Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልልማትና የጥብቅ ቦታዎች ሕልውና

ልማትና የጥብቅ ቦታዎች ሕልውና

ቀን:

የ75 ዓመቱ አዛውንት አቶ ዘውዴ ጎዱ በሸካ ዞን የጎሳ መሪ ናቸው፡፡ በትውልድ ቀያቸው ባህላዊ የእምነት ሥርዓቶች የሚካሄዱባቸው ብዙ ሥፍራዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ ከመጡት የተከበሩ ተፈጥሯዊ ጥብቅ ቦታዎች መሀከል ጉዶና ደዶ በመባል የሚታወቁት ቦታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውና ጥበቃ የሚደረግላቸው ደኖች፣ ዋሻዎች፣ ተራራዎች፣ ወንዞች እንዲሁም ረግረጋማ ቦታዎችም አሉ፡፡

በደኖቹ የሰብል መሰብሰብን ምክንያት በማድረግና ሌሎችም የማኅበረሰቡን የእለት ከእለት ሕይወት የተመረኮዙ ሁነቶችን በማስመልከት በተወሰነ ጊዜ ልዩነት በደኑ ውስጥ የሚካሄድ የእምነት ሥርዓት አለ፡፡ ደኖቹ የተጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ፣ ፈጣሪን ለመለመንና ለሌሎችም ሒደቶች የተመረጡ ናቸው፡፡ አቶ ዘውዴ እንደሚሉት ግን ደኖቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑ መጥተዋል፡፡

ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩት ደኖች እየተመነጠሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት ዛፎቹ ቢጨፈጨፉም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥጋት የሆነባቸው ደኖቹ ተመንጥረው ለሻይቅጠልና ሌሎችም ተክሎች ኢንቨስትመንት እየዋሉ መሆኑ ነው፡፡ የጎሳ መሪው፣ የደኖቹ አለመጠበቅ ከሚያስከትለው የአየር መዛባት ባሻገር የአካባቢው ማኅበረሰብ እምነትና ባህል እያደር መሸርሸሩ አሳሳቢ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

እንደ አንድ የጎሳ መሪ የአካባቢው ማኅበረሰብ ትውፊቱን ይዞ እንዲዘልቅና  የተፈጥሮ ሀብቱም እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረው፣ አሁን ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም በአካባቢው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ካልቆመ ችግሩ እንደሚባባስ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ባህልና ሥርዓቱ የሚጠበቀው አካባቢው ተጠብቆ ሲቆይ ነውና ኅብረተሰቡም መንግሥትም የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡

በሸካ ዞን እንደሚገኙት ሁሉ የተከበሩ ተፈጥሯአዊ ጥብቅ ቦታዎች (ሳክርድ ናቹራል ሳይትስ) በሌሎች አካባቢዎችም ይገኛሉ፡፡ እንደየአካባቢው የሚለያይ የእምነት ሥርዓት የሚካሄድባቸው ሲሆን፣ ማኅበረሰቡም ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ለአደጋ የሚጋለጡትበት አጋጣሚም ይፈጠራል፡፡ ባሌ በሚገኘው ዲንሾ ወረዳ የሚኖሩት የ71 ዓመቱ አርሶ አደር አቶ አዳ ሁሴን በአካባቢያቸው ስላለ ጥብቅ ቦታ ይናገራሉ፡፡

በዋነኛነት እርቀ ሰላም ለማውረድና የአካባቢው አርሶ አደር የዘራው እንዲበቅል የሚለማመኑበት ጥቅጥቅ ደን አለ፡፡ ደኑ ለዘመናት ተጠብቆ ሲቆይ ለዱር እንስሳትም ምቹ መኖሪያ ሆኖ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ሰዎች ዛፉን መቁረጥ ይጀምራሉ፡፡ የተፈጥሮ ሀብቱ መመናመን ያሳሰባቸው የአካባቢው ሽማግሌዎች ነዋሪዎችን በማስተባበር ደኑን ከልለው ጥበቃ እንዲደረግ ያሳስባሉ፡፡ አሁን ተፈጥሮው ወዳለበት እንዲመለስና በአካባቢው የሚካሄደው ሥርዓትም እንዳይስተጓጎል እየተጣጣሩ እንደሆነም አርሶ አደሩ ያስረዳሉ፡፡

ሁለቱ አዛውንቶች ከተለያየ አካባቢ ቢመጡም የየትውልድ ቀያቸውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ ዘመናትን ያስቆጠሩ የየአካባቢያቸው እሴቶች እንዳይሸረሸሩ የተከበሩ ተፈጥሯዊ ቦታዎችን መጠበቅ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ባህላቸውን፣ እምነታቸውንና፣ ተፈጥሯቸውን አደጋ ላይ ለጣሉት ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ ባለፈው ሳምንት በጅማ ከተማ ተሰባስበው ነበር፡፡ እንደ ሁለቱ አዛውንት ሁሉ ከሸካና ከባሌ ከተውጣጡ የጎሳ መሪዎች በተጨማሪ፣ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች በጉዳዩ ላይ መክረዋል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆነው የተራድኦ ድርጅት መልካ ኢትዮጵያ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች አጠባበቅ›› በሚል ርዕስ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የሁለት ቀናት ጉባዔ ስለተከበሩ የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎች አያያዝ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ጥብቅ ቦታዎችን አደጋ ላይ ጥለዋል ያሏቸውን ገልጸው፣ በዘርፉ ካሉ ባለድርሻ ተቋሞች የሚጠበቁ እርምጃዎችን ጠቁመዋል፡፡

ቦታዎቹን ለአደጋ አጋልጠዋል ከተባሉት አንዱ ሕገወጥ ሠፈራ ነው፡፡ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ደኖችን በመጨፍጨፍ ለመኖሪያ ቤት ግንባታና ሌሎችም አገልግሎቶች የሚያውሉ ጥቂት አይደሉም፡፡ የተከበሩ የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎች አስተዳደር ወጥና ተጠያቂነት ያለው አለመሆኑ ለሥፍራዎቹ መደበኛ ጥበቃ እንዳይደረግላቸው እንቅፋት እንደሆነ የተናገሩ ነበሩ፡፡ ለዘመናት አካባቢዎቹ እንዲጠበቁ ያደረጉት የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ሲሆኑ፣ በእነሱና በአዲሱ ትውልድ መካከል ያለው ክፍተት ቦታዎቹን ለአደጋ አጋልጧል ሲሉ አስተያየት የሰነዘሩም ነበሩ፡፡

ዘመናዊው ትምህርት ለአገር በቀል እውቀቶች ቦታ አለመስጠቱ በእነዚህ ጥብቅ ቦታዎች ያለው እውቀት ትኩረት እንዳይሰጠውና ደኅንነታቸው ቸል እንዲባል ክፍተት ፈጥሯል፡፡ ለቦታዎቹ የሚሰጠው ግምት አነስተኛ በመሆኑ አደጋ ሲደርስባቸው አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኝነት ያለው አካል ውስን የሚል ሐሳብ የሰጡም ነበሩ፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች የሚካሄዱ የእምነት ሥርዓቶችን የማይበቀሉ ሃይማኖቶች መስፋፋታቸውም  እንደ አንድ ነጥብ ተጠቅሷል፡፡

የጎሳ መሪዎቹ፣ የአገር ሽማግሌዎቹና የዘርፉ ባለሙያዎች እንደ መፍትሄ ካስቀመጧቸው ነጥቦች አንዱ መንግሥት ለቦታዎቹ ትኩረት መስጠት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የሃይማኖት መቻቻል ረገድ አገሪቱ ያወጣቻቸው ሕግጋት እንዲጠበቁ ያሳሰቡም ነበሩ፡፡ መንግሥት አማራጭ ኃይል አመንጪዎችን በማዘጋጀትና በሌሎችም መንገዶች የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል አለበት፡፡ ለኢንቨስትመንትና ልዩ ልዩ ክንውኖች የሚውሉ ቦታዎች ሲመረጡ በአንድ አካባቢ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተፅዕኖ ከግምት ገብቶ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት የተናገሩ የጉባኤው ተሳታፊዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በጉባኤው የትምህርት ተቋሞችና ማኅበረሰቡም አገር በቀል እውቀትና ባህላዊ እሴቶችን አስጠብቆ ከትውልድ ትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡ ተቋሞች ስለ አካባቢዎቹ በማጥናት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ እንደሚገባቸው የተናገሩም ነበሩ፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞችም  ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግና የመፍትሄ አቅጣጫ በማመላከት  መሳተፍ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

የውይይቱ አዘጋጅ መልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚሊዮን በላይ በውይይቱ ባቀረቡት ጥናት፣ የተከበሩ የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎች የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ፣ አገር በቀል ዝርያዎችን ለማከማቸት፣ የኅብረተሰቡን እሴቶች ለመጠበቅና በማኅበረሰቡ መካከል ትስስር ለመፍጠር ያላቸውን ሚና ገልጸዋል፡፡ ለታሪክ ጥናትና የአገር በቀል እውቀቶች ምርምር መነሻ ይሆናሉ፡፡ ለእንስሳት መኖሪያነት፣ ባህላዊ መድሐኒቶችን ለማግኘት፣ የኅብረተሰቡን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅም ይጠቅማሉ፡፡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ተፈጥሮአዊ ፋይዳም አጣምረው ይይዛሉ፡፡ ‹‹ቦታዎቹ ከማኅበረሰቡ ባለፈ አገራዊ ጠቀሜታ አላቸው፤ ባህልና ዘላቂ ልማትን ለማስተሳሰር የቦታዎቹ መጠበቅ የግድ ነው፤›› ይላሉ ዶ/ር ሚሊዮን

አካባቢዎቹ ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ፣ አካባቢዎቹን በሚመለከት መንግሥት በሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች የሕዝቡ ተሳትፎ እንደሚያሻና አገር በቀል እውቀቶች ከዘመን አመጣሽ እውቀት ጋር የሚጣመሩበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበሩ የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎችን ለማስጠበቅ ስለወጡ ሕግጋት የተናገሩት አቶ መርሻ ይልማ፣ በአገሪቱ ሥፍራዎቹን በቀጥታ የሚያስጠብቅ ሕግ እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ የሕዝቦችን ባህል፣ የእምነት ነፃነትና የተፈጥሮ ሀብትን የሚያስጠብቁ ሕጎች መኖራቸውን አጣቅሰው፣ ቦታዎቹ እነዚህን ባጠቃላይ ያጣመሩ በመሆናቸው መንግሥትና ኅብረተሰቡ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ያስገድዳሉ ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው አስገዳጅ የሆኑና ያልሆኑም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ለሀብቱ ጥበቃ ያስፈልጋሉ ያሉት አቶ መርሻ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎች የሚተገበሩበት አጋጣሚ ውስን እንደሆነና በተግባር ካልዋሉ ሕግጋቱ መኖራቸው ብቻ ትርጉም እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡ በዓለም ላይ ከ150,000 በላይ ጥብቅ ቦታዎች እንዳሉም ጥናታቸው ያሳያል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና ባህል እሴት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ሹመንካ ጥብቅ ቦታዎች ከማበልጸግ ይልቅ የመጥፋት አደጋ እንዳንዣበባቸው ይስማሙበታል፡፡ ከልማት ጋር በተያያዘ ቦታዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉበት ጊዜ እንዳለ አስረድተው፣ ‹‹ልማት ለአገር ዕድገት አስተዋፅኦ ቢኖረውም ጥብቅ ቦታዎቹ ሲሰጡ መታሰብ አለበት፡፡ በውስጣቸው የያዙት እምቅ ሀብት ተጠብቆ ትልቅ ሀብት ሊያስገኝ ይችላል፣›› ይላሉ፡፡ በቦታዎቹ የሚከናወኑ ትውፊታዊ ሥርዓቶች ለአካባቢ ጥበቃ ሚና ቢኖራቸውም እምነቶቹን የሚያጣጥሉ ግለሰቦች እንዳሉ አስረድተው፣ ‹‹የተፈጥሮና የባህል ሀብትን ጠብቀው ከዘመን ዘመን ያሸጋገሩ ስለሆኑ ሊጠበቁ ይገባል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

የቦታዎቹ መጥፋት ከሚፈጥረው የባህል መሸርሸር ባሻገር ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባት ስለሚያጋልጥም ጥበቃው መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በመንግሥት በኩል ያሉ ባለድርሻ ተቋሞች እስካሁን ስለ ወሰዷቸው እርምጃዎች የተጠየቁት አቶ አውላቸው እንደሚሉት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ባህላዊ እውቀትን ለመጠበቅ ባለው ኃላፊነት የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም በቂ አይደሉም፡፡ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለቦታዎቹ ጥበቃ በማድረግ ረገድ ብዙ እንደሚጠበቅባቸው ይገልጻሉ፡፡

መሥሪያ ቤቱ በሙሉ ኃይሉ እንዳይንቀሳቀስ ያደረጉ ያልተመለሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች መኖራቸው እንደሆነ ጠቁመው፣ በቀጣይ የያዟቸው ዕቅዶች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሌሎች የመንግሥት ተቋሞች ጋር ተጣምረው በመሥራት ረገድ ጅማሮ ላይ መሆናቸውንም ያክላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...