በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል በኢራቅና በሶሪያ የከተመውን ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ለማጥፋት የአየር ድብደባ ከጀመረ ዓመት ሆኖታል፡፡ ሆኖም የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ መንግሥትን ከሚቃወሙት ጋር በመሆን ተንሰራፍቶ የነበረውን አይኤስ ማሽመድመድ አልቻለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የወደመችውን ሶሪያ ከሚመሩት አሳድ ጋር በትብብር መሥራት አለመቻላቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡
አሜሪካም ሆነች አጋሮቿ የአሳድ መንግሥት ተገርስሶ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት አሳድን በመቃወም በደማስቆ የተካሄደውን አብዮት የመሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሥልጣን እንዲይዙም ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም የእነ አሜሪካ ፍላጐት አገሪቷን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከመክተት ውጪ የፈየደው የለም፡፡
አሜሪካ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ተቃዋሚዎችን ብትረዳም የአሳድ መንግሥት ሊገረሰስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም አይኤስ ከኢራቅ ተነስቶ የሶሪያ የተወሰኑ ቦታዎችን እንዲቆጣጠር በር ተከፍቶለታል፡፡
ተቃዋሚዎችና አይኤስ በአሳድ መንግሥት ላይ በሚያደርሱት ጥቃት ሶሪያ ፈራርሳለች፡፡ ሕዝቧም ለስደትና ለሞት ተዳርጓል፡፡ አውሮፓ በሶሪያ ስደተኞች ተጨናንቃለች፡፡
በሶሪያ ጉዳይ ከአሜሪካና ከግብረ አበሮቿ የተለየ አቋም ያላት ሩሲያ የአሳድን መንግሥት በመደገፍ በሶሪያ በሚገኙ የአይኤስ ታጣቂዎች ላይ የአየር ድብደባ በይፋ ከጀመረች ሦስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ሩሲያ የአየር ድብደባውን የጀመረችው እነ አሜሪካ ከጀመሩ መንፈቀ ካለፈ በኋላ ቢሆንም፣ የሩሲያው ጣልቃ ገብነት በሶሪያ ለሚገኙ ተቃዋሚዎችም ሆነ ለአይኤስ መዳከም ምክንያት ሆኗል፡፡
ከዚህ ቀደም በአይኤስ ቁጥጥር ሥር የወደቁ የሶሪያ ግዛቶች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት አሳድ ተጠናክረውም ከእጃቸው ያመለጡ ግዛቶችን በማስመለስ ላይ ናቸው፡፡ የሩሲያን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመናገር ጊዜው ገና ቢሆንም፣ የአሳድ ወታደሮች ከዚህ ቀደም በተቃዋሚና በሽብርተኞች የተነጠቁትን ደቡብና ምሥራቅ የአሌፖ ክፍልን በእጃቸው አስገብተዋል፡፡ መንግሥትና ተቃዋሚዎች በሚዋጉበት ኢድሊብና ሃማ የመንግሥት ወታደሮች የበላይነቱን መያዝ ችለዋል፡፡ አይኤስ ላለፈው አንድ ዓመት ሥር ከነበረው ራሲን አል አቦውድ ኤር ቤዝ አፈግፍጓል፡፡
የሩሲያ የጦር ጄቶች በአይኤስ ላይ ድብደባ ሲፈጽሙ፣ የአይኤስ አባላት ደግሞ አሜሪካ ሠራሹን ቶው (Tow) ፀረ ታንክ ሚሳይል ሲተኩሱ የሚያሳዩ የተለያዩ የቪዲዮ ምሥሎችም ተለቀዋል፡፡ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ሩሲያና አሜሪካ በምድረ ሶሪያ የአየር ውጊያ እያሳተፉ ነው፡፡ በሶሪያ ጦርነት ከሚያካሂዱ የተለያዩ ቡድኖች ጐራም ተቀላቅለዋል፡፡
የአሳድ መንግሥትን የሚደግፈው የሩሲያ ጦር የአየር ድብደባውን ከሶሪያ እግረኛ ጦር ጋር በማጣመር የሰሜን ምሥራቅ ሶሪያን መቆጣጠር ተችሏል፡፡
በኢራቅና በሶሪያ ግዛቶቼ ናቸው በሚላቸው ሥፍራዎች ላይ የተንሰራፋውንና በኃያላኑ መንግሥታት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን አይኤስ በመደምሰስ አንድ አቋም፣ አሳድ ከመንበረ ሥልጣናቸው መነሳት አለባቸው በሚለው የተለያየ አቋም ያላቸው ሩሲያና አሜሪካ በየፊናቸው በምድረ ሶሪያ የአየር ድብደባ እያካሄዱ ነው፡፡ አሜካ መራሹ ጥምር ኃይል ሰሞኑን በሶሪያ በሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ አዲስ ጥቃት ሰንዝሯል፡፡ በጥቃቱም ቡድኑን ብቻ ሳይሆን ንፁኃንን መግደሉ እያስወነጀለው ይገኛል፡፡
በአሁኑ ድብደባው 26 ንፁኃን ዜጐች መገደላቸውንና የሶሪያ የጦር ካምፕ መመታቱን ተከትሎ ሶሪያ አሜሪካን ወንጅላለች፡፡
ዘ ጋርዲያን እንደዘገባው፣ አሜሪካ መራሹ ጦር በሶሪያ አል ካን በተባለ መንደር በፈጸመው ጥቃት፣ የአይኤስ አባላትን ሳይሆን ንፁኃንን ገድሏል ተብሏል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አራት የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች በጥቃቱ መገደላቸውም ውጥረትን አንግሷል፡፡
የሶሪያ መንግሥትን ደግፋ የአየር ድብደባ እያካሄደች ያለችው ሩሲያ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ባትሰጥም፣ በአሜሪካ በኩል ግን ማጣራት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
በአልካን አካባቢያዊ ቅኝት አድራጊዎችን ጠቅሶ ዘገባው እንዳመለከተው፣ ሰኞ ኅዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ በተፈጸመ የአየር ድብደባ ሰባት ሕፃናትን ጨምሮ 26 ሞተዋል፡፡ በሶሪያ የሰብዓዊ መብት ቅኝት መሪ ራሚ አብዱልራህማን እንደሚሉት፣ የሞቱ ቁጥር ሊጨምር ይችላል፡፡ ምክንያቱም በከተማዋ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ጠፍተዋል፡፡ ፍርስራሽ ሥርም የተቀበሩ አሉ፡፡
በከተማዋ ዳርቻ የአይኤስ አባላት ቢኖሩም፣ የአየር ድብደባው በተፈጸመበት የከተማዋ እምብርት የሚኖሩት ንፁኃን ነበሩ፡፡ ይህም ለንፁኃኑ ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡
ጥምር ጦሩ ባለፈው ወር በኢራቅ ባደረገው ድብደባ፣ አራት ንፁኃንን ገድሏል፡፡ በሶሪያ ሁለት ሕፃናትን በስህተት መግደሉንም አምኗል፡፡ በአልካን በነበረው የአየር ድብደባ 26 ንፁኃን የተገደሉት ጥምር ጦሩ አራት የሶሪያ መንግሥት ወታደሮችን ገድሏል ተብሎ ከተወነጀለ በኋላ ነው፡፡
ሶሪያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጽሕፈት ቤትና ለዋና ጸሐፊው ባን ኪሙን በላከችው ደብዳቤ፣ አሜሪካ መራሹ ጥምር ጦር በሰሜን ሶሪያ በምትገኘው ዴር ኢዞር አራት ወታደሮችን መግደሉንና 13 ማቁሰሉን አሳውቋል፡፡ የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱን አውግዞ ድርጊቱን ‹‹ወረራ›› ብሎታል፡፡
አሜሪካ ግን ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምኩም›› ብላለች፡፡ በአራት የበረራ ዙር በዴር ኢዞር በተደረገ ድብደባም፣ ከደቡብ ምሥራቅ አያሽ 55 ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙትን የነዳጅ ዘይት ማውጫ መሣሪያዎች መደብደቧን አሳውቃለች፡፡
የሶሪያ ወታደራዊ ምንጭ ግን በድብደባው የመንግሥት የመሣሪያ መጋዘኖች፣ የወታደር ማሠልጠኛ ካምፕና ሁለት ታንኮች ወድመዋል፡፡
አብዛኛው የዴር ኢዞር ክፍል በአይኤስ ታጣቂዎች የተወረረ ነው፡፡ ቡድኑ በከተማዋ ዳርቻ ሲኖር፣ የመንግሥት ወታደሮችና ሕዝቡ ደግሞ በመሀል ከተማ አሉ፡፡ የጥምሩ ድብደባ ደግሞ ከተማ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡
ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገውና በንግድ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚያማክረው አይኤችኤስ (IHS) አይኤስ በወር 80 ሚሊዮን ዶላር ከነዳጅ፣ ከግብርና ከዝርፊያ ይገኛል፡፡ በከተማዋ የሚገኘው የነዳጅ ሀብት የአይኤስ ዋና የሀብት ምንጭ ነው፡፡ በመሆኑም አሜሪካ የወሰደችው የአየር ድብደባ ቡድኑን አቅም ሊያሳጣ ይችላል ይላል፡፡
የሶሪያ መንግሥት አሜሪካ መራሹን የአየር ድብደባ ‹‹በሶሪያ ላይ የተፈጸመ የመብት ጥሰት›› ሲል በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ ጥምረቱ ሕገወጥ በመሆኑና ከሶሪያ መንግሥት ጦር ጋር ባለመጣመሩ ውጤታማ ሊሆን አልቻለምም ብሏል፡፡
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ‹‹አሜሪካ መራሹ ጦር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ቁርጠኝነትና ተዓማኒነት ይጐድለዋል፤›› ብሏል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ በሁለት ጥንዶች የተገደሉትን 14 ሰዎች አስመልክቶ ኅዳር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አሜሪካ አይኤስን ታጠፋለች፡፡ በአሜሪካና በሌሎች አገሮች የሚገኙ ተከታዮቻቸውንም ታድናለች፤›› ብለዋል፡፡
የአሜሪካ መራሹ ጦር የአየር ድብደባ አደርጋለሁ የሚለው በሶሪያና በኢራቅ የተንሰራፋውን አይኤስ ለማጥፋት ነው፡፡ ሆኖም በሶሪያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞውንም በእርስ በርስ ጦርነት ለላሸቀችውና የሩሲያ ጦር ጣልቃ ከገባ በኋላ መንሰራራት ለጀመረችው ሶሪያ ሌላ ሥጋት ነው፡፡ ምክንያቱም አሜሪካ አሳድ ላይ ያላትን አቋም በግልጽ አሳውቃለች፡፡
አገሪቷ በተሽመደመደችበት ጊዜም ቢሆን አሳድ ከሥልጣን መውረድ አለባቸው ትላለች፡፡ ከዚህ አቋሟ ጋር የአሳድ ወታደሮችና ትጥቆች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አሜሪካ ብታስተባብልም ለሶሪያ መንግሥት ሌላ መልዕክት አለው እየተባለ ነው፡፡