Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ናይጄሪያ የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካን ትናፍቃለች

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ ሳቢያ ልታጣው ትችላለች 

በቻይናው ትራንዛሽን ሆልዲንግስ ግሩፕ ሥር የሚተዳደረው ቴክኖ ሞባይል በየጊዜው አዳዲስ ምርቶቹን በተለያዩ ከተሞች ውስጥ በሚያሰናዳቸው ዝግጅቶች አማካይነት ይፋ የማድረግ የኮርፖሬት ልማድ አለው፡፡ 

ኩባንያው እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ ሥራ ከጀመረ ወዲህ በአፍሪካ ያለው ተደራሽነት እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ከፍተኛ ተቀባይነት ባገኘበት የናይጄሪያ ገበያም በየዓመቱ አዳዲስ ምርቶቹን ይፋ ማድረግ ከጀመረ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዘንድሮም በቴክኖሎጂ የተራቀቀባቸውን አዳዲስ ሞዴሎች ይፋ ያደረገው በናይጄሪያዋ ሌጎስ ከተማ ነበር፡፡

ወትሮውንም ለቴክኖ ሞባይል ምርቶች ፍላጎት ያላቸው ናይጄሪያውያን ኩባንያው ይፋ ያደረጋቸውን ምርቶች ቀደም ብለው በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለማወቅ ሲጣጣሩ ታይቷል፡፡ ጋዜጦች ያፈተለከ ዜና እያሉ የሚዘግቡት አዳዲስ ሞዴሎቹ ይዘዋቸው ብቅ ያሉት ቴክኖሎጂ አብዛኛው መካከለኛ ገቢ ያለው ናይጄሪያዊ መግዛት የሚችላቸው፣ ለብዙ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችሉና ሌሎችም መመዘኛዎች የቴክኖ ሞባይል ስልኮችም ተመራጭ እንደሚያደርጓቸው ሲናገሩና ሲጽፉ ከርመዋል፡፡

የቴክኖ ሞባይል ምርቶችን በዚህ ደረጃ ሲያስተዋውቁ ከተደመጡት አንዱ ደግሞ የናይጄሪያ ኮሙዩኒኬሽንስ ሚኒስትሩ አብዱራሒም አዴባዮ ሺቱ ናቸው፡፡ የክብር እንግዳ ሆነው በታደሙበትና ሐሙስ መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በሌጎስ ከተማ አዳዲስ ምርቶች ይፋ በተደረጉበት መድረክ ነበር ይህንን የተናገሩት፡፡

ሚኒስትሩ የቴክኖ ብራንዶች በናይጄሪያ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ መሆኑን፣ በርካቶችም እንደሚጠቀሙበት ሲናገሩ አብረው የገለጹት የመንግሥታቸውንም አቋም ነበር፡፡ ‹‹እኛም ጋ መጥታችሁ ፋብሪካ ክፈቱ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ መንግሥት ቁርጠኛ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ነገሮችን አከናውኗል፡፡ በአገሪቱ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከነበረበት 3,500 ሜጋ ዋት ወደ 7,500 ሜጋ ዋት ከፍ አድርጓል፡፡ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታትም ወደ አሥር ሺሕ ሜጋ ዋት ከፍ ያደርገዋል፤›› በማለት የመንግሥታቸውን ለኢንቨስትመንት የተስማማ እንቅስቃሴ ማብራራቱን ገፉበት፡፡

እንደ ሚኒስትሩ አዴባዮ ሺቱ ማብራሪያ፣ ኢንቨስተሮች የሚጠይቋቸውን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች መንግሥታቸው በአፋጣኝ መመለስ ጀምሯል፡፡ የመንገድ፣ የባቡር ትራንስፖርት፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የቀረጥና የመሳሰሉት ላይ የሚታዩ ችግሮች ያለምንም ማቅማማት እንደሚፈቱና እየተፈቱ እንደሚገኙም አስታቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመንግሥታዊ ተቋማት በኩል የሚገጥሟቸውን ችግሮች እግር በእግር እየተከታተለ የሚፈታ መንግሥት በመሆኑ ሐሳብ አይግባችሁ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በዚህ አላበቁም፡፡ በናይጄሪያ ፋብሪካችሁን ትከሉ ለሚለው ጥያቄያቸው ኢትዮጵያን የነቀሱበትም አጋጣሚ ነበር፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ፋብሪካ እንዳላችሁ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እኛ ከኢትዮጵያ የበለጠ ገበያ አለን፡፡ የሕዝብ ቁጥራችን ከእነሱ [ከኢትዮጵያ] በእጥፍ ይበልጣል፡፡ የምርጫ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ይህ ሰፊ የገበያ ዕድል ነው፤›› በማለት ጥያቄያቸውን ለቻይኖቹ የቴክኖ ሞባይል ኃላፊዎች ሰንዝረዋል፡፡

የፋብሪካው መምጣት ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ወጪ መቀነስ ብቻም ሳይሆን፣ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚያስገኝ በመሆኑ ጥያቄያቸውን ረገጥ አድርገው ፋብሪካ በናይጄሪያ እንዲከፍት ቴክኖ ሞባይልን ጠይቀዋል፡፡ የቴክኖ ሞባይልም ሆነ የትራንዛሽን ሆልዲንግስ ኩባንያ ኃላፊዎች ፍላጎት እንዳላቸው በድፍኑ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ 

ሚኒስትሩ ብቻም ሳይሆኑ አብዛኞቹ ናይጄሪያውያን ቴክኖ ሞባይል በአገራቸው ፋብሪካ ቢከፍት አሁን ካስመዘገበው የሽያጭ ወሰን በላይ እንደሚያስደስታቸው ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡ በየገበያው ከሚሸጠው ባሻገር፣ በየኪዮስኩና በኤርፖርት አካባቢ ሳይቀር በርካቶቹ ናይጄሪያውያን በቻይናው ቴክኖ ሞባይል ምርቶች እምነት አድሮባቸዋል፡፡ በሰፊው ይጠቀሙበታል፡፡ ለምርጫቸውም ተመሳሳይ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ለአብዛኛው ሰው ኪስ ተመጣጣኝነቱን፣ ቶሎ አለመበላሸቱን፣ ባትሪ ቀይሩን አለማለቱንና ሌላም ሌላም የመለኪያ መሥፈርቶች ይቀርቡለታል፡፡

ቴክኖ ሞባይል በናይጄሪያ ከየትኛውም የአፍሪካ አገር ይልቅ የገበያ ድርሻ እንደያዘ ይታወቃል፡፡ የሳምሰንግና የአፕል ኩባንያዎችን በማስከተል ለአፍሪካ ገበያን ከሚመራባቸው አገሮች ግንባር ቀደሟም ናይጄሪያ ነች፡፡ ይህም ሆኖ በአፍሪካ ምርቶቹን የሚገጣጥምባቸው ፋብሪካዎች ያሉት ግን በኢትዮጵያ ነው፡፡ እንደ ናይጄሪያ ሁሉ ግብፃውያንም የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ በአገራቸው እንዲከፈት ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የግብፅ ጋዜጠኞችም ይህንኑ ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ ጥያቄ በማንሳትም የቴክኖ ሞባይል ኃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡበት ወትውተዋል፡፡

ፌሊክስ ሜንግ የቴክኖ ሞባይል ዓለም አቀፍ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ወቅት ያሉትን አምስት ማምረቻና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ጨምሮ ኩባንያው በሌሎችም አገሮች የመስፋፋት ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ አገሮች አንዷ ግብፅ እንምትሆንና ናይጄሪያም ታሳቢ እንደምትሆን ጠቅሰዋል፡፡ የታንሽን ሆልዲንግስ ምክትል ፕሬዚዳንት አንዲ ያን በበኩላቸው ኩባንያው የቴክኖ ሞባይል መዳረሻዎችን የመስፋፋት ዕቅድ በማውጣት አገሮችን እየቃኘ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ግብፅ ምናልባትም ኢትዮጵያን በመከተል ሁለተኛ በአፍሪካ የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካዎች መገኛ ሳትሆን እንደማትቀር ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጉዳይ

ቴክኖ ሞባይል በኢትዮጵያ የሚገጥሙት ችግሮች በናይጄሪያ አይገጥሙትም፡፡ በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ በናይጄሪያ የውጭ ምንዛሪ ችግር የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ ግን ምርቶቹን ገጣጥሞ ወደ ውጭ ለመላክም ቢሆን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ዳገት ከሆነበት ሰነባብቷል፡፡ በአንድ ወቅት በአገሪቱ በሚታየው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ከሦስት ወራት በላይ ምርት ለማቆም መገደዱን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ 

ይኸው የውጭ ምንዛሪ ችግር አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡ ቴክኖ ሞባይል በአሁኑ ወቅት ሁለት ሚሊዮን ስልኮችን በኢትዮጵያ ገጣጥሞ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ቢገነባም፣ ከአቅሙ በታች ለማምረት መገደዱን የኩባንያው ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ተስፋ የሚሰጣቸው ገበያ እንደሚታይም ጠቅሰዋል፡፡

ቴክኖ ሞባይል በኢትዮጵያ በሚገኙ ሦስት ፋብሪካዎቹ የሚገጣጠሙትን ስልኮች በብዛት ለአፍሪካ አገሮች የማቅረብ ፍላጎት ቢኖረውም፣ በገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ግን አብዛኛውን ምርት ከቻይና በማስመጣት ናይጄሪያን ጨምሮ ለሌሎች አገሮችም ለማቅረብ መገደዱን ገልጿል፡፡

በአንፃሩ ከማምረቻ ፋብሪካዎች ባሻገር፣ በናይጄሪያ ብቻም ሳይሆን በኬንያና በሌሎችም አገሮች ውስጥ የምርምርና የቴክኖሎጂ ማዕከላትም እየከፈተ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ የእነዚህ ተቋማት ተቋዳሽ አለመሆኗ ታውቋል፡፡ በናይጄሪያ ይፋ ያደረጋቸው ካሞን ኤክስና ካሞን ኤክስ ፕሮ የተሰኙት ስልኮች አዳዲስ የፊት ገጽታን በማንበብ ጭምር ማንነትን እንዲለዩ ተደርገው የተፈበረኩ ናቸው፡፡ ይህንን ቴክኖሎጂ ለማበልፀግ ደግሞ በኬንያና በናይጄሪያ የሚገኙት የገጽ ወይም የኢሜጅ ሴንሲንግ ጥናት ማዕከላት ትልቅ ሚና አበርክተዋል፡፡

ናይጄሪያ ችግሮቼን ፈትቼ፣ እጆቼን ዘርግቼ እቀበላችኋለሁ በምትልበት ወቅት ኢትዮጵያ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ለምትላቸው አምራቾች እንኳ ተፈላጊውን ማሟላት አልቻለችም፡፡ የአብዛኛው አምራች ጥያቄ የውጭ ምንዛሪ ያለህ ሆኗል፡፡ የመንግሥት ዕርምጃዎች ግን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ከመሆን ይልቅ ብዙዎችን የሚያስመርር ሆኗል፡፡

መንግሥት የቱንም ያህል ቢያደርግ ዕጥረቱን ሊቀርፍ አልቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ የመዘጋት አደጋ ያንዣበባቸው፣ ሥራ ለማቆም እየተገደዱ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ማየት የማይቀር ስለመሆኑ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የቴክኖ ሞባይል ኃላፊዎች በተቻላቸው አቅም በኢትዮጵያ ጥረው ብዙ አምርተው ለመሥራት እንደሚፈልጉ ከመግለጽ በቀር፣ የሚገጥማቸው ችግር ከቀጠለ አማላይ ጥያቄዎችን ወደሚያቀርቡላቸው አገሮች ጠቅልለው ስላለመሄዳቸው ዋስትና የለም፡፡

መንግሥት ግን እንዲህ ያለውን አደጋ የተገነዘበው አይመስልም፡፡ ቴክኖ ብቻውም ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይሁንና የሚገጣጥማቸውን ዕቃዎች ለማስገባት ግን የውጭ ምንዛሪ ወረፋ ለመጠበቅ ሲገደድ ይታያል፡፡ በዚያም ላይ የመንግሥት ተቋማት በሚያወጧቸው የግዥ ጨረታዎች ላይ የሚታዩ ግድፈቶች እንዳሉ፣ አገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች እያሉ ወደ ውጭ ሄዶ መግዛትና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማውጣት እንደሚታይ የኩባንያው ኢትዮጵያዊ ባለድርሻዎች በተለያዩ መድረኮች ሲገልጿቸው ከሚደመጡ ችግሮች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች