Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ትምህርት ቤቶች የጥራት መቆጣጠሪያ ሥልቶች ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኤጀንሲው በትምህርት ጥራትና ደረጃ ላይ ድርድር የለም ይላል

የአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ በቅርቡ ጠርቶት በነበረው ስብሰባ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶችን በተለይም የግል አገልግሎት ሰጪዎችን ለማነጋገርና በአገሪቱ የትምህርት ጥራት ላይ በተቀመጠው ደረጃ መሠረት ያዘጋጀውን የመቆጣጠሪያ ሰነድ ወይም ‹‹ቼክ ሊስት›› ይፋ ባደረገበት ወቅት ቅሬታ ቀረበበት፡፡

የግል ትምህርት ቤቶቹ ካቀረቧቸው በርካታ ቅሬታዎች መካከል ኤጀንሲው በደረጃው መሠረት አዘጋጀሁት ያለው መቆጣጠሪያ ሰነድ፣ ውይይት ሳይደረግበትና የትምህርት ተቋማቱ ሐሳብ ሳይሰጡበት የወጣ መሆኑ አንዱ ነው፡፡

በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሠሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ጣሰው ከሪፖርተር ስለውይይቱ ተጠይቀው እንደገለጹት፣ የጥራት መቆጣጠሪያ ሰነዱ ሲወጣ ትምህርት ቤቶቹ እንዲሳተፉበት ካለመደረጋቸውም ባሻገር ከወጣም በኋላ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ማግኘት አልቻሉም፡፡ 

ኤጀንሲው በትህምርት ጥራትና አግባብነት ደረጃ መሠረት አዘጋጀሁት ባለው መቆጣጠሪያ ሰነድ ውስጥ ከተካተቱት መጠይቆች መካከል፣ በአንድ ትምህርት ተቋም ውስጥ ለመፀዳጃ ቤቶች የተየጠቀው ካከራከሩና ካነጋገሩት ውስጥ አንደኛው ነው፡፡ ይኼውም በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ሽንት ቤት ለ20 ተማሪዎች መኖር እንዳለበት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ እንደ አቶ አበራ ገለጻ፣ 3,000 ተማሪዎች ያሉት አንድ የትምህርት ተቋም በዚህ ጥመርታ መሠረት 150 መፀዳጃ ቤቶችን መገንባት ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ‹‹ይህ ምክንያታዊ አይደለም፤›› ያሉት አቶ አበራ፣ ሌሎችም እንዲህ ያሉ የከተማዋንና የትምህርት ተቋማቱን ነባራዊ ዕውነታዎች ከግምት ያላስገቡ መጠይቆች በመቅረባቸው ምክንያት ቅሬታ ማሳደራቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ በአዲስ አበባ ከተማ 1,600 ያህል የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይሁንና መሠረታዊ ከሚባሉ የተቋማቱ ችግሮች መካከል የቦታ ጥያቄ ዋነኛው ሆኖ ይገኛል፡፡ በስፋቱ ለትምህርት ቤቶች የሚውል ቦታ በሊዝም ሆነ በድርድር ማግኘት ከባድ እንደሆነ አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶችም ሕንፃ ተከራይተው ለመሥራት የሚገደዱት መሬት ማግኘት ባለመቻላቸውና የሚጠይቀው ኢንቨስትመንትም ከፍተኛ በመሆኑ ጭምር እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ 

ከዚህ ባሻገር በግል ትምህርት ቤቶችና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን እኩል ዕድል እንደማያገኙም አብራርተዋል፡፡ ለአብነትም ለመንግሥት ትምህርት ቤት አስተማሪዎች የሚሰጠው የትህምርት ዕድልና የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለግል ትህምርት ቤቶች አስተማሪዎች አይሰጥም ብለዋል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ለመምህራኖቻቸው አበል ሲያስቡ ታክስ ቁረጡ እንደሚባሉም ጠቅሰዋል፡፡

እንዲህ ያሉ አሠራሮች በተዘዋዋሪነት የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ዋጋ እንዲጨምሩ የሚያስገድዷቸው ችግሮች መሆናቸውንም አቶ አበራ ይናገራሉ፡፡ መንግሥት የክፍያ ጭማሪን በሚመለከት ጣልቃ በመግባት ሲንቀሳቀስ መታየቱም ችግሩን እንደማይቀርፈው ተገልጿል፡፡ የትምህርት አገልግሎት ኢንቨስትመንት በገበያ ዋጋ የሚመራ እንደመሆኑ ዋጋ ላይ የሚከተለው አቋምና ጣልቃ ገብነትም መታየት እንደሚገባው ትምህርት ቤቶቹ ይናገራሉ፡፡

የክፍያ ዋጋ በገበያው እንደሚመራ መንግሥት ያምናል በማለት በትምህርት ቤቶቹ ቅሬታ ላይ ምላሽ የሰጡት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ብሩክነሽ አርጋው ናቸው፡፡ ወ/ሮ ብሩክነሽ ትምህርት ቤቶቹ ያቀረቡት ቅሬታ ካሉበት ሁኔታ ወይም ካላቸው የአገልግሎት መስጫ ይዘት አኳያ ጥያቄ እያቀረቡ ነው በማለት ቅሬታቸውን ውድቅ አድርገዋል፡፡

ኤጀንሲው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የጥራት ቁጥጥር ሥራ ከሚያከናውንባቸው መስኮች አንዱ የሆነውን የጥራት መቆጣጠሪያ ሰነድ ከልሶና አሻሽሎ ማፅደቁን ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ትምህርት ቤቶቹ ለትምህርት ጥራት የተቀመጠውን መሥፈርት ሙሉ በሙሉ አሟሉ ተብለው እንዳልተጠየቁም ተናግረዋል፡፡ ዋቢ ያደረጉትና ብዙ ክርክር ያስነሳውም አንድ ለ20 የተባለው የመፀዳጃ አቅርቦትን ነው፡፡ ምንም እንኳ ደረጃው ይህንን ቢጠይቅም፣ ዝቅተኛውን አሟልተው እንዲገኙ ኤጀንሲው መጠየቁን ገልጸዋል፡፡

ተቋማት ወደ ደረጃው እንዲመጡ በሚፈለግት ወቅት ደረጃውን ወደ ተቋማቱ ነባራዊ ሁኔታ የመጎተት አዝማሚያ እንደሚታይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ‹‹ደረጃውን መጠበቅ ግድ ነው፡፡ የትምህርት ተቋማቱ በአገሪቱ ደረጃ ልክ መገኘት አለባቸው፤›› ያሉት ወ/ሮ ብሩክነሽ፣ የመሬት ጥያቄ የኤጀንሲው ኃላፊነት ባይሆንም፣ የትምህርት ቤቶች አንገብጋቢ ጥያቄ በመሆኑ ግን ለአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

ተማሪዎች እንደልባቸው የሚጫወቱባቸውና የሚንቀሳቀሱባቸው ክፍት ቦታዎች በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደማይታይ ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ከስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ ውጪ ተማሪዎች በዕረፍት ጊዜያቸው በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚናፈሱባቸው ቦታዎችን እንዲያዘጋጁ ኤጀንሲው ለትምህርት ቤቶቹ ጥያቄ ማቅረቡንም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች