‹‹ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን የምታህል ታላቅ አገራችንን ከሚመራ ይልቅ የገዳዮች ስብስብ መሪ ይመስላል››
የአሜሪካና የእስልምና ግንኙነት ብሔራዊ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ኒሃድ አዋድ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንታዊ ዕጩነት ለመቅረብ የሚወዳደሩት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕን የወረፉት አዋድ፣ ትራምፕና መሰሎቻቸው በአሸባሪው አይኤስ መዳፍ ውስጥ ሆነው እየተጫወቱ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ሰሞኑን ትራምፕ በቅስቀሳ ንግግራቸው አንድም ሙስሊም የአሜሪካን ምድር መርገጥ የለበትም በማለታቸው ነው፡፡ አዋድ እንደሚሉት የትራምፕ ንግግር የሚያሳየው አሜሪካውያን እርስ በርስ እንዲባሉ አይኤስ የሚፈልገው አጀንዳ ነው፡፡ ‹‹እኛ አሁን በጦርነት ላይ ነን!›› የሚሉት አወዛጋቢው ትራምፕ ሙስሊሞች አሜሪካ እንዳይገቡ ቪዛ መከልከል አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህ አባባላቸው ዓለም አቀፍ ውግዘት አስከትሎባቸዋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሜክሲካውያንና አፍሪካውያንን በግልጽ ተሳድበዋል፡፡ በተለይ አፍሪካውያንን ሰነፎችና ምግብ ብቻ የሚወዱ በማለት ወርፈዋል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ለመሆን የሚወዳደሩት አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡