Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊልገሳ ላይ ያተኮረው ዲፕሎማቲክ ባዛር

ልገሳ ላይ ያተኮረው ዲፕሎማቲክ ባዛር

ቀን:

የቅጥሩ መግቢያ የተለያየ ዜግነት ባላቸው ሰዎች ተሞልቷል፡፡ የቲኬት መቁረጫው መስኮት ጋርም ረጅም ሠልፍ አለ፡፡ አንዳንዶች ፌስታል ሞልተው ከቅጥሩ ሲወጡም ይታያል፡፡ ተራ ደርሷቸው ትኬት ያገኙ ወደ አዳራሹ በጥድፊያ ይዘልቃሉ፡፡ ከአዳራሹ የተለያዩ አገሮች ባህላዊ ሙዚቃም ይስተጋባል፡፡ ቅዳሜ ኅዳር 25ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የዲፕሎማቲክ ባዛር የአገር ውስጥ ነጋዴዎችና በርካታ ኤምባሲዎች ተሳትፈዋል፡፡

በባዛሩ ልዩ ልዩ የመዋቢያ ግብአቶች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ምግብና መጠጥ እንዲሁም የተለያዩ ፈርኒቸሮችና ሌሎች የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ የዲፕሎማት የትዳር አጋሮች ነጋዴ በሆኑበት በዚህ ባዛር፣ የየአገራቸውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህል የሚያንፀባርቁ ቁሳቁሶች ሲሸጡ ውለዋል፡፡

በባዛሩ ተሳታፊ ከነበሩ ኤምባሲዎች መካከልም ከተቋቋመ ጥቂት ጊዜያት ያስቆጠረው የአዘርባጃን ኤምባሲ ይገኝበታል፡፡ ሻይ፣ ልዩ ልዩ ምግብና መጠጥ፣ ጌጣ ጌጦች፣ የጽሕፈት መሣሪያዎች የስልክ መያዣ ቦርሳዎች ኤምባሲው በዕለቱ ለሽያጭ ካቀረባቸው ዕቃዎች መካከል ናቸው፡፡ የአዘርባጃን ዲፕሎማትና ባለቤታቸውም በአጋጣሚው አገራቸውን ለማስተዋወቅ ሞክረዋል፡፡

‹‹ከጠዋት ጀምሮ ብዙ ዕቃዎች ሸጠናል፡፡ ምን ያህል መሸጥ እንደቻልኩ ሁሉ ለማየት ጊዜው አልነበረኝም፡፡ ሥራው ውጥር አርጎኛል፤›› ያሉት የአዘርባጃኑ ዲፕሎማት ባለቤት ሚስ ጊልኖ አብዱላሂራ ናቸው፡፡ በባዛሩ ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው ቢሆንም፣ ‹‹ነጋዴ መሆን ደስ ይላል፤›› ሲሉ ዝግጅቱ ያሳደረባቸውን ስሜትም ገልጸዋል፡፡ የአዘርባጃንን ባህል ከሚያንፀባርቁና በዓይነት ከቀረቡ ቁሶች ባሻገር ስለአገሪቱ ልዩ ልዩ መረጃዎች የሚሰጡ መጻሕፍት አዘጋጅተዋል፡፡ ‹‹አጋጣሚው ባህላችንን ከማስተዋወቅ ባሻገር ሌላም ጥቅም አለው፤›› የሚሉት ሚስ አብዱላሂራ፣ ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ ለልዩ ልዩ የአገር ውስጥ ተራድኦ ድርጅቶች እንደሚሰጥ፣ ይህም በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡

ባዛሩ ከተከፈተ ወራት ብቻ ያስቆጠረውን ኤምባሲያቸውን የሚያስተዋውቁበት በመሆኑ፣ ዲፕሎማቱን ጨምሮ ሌሎች የኤምባሲው ሠራተኞች አገራቸውን በማስተዋወቅ በሥራ ተጠምደው ውለዋል፡፡ ለሽያጭ የቀረቡ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ቅነሳ በማድረግና ያዘጋጇቸውን ባህላዊ ምግቦች ለሚጎበኟቸው ደንበኞች በማስቀመስ አርፍደዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው በዚህ ባዛር የተለያዩ የአገር ውስጥ ነጋዴዎችም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በብዛትም ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣ ጌጦችና የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች አቅርበዋል፡፡ የተለያዩ ተቋማትም ልዩ ልዩ ምርቶች ይዘው ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ሙዳይ የሕፃናትና የእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት አንዱ ነበር፡፡ ከ60 ብር ጀምሮ እስከ 400 ብር ድረስ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የሸክላ ውጤቶች፣ ከዘንባባ የተዘጋጁ እንደ ቅርጫት፣ መሶብና መጋረጃዎች ያሉ የቤት መገልገያዎች፣ እንዲሁም ባህላዊ የአንገት ልብሶች ለሽያጭ አቅርበዋል፡፡

‹‹ለሽያጭ ያቀረብነው የተረጂ እናቶች ያዘጋጁትን ዕቃዎች ነው፡፡ ሥራዎቻችንም ከሌሎቹ የተለዩ በመሆናቸው ደንበኞች ከሌላው በተሻለ ጎብኝተውናል፤›› የምትለው፣ ድርጅቱን ወክላ የተገኘችው ወጣት ኤልሳቤት ብርሃኔ ነች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ የድርጅቱ ምርቶች እዚያው በሚሠሩበት ግቢ ውስጥ ይሸጣል፡፡ ከዚህ ቀደምም በባዛር ተሳትፈው አያውቁም፡፡ በዲፕሎማቲክ ባዛር ሲሳተፉም የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ሰፊ ገበያም ፈጥሮላቸዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም በዓመት አንዴ ብቻ ከሚሆን በየሁለትና ሦስት ወሩ ቢሆን ይመረጣል፤›› ትላለች፡፡

ወ/ሮ ዮርዳኖስ ኃይሌ የባዛሩ አዘጋጅ የፌስቲቭ ኤቨንት ባልደረባ ባዛሩ ለሃያኛ ጊዜ መዘጋጀቱን ትናገራለች፡፡ እሷ እንደትምለው፣ ዝግጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ‹‹የዲፕሎማቶች ባለቤቶች ተሰብስበው ለሕፃናት፣ እናቶች እንዲሁም ለሌሎች ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች የሚያዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ነው፤›› ብላለች፡፡

60 ኤምባሲዎችና 20 የሚሆኑ የፕሮግራሙ ስፖንሰሮች ከተሳተፉበት ባዛር የሚገኘው ገቢ፣ 20 ለሚሆኑ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ተቋማት እንደሚከፋፈል ወ/ሮ ዮርዳኖስ ተናግራለች፡፡ በየዓመቱ 10,000 የሚሆኑ ሰዎች እንደሚጎበኙት በሚነገርለት ባዛሩ፣ ባለፈው ዓመት 3 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ በዚህኛው ባዛርም ከዚህ በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ወ/ሮ ዮርዳኖስ ታስረዳለች፡፡  

እንደ ወ/ሮ ዮርዳኖስ፣ ድጋፍ የሚደረግላቸው ግብረ ሰናይ ተቋማት ስለድርጅታቸው አጠቃላይ ሁኔታና የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለባዛሩ አዘጋጅ አካል በጽሑፍ የሚያስገቡ ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፉ ማመልከቻቸውን መሠረት በማድረግ ለተመረጡ ተቋማት የሚደረግ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...