በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር በምሥራቅ በለሳ ወረዳ ጠርጣሮ ቀበሌ በመኪና እየመጣ የሚታደለውን ውኃ ለመቋደስ ታዳጊዎችና እናቶች ከሁለት ሰዓት ያላነሰ የእግር ጉዞ አድርገው ከቦታው ይደርሳሉ፡፡ ዕድል የቀናው በጀሪካን የሚሰጠውን ውኃ አግኝቶ የሚመለስ ሲሆን፣ ዕድል ፊቷን ያዘረችበት ባዶ ጀሪካኑን ይዞ ይመለሳል፡፡ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ከድርቁ ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ የውኃ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ ችግሩን ለማቃለል የሚመለከታቸው አካላት ውኃ በመኪና እየጫኑ የሚያድሉ ቢሆንም፣ በቂ ውኃ ስለማይዙ ነዋሪዎቹ ሊዳረሳቸው አይችልም፡፡
*****
የሚታጠብ ስማርት ፎን
ስልካቸውን እያጠቡ ፅዱ ማድረግ ለሚፈልጉ የጃፓን ስልክ አምራች ኩባንያዎች መፍትሔ አለን ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ቀደም ሲል ውኃ የሚቋቋም ስልክ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ገበያ ላይ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም KDDI የተሰኘው የጃፓን ኩባንያ በውኃና በሳሙና በደንብ ሊታጠብ የሚችል ያለውን ስማርት ፎን በዚህ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ የካምፓኒው ቃል አቀባይ ለአጃንድ ፍራንስ ፕሬስ ‹‹ጥንካሬውን ለማወቅ ስማርት ፎኑን 700 ጊዜ አጥበነዋል፤›› ብለዋል፡፡ ካምፓኒው እንዳስታወቀው በተለይም ልጆቻቸው በስልካቸው ለሚጫወቱ ወላጆች ይህ ስልክ ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የስልኩ ዋጋ 175 ዶላር እንደሆነ ያስታወቀው ካምፓኒው ስልኩ መታጠብ የሚችለው በማንኛውም ዓይነት ሳሙና ሳይሆን ጃፓን ውስጥ ብቻ በሚሸጡ የተወሰኑ ሳሙናዎች እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
*****
ጠፍታ ከስምንት ዓመታት በኋላ የተገኘችው ድመት
ካሊፎርኒያ ውስጥ ከአሳዳሪዎቿ ለስምንት ዓመታት ጠፍታ የነበረች ድመት መገኘቷን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ድመቷ በመጨረሻ ልትገኝ የቻለችው እንደጠፋች ወዲያው ያገኛት ሰው የእንስሳት ማቆያ ውስጥ እንድትገባ በማድረጉ ነው፡፡
ዘገባው እንደሚያሳየው ድመቷ ልትገኝ የቻለችው ማይክሮቺፕ ተደርጎባት ስለነበር መጠለያው በዚያ አማካይነት አሳዳሪዎቿን ፈልጎ ማግኘት በመቻሉ ነው፡፡ የመጠለያው ቃል አቀባይ ሊዛ ቦልች የጠፉ እንስሳትን ከአሳዳሪዎቻቸው በማገናኘት የመጠለያው ታሪክ ይህች ለስምንት ዓመታት ጠፍታ የነበረችን ድመት ከአሳዳሪዎቿ ማገናኘት የመጀመሪያው ሪከርድስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
*****
ትዕይንት ላይ በስህተት በጥይት የተመታው ሰው
በአሪዞና ፎኒክስ የጦር መሣሪያ ኤግዚቢሽን ላይ ለመታደም የተገኘ ግለሰብ እዚያው ለዕይታ ቀርቦ በነበረ ሽጉጥ መመታቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የአሪዞና የኅብረተሰብ ደኅንነት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ራውል ጋርሺያ ግለሰቡ የተመታው ጓደኛው እያገላበጠ ያይ በነበረው ሽጉጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጉዳቱ የግለሰቡን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
እንደዚህ ያሉ ትዕይንቶች ላይ ጥይት የጎረሱ መሣሪያዎችን ማስገባት የሚፈቀድ ባለመሆኑ ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ጥያቄ ሆኗል፡፡ የኅብረተሰብ ደኅንነት ዲፓርትመንት ቃል አቀባዩ ጋርሽያም ሽጉጡን የተኮሰው ሰው ላይ ክስ ይመሥረት አይመሥረት ምንም የሚታወቅ ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡