብር ዘበኛ ሠራዊት አምስተኛ የሻለቃ ጦር ጅግጅጋን እንዲረከብ ታዞ ወደ ሥፍራው ተንቀሳቀሰ፡፡ እኔ ያን ጊዜ የሻምበል አዛዥ ነበርኩ፡፡ ጦሩም በድሬዳዋ አድርጎ ወደ ጅግጅጋ ካቀና በኋላ ካራማራ ከመድረሱ በፊት አንድ ቦታ ላይ እንዲሰፍር ተደረገ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አካባቢውን ለመቆጣጠር የተሰጠንን መመርያ ለመፈጸም ሲባል ነው፡፡ በወቅቱም የተጠቀምንበት የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ከአሜሪካ መንግሥት የተሰጠን 12 ‹‹ማክ›› የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ጅግጅጋም የደረስነው መንገዱን እየሠራንና እያቋረጥን ነው፡፡ ጅግጅጋ ከደረስን በኋላ ከድሬዳዋ ስንቅ ስለመጣልን አንድ ማክ ለመጫን ሄዶ ጭኖ ሲመለስ ሠፈር ከመድረሱ በፊት ተገለበጠ፡፡ በዚያን ጊዜ እንግሊዞች ሐረር ነበሩ፡፡  ምክንያቱም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመግዛትም ያስቡ ነበር፡፡ ግን አልሆነላቸውም፡፡ የመኪናውም መገልበጥ አዲስ አበባ ለጄኔራል ሙሉጌታ ቴሌግራም ተደረገላቸው፡፡ ጄኔራሉም ከተቻላችሁ ሌሊቱን አንሱ፣ የማይቻል ከሆነ አቃጥሉት አሉን፡፡ ይህን ትዕዛዝ ሊሰጡ የቻሉት ጉዳዩ የፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነና እንግሊዞችም በሐረር በኩል ሁልጊዜ ወደ ሐርጌሳ ስለሚመላለሱ የመኪናውን መገልበጥ ድንገት ካዩ ኢትዮጵያ ራሷን አትችልም፣ መኪናውንም ለመቆጣጠር ተስኖአቸዋል እያሉ በኢትዮጵያ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ለማከናወንና መጥፎ ገጽታም ከማላበስ ወደኋላ አይሉም በማለት ነው፡፡ እኛ ግን ሌሊቱን ሄደን የተገለበጠውን መኪና አስነስተንና አቃንተን ወደ ሰፈራችን ይዘነው ገባን፡፡ በመጨረሻም በሸራ ተሸፍኖ በባቡር ተጭኖ ለጥገና ወደ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ይህም የጄኔራሉን ብልህነት ያሳያል፡፡

ሪፖርተር፡- የክብር ዘበኛ የመጀመርያው አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ሲሆኑ፣ ቀጣዩ አዛዥ ደግሞ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እኚህን ጄኔራል መኰንኖች እንዴት ይገልጿቸዋል?

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር ጦሩን እየመሩ ከስደት የተመለሱ ናቸው፡፡ እንደተመለሱም ክብር ዘበኛን እንደገና በአዲስ መልክ እንዲያቋቁሙ ከጃንሆይ ታዘዙ፡፡ በተሰጣቸውም ትዕዛዝ መሠረት ክብር ዘበኛን በ1933 ዓ.ም. እንደገና በአዲስ መልክ አደራጁ፡፡ ያቋቋሙትም አምቦ ውስጥ ነው፡፡ ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ክብር ዘበኛን ብቻ አይደለም ያቋቋሙት፡፡ አየር ኃይልን፣ ባህር ኃይልንና ምድር ጦርንም አሠልጥነዋል፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ደግሞ አዛዥ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ወጣት መኰንኖቻቸውን በጣም የሚወዱና የሚያፈቅሩ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ የመኰንኖቻቸው ሞራል ሲነካ አይወዱም፡፡

ሪፖርተር፡- በኮሪያ ልሳነ ምድር ዘምታችሁ ከተመለሳችሁ በኋላ አሁን በሕይወት ያሉት የክብር ዘበኛ ዘማቾች ስንት ናቸው? ምንስ እያደረጉ ነው? የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ኮሪያ ዘምተውና ግዳጃቸው ተወጥተው ለተመለሱት እስካሁን ምን አድርጓል?

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- ኮሪያ ዘምተን ከተመለስነው መካከል በሕይወት ያለነው ከ200 በላይ እንሆናለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 100 ያህሉ ቤት ውለዋል፡፡ የኮሪያ መንግሥት በኮሪያ ልሳነ ምድር ግዳጃቸውን ሲወጡ ለተሰውት ዘማቾች የመታሰቢያ ሐውልት አቁሞላቸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ጽሕፈት ቤትም ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ሠርቶላቸዋል፡፡ ሕንፃው ራሱን የቻለ ሙዚየም፣ የስብሰባ አዳራሽና ልዩ ልዩ ቢሮዎች አሉት፡፡ የኮሪያ ሕዝብ ደግሞ በሕይወት ለሚገኙ ዘማቾች በየወሩ የገንዘብ ድጎማ የሚያደርግላቸው ሲሆን፣ ለቤተሰቦቻቸውም ጭምር ነፃ የሕክምና አገልግሎት እያቀረበ ይገኛል፡፡ የዘማች ልጅ ልጆችን በልዩ ልዩ የቴክኒክ ሙያ ላይ ያተኮረ ትምሀርትም ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ክብር ዘበኛ ታኅሣሥ 1953 ዓ.ም. ያካሄደውን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ወይም የታኅሣሥ ግርግር እየተባለ የሚጠራው ንቅናቄ ዓላማ ቢነግሩን፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ደስታ፡- ሙከራውን የጀመረው ክብር ዘበኛ ብቻ አይደለም፡፡ የጦር ሠራዊት ከፍተኛ መኰንኖችም በንቅናቄው ላይ ነበሩበት፡፡ ነገር ግን የግንኙነት ጉዳይ ስላልተመቻቸ ሁኔታው ሊከሽፍ ቻለ፡፡ በተረፈ ሁሉም ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ለውጥ የማይፈልግ ሰው የለም፡፡ ክብር ዘበኛም ንቅናቄውን የጀመረው ንጉሠ ነገሥቱን በመጥላት ሳይሆን ኢትዮጵያ እንድትሻሻልና ከሌላው ጋር እኩል እንድትሆን በማሰብ ነው እንጂ፣ ከዚህ ውጪ የሆነ ፍላጎትና ዓላማ አልነበረንም፡፡ በወቅቱ የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች ግን ክብር ዘበኛ የቤተ መንግሥት ጮማ እየጎረዳና ጠጅ እየጠጣ ሲወፍር ጊዜ ዙፋኑን ለመገልበጥ አመፀ እያሉ ሲያወሩ ነበር፡፡ ይህ በፍጹም ስህተትና ከዕውነት የራቀ ነው፡፡ የንቅናቄውም ዓላማ ይህ አልነበረም፡፡ በንቅናቄው ወቅት የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ቤተሰቦቻቸውን በሚገባ ጠብቀን በክብር ያዝናቸው እንጂ አፍነን አልገደልናቸውም፡፡ ያን ጊዜ እንዲሁ ዓይነት ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች ናቸው ንጉሠ ነገሥቱን አፍነው የገደሏቸው፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...