Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ሥራ ስላልተለመዱ ተቸግረን ነበር››

አቶ ሱልጣን ቃሲም፣ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ኮሌጅ የማኅበራዊ ፍትሕ ማዕከል ኃላፊ፣ የፍትሕ ተደራሽነትና ንቃተ ሕግ ፕሮጀክት ዳይሬክተር

የአንጋፋው ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ኮሌጅ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ኮሌጁ ከጥቂት ቀናት በፊት ይህን አገልግሎት ምክንያት በማድረግ ጋዜጠኞች ሁለገብ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጋብዞ ነበር፡፡ ኮሌጁ የሚሰጠውን ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎና ተደራሽነትን በሚመለከት የኮሌጁ የማኅበራዊ ፍትሕ ማዕከል ኃላፊ፣ የፍትሕ ተደራሽነትና ንቃተ ሕግ ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን ቃሲም ጋር ታምራት ጌታቸው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ነፃ የሕግ አገልግሎት እንዴት ተጀመረ?

አቶ ሱልጣን፡- ዩኒቨርሲቲዎች በመማር ማስተማሩ ሒደት ሦስት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንደኛው ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን ማድረግ ሁለተኛው ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው ሕግ መሠረት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚሰጠው ትምህርት በተጨማሪ በየፋብሪካዎችና በተለያዩ ተቋማት የተግባር ትምህርት መውሰድ አለባቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ማገልገል አለበት የሚለው ነው፡፡ እነዚህን መነሻ በማድረግ ነው ዩኒቨርሲቲው ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ነፃ የሕግ  አገልግሎት መስጠት የጀመረው፡፡ አገልግሎቱን የጀመረው ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን፣ በሐሮማያና በሐረር ከተማ ሁለት ቢሮዎችን በመክፈት ነበር፡፡ ይህ ፕሮጀክት  መቀጥል እንዳለበት ስለታመነ ተማሪዎችም በነፃ የሕግ አገልግሎቱ እንዲሳተፉ ተደረገ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት በግብርናው እንጂ በሕግ በኩል ብዙ ሠርቶ ስለማያውቅ ይህንንን ልምድ ለማስቀጠል ከፍትሕ ሴክተሩ ጋር ሥራውን እያዳበረ ሲመጣ፣  አገልግሎቱን የሚፈልገው ማኅበረሰብም በየጊዜው እየጨመረ ሲሄድ ዩኒቨርሲቲው እንደ አዲስ በ2006 ዓ.ም. 11 አዳዲስ ቢሮዎችን በተለያዩ ወረዳዎች በመክፈት የነፃ የሕግ አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ እንቅስቃሴው በሁሉም መልክ እየሰፋ በመምጣቱ ከጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀጠለ ሆኖ እንደገና በሁሉም ወረዳ ቢሮ መክፈት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ዩኒቨርሲቲያችን ከተለያዩ የፍትሕ አካላትና ከዩኤስኤአይዲ (USAID) ባገኘነው የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ 43 ቢሮዎችን ለመክፈት ችለናል፡፡ ከነዚህ ቢሮዎችም  በቋሚነት በሕግ ሙያ የተማሩ፣ ዲግሪ ያላቸውና ልምድ ያላቸውን ቀጥረን እያሠራን ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ተማሪዎቻችን የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉና በዚያውም ማኅበራዊ ኃላፊነት እንዲሰማቸውና ይህንንም በደንብ እንዲያጠነክሩ የምናደርግበት ሦስት የሕግ ክሊኒክ ብለን የምንጠራቸው አሉን፡፡ እነዚህ በሐሮማያ፣ በአወዳይና  ሐረር  ይገኛሉ፡፡ በነዚህም ክሊኒኮች 60 የሚሆኑ ተማሪዎች ተራ በመግባት በተለይ ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞች ላይ  ይሠራሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- አገልግሎቱ ምን ያህል ተደራሽ ነው?

አቶ ሱልጣን፡- አገልግሎቱን በሁሉም ወረዳዎች እየሰጠን ነው፡፡ በምዕራብና በምሥራቅ ሐረርጌ፣ 33 ሚሆኑ ቢሮዎች ሲኖሩ ከዚያ በተጨማሪ ሁለቱ ዞኖች ላይ ሁለት ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ቢሮዎች አሉን፡፡ በሐረር ደግሞ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉን፡፡ በተመሳሳይ ሰባት በሚሆኑ  ማረሚያ ቤቶችም አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ ምን ምን ይጨምራል?

አቶ ሱልጣን፡- አገልግሎቶቹ ወደ አምስት ይሆናሉ፡፡ የመጀመርያው የሕግ የምክር አገልግሎት ነው፡፡ ሁለተኛው ማመልከቻዎችንና የመልስ ክሶችን በአግባቡ የምንሰጥበት ሲሆን፣ ትልቁና ሦስተኛው ሥራችን የውክልና ሥራ ነው፡፡ ውክልና ወስዶ አቅመ ደካሞችን ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ወስዶ ፍትሕ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ አራተኛው በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ታራሚዎችን ማረሚያ ቤት ድረስ በመሄድ ከማረሚያ ቤቱና ከፖሊስ ጋር በመሆን ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት በማቅረብና መከታተል ፍትሕ እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡ የመጨረሻውና አስምተኛው ደግሞ የንቃተ ሕግ (ግንዛቤ ማስጨበጥ) ላይ የምንሠራው ነው፡፡ የንቃተ ሕግ ሥራውን የምንሠራው በሁለት ከፍለን ነው፡፡ የመጀመርያው  ሠራተኞቻችን ወደ ፍርድ ቤት በሚሄዱበት ጊዜ ጠዋትና  ለ30 ደቂቃ ትምህርት ይሰጣሉ ይህንንም ከፍርድ ቤቱ ጋር በመምከር የትኛው ጉዳይ ላይ ትምህርት ቢሰጥ ይሻላል? እያሉ በዕቅድ እየተዘጋጀ የሚሰጥ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የራሱ የሆነ ማኅበረሰብ FM ሬዲዮ ስላለው በሕግ ሙያ ልምድ ያላቸውን ቀጥረን በሳምንት ሁለት ጊዜ በአማርኛና በኦሮምኛ የሚተላለፍ ፕሮግራም አለን፡፡ ፕሮግራሙን ማስተላለፍ ከጀመርንበት ከ2006 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2008 ዓ.ም. ድረስ 336 ሺሕ ለሚሆኑ አገልግሎቱን ስጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡-  ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ የሰጣችሁት የሕግ አገልግሎት በብር ምን ያህል ይሆናል?

አቶ ሱልጣን፡- 80.6 ሚሊዮን ብር ያወጣል፡፡ ይህ የሕግ ግንዛቤ ማስጨበጫን አይጨምርም፡፡ ለምሳሌ የቃል ምክርን የገመትነው ገበያ ላይ ባለው የመጨረሻ ዝቅተኛ ዋጋ ነው፡፡ የቃል ምክሩ ከ50 እስከ 70 ብር ነው፡፡ ማመልከቻ የሚጻፈው እስከ 200 ብር ብለን ወሰድን፡፡ ገበያ ላይ ግን ከዚህ በላይ ነው፡፡ ከውክልና ፍርድ ቤት ቆሞ መከራከር እስከ 10,000 ሺሕ ብር ይገመታል፡፡ እንደዚህ እንደዚህ እያልን ገበያ ላይ ካለው ዝቅተኛውን ዋጋ ወስደን ነው ያሰላነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምትሰጡት አጠቃላይ አገልግሎት ምን ያህል ባለሙያዎች ተሳታፊዎች ናቸው?

አቶ ሱልጣን፡- በቋሚነት ነፃ የሕግ አገልግሎት የሚሰጡ 43 ሠራተኞች አሉ፡፡ ሁሉም የሕግ ዲግሪና ልምድ ያላቸው ናቸው ከዚያ በተጨማሪ የሕግ ክልኒክ ላይ የሚሠሩ 60 ተማሪዎች አሉን፡፡ እነዚህም ሦስተኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ሲሆኑ በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ፣ ውጤታቸውም ጥሩ የሆነ ተማሪች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ሁለት መምህራን በቋሚነት ተመድበው ተማሪዎችን እያስተባበሩ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ በሌላ በኩል የፍትሕ አካላት ከሚባሉ ጋር ሁሉ እንሠራለን በዋናነት ግን ከዩኒቨርሲቲያችን ሲሆን፣ የኦሮሚያና የሐረር የፍትሕ ቢሮዎች ጥበቃና ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ አብረውን እየሠሩ ነው፡፡ በየዓመቱ ፍቃድ በነፃ ነው የሚያድሱልን ሴቶችና ሕፃናት ቢሮም እገዛ ያደርጉልናል፡፡ ፖሊስና ማረሚያ ቤቶችም ሥራቸውን እንዳቀለልንላቸው ይገልጹልናል፡፡

ሪፖርተር፡-  በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ በእንቅስቃሴያችሁ የተለያዩ ችግሮችን ዓይተናል፡፡ ያጋጠማችሁ ችግር ምንድ ነው?

አቶ ሱልጣን፡- ችግሩ የሚጀምረው የሰው ኃይል ከማግኘት ነው፡፡ በዲግሪ ደረጃ በሕግ የተማረ በገጠር ማግኘት ችግር ነው፡፡ ወደፊት የተገልጋዩ ቁጥር እየበዛ ሲሄድ በጥቂት   ሰው ብቻ ማሠራቱ ውስንነት ይኖረዋል፡፡ ተጨማሪ የሰው ኃይል የሚቀጠርበትን መንገድ እየፈለግን እንገኛለን፡፡ አገልግሎቱ በሙሉ የሚሰጠው ገጠር ወረዳዎች ላይ ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ሊሟሉ የሚገባቸውን አሟልተናል፡፡ የእያንዳንዱ ወረዳ ቢሮ ኮምፒውተር አለው ግን ይህንንም መጠቀም በኤሌክትሪክ ምክንያት አልቻልንም፡፡ ለዚህም መፍትሔ ብለን በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ሌሎቹም እንዲጠቀሙ እያደረግን ነው፡፡ ቢሆንም ችግር አለ፡፡ መጀመርያ ላይ ስለ አገልግሎቱ ምንነት ተቋማቱ ኅብረተሰቡም ምንም ግንዛቤ አልነበራቸውም፡፡ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ሥራ  ስላልተለመዱ ተቸግረን ነበር፡፡ ከተከላካይ ጠበቆችም ችግር ገጥሞን ነበር፡፡ ዓላማችንን በግልጹ በማስቀመጥና ብዙ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ቀስ በቀስ አገልግሎቱን ሲመለከቱት ሁሉም መተባበር ጀመሩ፡፡ ኅብረተሰቡም አገልግሎቱን የትና እንዴት እንደሚሰጥ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ ይህም ትልቅ ችግር ነበር፡፡ ይህንንም ከቀበሌና ከሌሎች ጋር በመነጋገርና በማስተማር እንዲሁም አገልግሎቱን ያገኙት ሰዎች ለኅብረተሰቡ ሲያስረዱ ሰዎች አሁን በቀላሉ አገልግሎት እንዴት እንደሚገኝ ማወቅ ችለዋል፡፡ ሌላው ፈተና ሆኖ የነበረውና በእኛ በኩል መፍትሔ ያገኘው የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ የጥብቅና ፈቃድ ለተቋሞች አይሰጥም ነበር፡፡ የመንግሥት ነገረ ፈጅ ከሆነ  ፈቃድ መውሰድ ይቻላል ወይም ደግሞ የተገልጋዩ ዘመድ መሆን ብሎ ያስቀምጣል ሕጉ፡፡ የእኛ አገልግሎት ደግሞ በነዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አይወድቅም ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ብቻ ብዙ ችግር ነበር፡፡ ይህንንም ችግር ጉዳዩ  ጨፌ ኦሮሚያ ላይ እንዲቀርብ አድርገን ሕግ እንዲሻሻል አድርገን ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ልዩ የጥብቅና ፈቃድ እንዲኖራቸው በማስቻል ሥራውን ልንቀጥል ችለናል፡፡ በሐረርም እንደዚሁ ፈቃድ ተሰጥቶናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፕሮጀክቱ ብዙዎች ተጠቅመዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ለአገልግሎቱ ትልቅ ግምት እንደሚሰጥ አስተውለናል፡፡ ለወደፊቱ ምን ለማድረግ አስባችኋል?

አቶ ሱልጣን፡- በቀጣይ የአገልግሎቱ ዕድገት ላይ ትልቅ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ መጀመርያ ግን ቀጣይነቱን ከማረጋገጥ አንፃር የአገር ውስጥ ሀብትን ለመጠቀም ነው ያሰብነው፡፡ በገንዘበም ይሁን በቁሳቁስ ትኩረት ያደርግነው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ቢሮዎችን በነፃ ካገኘን የቢሮ ዕቃዎችን ደግሞ እኛ እያቀረብን በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲውን ንብረት በተለያየ መልኩ እያስፈቀድን በመጠቀም፣ እንዲሁም ከወዲሁ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ አጋር ድርጅቶችን በመጠየቅ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ አሁን ዩኒቨርሲቲው ቢሮ ማዘጋጀት ባልቻሉ አካባቢዎች  ወደ 400 ሺሕ ብር አውጥቶ ቢሮ ገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስለዚህ መጀመርያ የአገር ውስጥ ሀብትን መጠቀም ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕገ መንግሥቱም የፍትሕ ተደራሽነት በመንግሥት ላይ ነው ይላል፡፡ በተለይም አቅም ለሌላቸው አገልግሎቱን ማግኘት ለማይችሉት በራሱ ወጪ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚያ ውጭ ይህ የዩኒቨርስቲው ኃላፊነትም ስለሆነ ትምህርት ሚኒስቴርም በዚሁ አቅጣጫ ትኩረት ሰጥቶ ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሠሩ ማድረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተማረና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጥ ያለው እዚህ አካባቢ ነውና ነው፡፡ አሁን ዩኒቨርሲቲዎች በየቦታው ስለሚገኙ ከፍትሕ አካላት ጋር በመሆን መሥራት ይቻላል፡፡ ይህ የነፃ የፍትሕ አገልግሎት ፖሊሲ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥቶለት በባለቤትነት የሚያስተዳድረው አካል ተቋቁሞ እንደማንኛውም የመንግሥት ሥራ እንዲሆን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ይህ አሁን የያዝነው ፕሮጀክት የሚያበቃው እ.ኤ.አ. በ2017 ሲሆን፣ ከወዲሁ ግን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን የሚቀጥልበትን መንገድ እያመቻቸን ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን በዩኒቨርስቲያችሁ የተካሄደው የተማሪዎች ተቃውሞ በመማር ማስተማሩ ላይ ችግር አልፈጠረም?

አቶ ሱልጣን፡- ግርግር በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲፈጠር ቀስ እያለ ነው የሚረጋጋው፡፡ ስለዚህ ሁኔታው አሁን እየተረጋጋ ነው፡፡ እኛም ኃላፊነት ስላለብን ክፍል እየገባን አንድም ይሁን ሁለት ያለውን ተማሪ እያስተማርን ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የተማሪው ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ሱልጣን፡- በተማሪው በኩል አሁንም ተረጋግቶ ያለመማር ነገር አለ፡፡ ካሁን አሁን ረብሻ ይነሳል ፖሊስ ይደበድበናል የሚል የሥነ ልቦና ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...