Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ውኃ ላይ ሆኖ በድርቅ መጠቃት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  በተደጋጋሚ በድርቅ ከፍተኛ ጉዳቶች የደረሱባቸው በአማራና በትግራይ ክልል የሚገኙ የሰሜን ወሎና የደቡባዊ ትግራይ ዞኖች ውስጥ ያሉ ወረዳዎች፣ ድርቅን  ለመከላከል በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ለመስኖ ልማት የሚውሉ ጉድጓዶች ባለመከፈታቸው አሁንም የድርቅ ተጎጂዎች እንዳደረጋቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡

  በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በ2007 የምርት ዘመን ባጋጠማቸው ከፍተኛ የሆነ ድርቅ ምክንያት፣ ከመንግሥት እየተሰጣቸው ካለው የዕለት ዕርዳታ ይልቅ ያለ ሥራ ለዓመታት የተቀመጡት የመስኖ ጉድጓዶች እንዲከፈቱላቸው የሚሹ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

  በቅርቡ በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች የተወሰኑትን ለመጎብኘት የቻለው የጋዜጠኞች ቡድን ማረጋገጥ እንደቻለው፣ በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውኃ ለመስኖ ልማት ማዋል እንደሚቻል ተረጋግጦ፣ የከርሰ ምድር ውኃ ጉድጓዶች ፕሮጀክት ግንባታ የተጀመረው ከ15 ዓመታት በፊት ነበር፡፡

  በእነዚህ ክልሎች በተመረጡት ወረዳዎች በ100 ሺሕ የሚገመት ሔክታር ሊያለሙ ይችላሉ የተባሉት የከርሰ ምድር ውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮና ግንባታዎች ከ15 ዓመታት በኋላም እየሰጡ ያሉት አገልግሎት እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ፣ በወቅታዊው ድርቅ አሁንም ሊመቱ መቻላቸውን የወረዳዎቹ አርሶ አደሮች በምሬት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በውኃ ላይ ቆመን ለድርቅ እየተጋለጥን ነው፤›› የሚሉት አርሶ አደሮች፣ ‹‹ከዕለት ዕርዳታው ይልቅ ለመስኖ ልማት የተቆፈሩ ጉድጓዶች ይከፈቱልን፤›› ብለዋል፡፡

  የራያ ቆቦ ወረዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት የ78 ዓመቱ አዛውንት አቶ ደሳለው አራርሳ እንደገለጹት የአካባቢው አርሶ አደር ይህን ፕሮጀክት ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን የጥልቅ ጉድጓድ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ የተጠናቀቀላቸው ሳይቀሩ ወደ ሥራ ሳይገቡ መቅረታቸው እንደቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡

  በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ያረጋል ኃይሉ እንደሚሉት፣ አካባቢው በተደጋጋሚ በድርቅ ሲጠቃ ስለነበረ በዚህ በከርሰ ምድር ውኃ መስኖ ፕሮጀክት ለመታደግ በሰሜን ወሎ ዞን በሦስት ወረዳዎች ተግባራዊ እንዲደረግ የታሰበ ነው፡፡

  በራያ ቆቦ አካባቢ ብቻ ከ17 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ማልማት የሚችል መሆኑን የገለጹት አቶ ያረጋል፣ እስከ 2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በከርሰ ምድር ውኃ ተጠቅመው በመስኖ ማልማት የተቻለው ግን 1,700 ሔክታር ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

  በሰሜን ወሎ ዞን በሦስቱ ወረዳዎች መቆፈር ከነበረባቸው 450 ጉድጓዶች ውስጥ ግንባታቸው የተጠናቀቀው 82 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወደ አርሶ አደሮቹ ማሳ ውኃ ሳይለቁ ተዘግተው ተቀምጠዋል፡፡ መቆፈር የነበረባቸውን ያህል ጉድጓዶች ያለመቆፈራቸውም ፕሮጀክቱ ተይዞለት በነበረው ዕቅድ መሠረት ያልተከናወነ ስለመሆኑም ያመላክታል፡፡

  እንደ ቆቦው ሁሉ በደቡባዊ ትግራይ ዞን በተመሳሳይ መንገድ እንዲገነቡ በዕቅድ ተይዘው የነበሩ ጉድጓዶች ያለመቆፈራቸውን፣ ከተቆፈሩት ውስጥም ወደ ሥራ የገቡት የተወሰኑ መሆናቸው በአካባቢ ለታየው ድርቅ መባባስ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል፡፡ በደቡባዊ ትግራይ ዞን ተስፋ ከተጣለባቸውና ግንባታቸው ከተጠናቀቁ 125 ጉድጓዶች ውስጥ 36ቱ ብቻ ሥራ ላይ መዋላቸውንም የወረዳው ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ የጉድጉዶቹ ወደ ሥራ አለመግባት ደግሞ በድርቅ ወቅት በቀላሉ አምርተው ድርቁን መቋቋም እንዳላስቻላቸው ይናገራሉ፡፡

  የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ አያሌው እያሱ፣ ‹‹እነዚህ ጉድጓዶች ቢለቀቁ ኖሮ ዘንድሮ ለድርቅ ባልተጋለጥን ነበር፤›› በማለት ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ጉድጓዶች ያለ ሥራ መቀመጣቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

  የትግራይ ደቡባዊ ዞን የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አረጋዊ እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ፣ በራያ አላማጣ ወረዳ ከተገነቡት 84 ጉድጓዶች ሥራ ላይ የዋሉት 46 ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቀድሞ በራያና አዘቦ ደግሞ ከተገነቡት 125 ጉድጓዶች ውስጥ ሥራ የጀመሩት 35 ብቻ መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡ 90 የሚሆኑ ጉድጓዶችም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ ጉድጓድ ተቀፍሮ ውኃው ወደ ማሳቸው የገባላቸውና በመስኖ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ወቅታዊውን ድርቅ መቋቋም ሲችሉ፣ በቅርብ ርቀት የተቆፈሩት ጉድጓዶች  ተዘግተው የተቀመጡባቸው አርሶ አደሮች ደግሞ ማምረት ባለመቻላቸው እጃቸውን ለዕርዳታ ዘርግተዋል፡፡

  እንደተዘነጋ የሚቆጠረው ይህ ፕሮጀክት በ2007 ዓ.ም. ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተያይዞ ትኩረት የተሰጠው ቢመስልም፣ አሁንም ጉድጓዶችን ከፍቶ ወደ ማሳ ውኃ እንዲያሰራጩ የተደረጉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡

  ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ባይጠናቀቅም በሰሜን ወሎ ዞን አዲስ ቀኝ ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ የጉድጓድ ውኃን ወደ ማሳ በመልቀቅ ወደ 200 የሚጠጉ የአርሶ አደሮች ማሳ ውስጥ እንዲገባ መደረግ ተጀምሯል፡፡ እንዲህ ማድረግ ከተቻለ ሌሎቹንም ጉድጓዶች ሥራ አስጀምሮ ድርቁን መከላከል ይቻል እንደነበር የተመለከቱ አርሶ አደሮች በሁኔታው ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

  በአዲስ ቀኝ ቀበሌ የጉድጓድ ውኃው እንዲሳብ የተደረገው ጄኔሬተር ተገጥሞ ሲሆን፣ ከዚህ ጉድጓድም በሰከንድ 70 ሊትር ውኃ በማመንጨት ወደ ማሳዎቹ ሲገባ በጉድጓዱ ዙሪያ ማሳ ያላቸው ገበሬዎችን ተስፋ አለምልሟል፡፡

  በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስቸኳይ ውሳኔ ጄኔሬተር እንዲገባና አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየውን የጉድጓድ ውኃ ሥራ ለማስጀመር ቢቻልም፣ በአካባቢው ካለው ፍላጎት አንፃር ዕርምጃው እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡

  አቶ ያረጋል እንዳሉት ግን ተጨማሪ አራት ጉድጓዶችን ሥራ ለማስጀመር የአራት ጄኔሬተሮች ግዥ በመፈጸሙ በአካባቢው በድርቁ የተከሰተውን ችግር እንዲህ ባለው የመስኖ ሥራ ለመታደግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከእነዚህ ጉድጓዶችም በሁለትና በሦስት ወራት ውስጥ እስከ 4,500 ሔክታር ለማልማት ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በጉድጓዶቹ ውኃ ተጠቅመው እያለሙ ያሉ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ጠቀሜታ እያገኙ መሆኑን የተመለከቱ የአጎራባች ቀበሌ አርሶ አደሮች፣ እነሱም ጉድጓዶቻቸው ተከፍተው እንደ ጎረቤቶቻቸው ማልማት የሚሹ መሆኑን በመግለጽ አቤቱታቸው ምላሽ እንዲያገኝ እየተማፀኑ ነው፡፡  በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በጎረቤት ቀበሌ አምናና ዘንድሮ የተከፈቱት ጉድጓዶች የሚለቁትን ውኃ በመጠቀም በመስኖ ያለሙት አርሶ አደሮች፣ በዓመት ሦስት ጊዜ እያመረቱ በመሆናቸው ይህ ዕድል ‹‹ለሁላችንም መድረስ አለበት፤›› ይላሉ፡፡

  ‹‹እኛ የዘራነው እህል ፍሬ አልባ ሲሆን፣ እነሱ ድርቁ አልዳበሳቸውም፡፡ ነገር ግን ከከርሰ ምድር ውኃ በማውጣት ለመስኖ ሊውሉ ይችላሉ የተባሉ ጉድጓዶች ተዘግተው እኛ የበይ ተመልካች ሆነናል፤›› በማለት የጉድጓዶቹ አለመከፈት እንዳሳዘናቸው አንድ አርሶ አደር ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ጉድጓዶቹ ይከፈቱልን›› ብለን በተደጋጋሚ ጠይቀናል ያሉት እኝሁ አዛውንት አርሶ አደር፣ ‹‹በቅርብ ርቀት ያለን አርሶ አደሮች ኑሯችን ለየቅል ሆኗል፤›› በማለት መንግሥት ከዚህም በኋላ ቢሆን  ጉድጓዶቹን ከፍቶ ድርቁን እንዲቋቋሙ እንዲረዳቸው ጠይቀዋል፡፡

  በ1977 ዓ.ም. የተከሰተውን ድርቅ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታወሱት እኝሁ አዛውንት፣ ‹‹ድርቁ ከዚህ በኋላ የከፋ ችግር እንዳያስከትል በእጃችን ያለውን ጉድጓድ ልንጠቀምበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

  በ1977 ዓ.ም. እና ከዚያ በፊት የተከሰቱ የድርቅ ወቅቶች ለአንድ ዓመት ችግር ፈጥረው የሚቆሙ ስላልነበሩ፣ በቀጣይም የምርት ዘመን ተመሳሳይ የሆነ ችግር እንዳይፈጠር እነዚህ ጉድጓዶች ጥሩ መፍትሔዎች ስለመሆናቸው በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡ አሁን መፍትሔው ዕርዳታ ሳይሆን እነዚህን ጉድጓዶች መክፈት ብቻ ነውም ብለዋል፡፡

  ውኃው ወደ ተለቀቀበት ሥፍራ አጎራባች ቀበሌ የወጡት አርሶ አደር  የዘንድሮው ድርቅ በእጅጉ ጎድቶናል ይላሉ፡፡ ‹‹ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጣለው ዝናብ ውጪ አላየንም፤›› ያሉት እኝሁ አርሶ አደር፣ ‹‹ያለችንን ጥሪት እየሸጥን አንድ ጣሳ ማሽላ በ12 ብር እየገዛን እስካሁን ቆይተናል፤›› ብለዋል፡፡

  ካሁን በኋላ እንዲህ እየገዙ የሚዘልቁት እስከ ጥር ብቻ እንደሆነ አመልክተው፣ ከዚያ በኋላ ያለ ዕርዳታ መቆየት እንደማይችሉ  ገልጸዋል፡፡ በአዲስ ቀኝ ቀበሌ ከአንድ ሳምንት በፊት ውኃ ያፈለቀው ጉድጓድ በእሳቸውም ቀበሌ ሥራ ቢጀምር መጋቢትና ሚያዝያ ወር ላይ ሊረማመዱበት የሚያስችል ምርት ማግኘት ያስችላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዕርዳታም ከመጠበቅ እንድን ነበር፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

  እንደታሰበው ጉድጓዶቹ ሥራ ካልጀመሩ ግን በአካባቢያቸው ችግሩ የፀና ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹አንድ ጉድጓድ ተለቀቀ ማለት በመቶዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ይጠቀማሉ፡፡ ጥቅሙ ደግሞ ለአሁን ላለው ችግር ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም ድርቅ እንዳያገኛቸው ያደርጋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

  ‹‹ይህንን ፕሮጀክት ለማስጀመር ከዓመታት በፊት ጉድጓድ ሲቆፈር እንዴት እኔ መሬት ላይ ይቆፈራል ይባል ነበር፤›› ያሉት አቶ ያረጋል፣ ‹‹አሁን ግን ከድርቁ ጋር በተያያዘ በየትም ቦታ ስንሄድ የአርሶ አደሩ ጥያቄ ይኼው የጉድጓድ ውኃ ይለቀቅና አዳዲስ ጉድጓዶች ይቆፈሩ የሚል ነው፡፡ በእርግጥም በአማራ ክልል ቆቦ አካባቢና በትግራይ ደቡባዊ ክፍል የከርሰ ምድር ውኃ መኖሩ የተረጋገጠ ስለሆነ፣ የጉድጓድ ቁፋሮና ትግበራው ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

  ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል የተባለው ፕሮጀክት በታሰበው ያህል ተግባራዊ ባለመሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች የሚሰነዘሩ ሲሆን፣ ችግሩ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥት አቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አቶ ያረጋል ገልጸዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ጉድጓዶች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በአነስተኛ ግምት አንዱ ጉድጓድ እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ በቆቦ አካባቢ በጉድጓድ ውኃዎች በመስኖ ለማልማት ታስቦ የነበረውን 17 ሺሕ ሔክታር ለማልማት የሚችሉ ሁሉንም ጉድጓዶች  ለማስጀመር በመቶ ሚሊዮን ብሮች ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡

  ስለዚህ ይህንን ሁሉ ወጪ በአንዴ ለማውጣት ስለማይቻል ደረጃ በደረጃ የሚሄድ ነው ተብሏል፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ያለመዘርጋቱ ትልቅ ችግር መሆኑንም ኃላፊዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በአማራ ክልል የተወሰኑ ጉድጓዶችን በጄኔሬተር ለማስጀመር ቢሆን ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል ነው የሚሉት፡፡

  አሁን በአንድ ቀበሌ በጄኔሬተር እየተሳበ የመጣውን ውኃ ለማመንጨት ጄኔሬተሩ በቀን 800 ሊትር ነዳጅ ይጠየቃል ብለዋል፡፡ አሁን ካለው ችግር አኳያ የክልሉ የምግብ ዋስትና ቢሮ ለነዳጅ ግዥ አንድ ሚሊዮን ብር መደቦ ነው እንጂ፣ ይህንንም ማንቀሳቀስ ከባድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁን ላሉትም ሆነ ወደፊት ለሚቆፈሩት ጉድጓዶች ለሚያስፈልጉ ፓንፖች የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ እንደሆነ አቶ ያረጋል ይገልጻሉ፡፡ የትግራይ ክልል የደቡባዊ ዞን ግብርና ኃላፊም ያሉት ጉድጓዶች ውኃ እንዲያወጡ ለማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል ትልቅ ፈተና እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ፓንፖቹን ለማንቀሳቀስ የኤሌክትሪ ኃይል እንዲለቀቅ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 23 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ቢሆንም፣ ይህ እስካሁን ተግባራዊ ባለመሆኑ የታሰበውን ማሳካት ያለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡

  በትግራይም ይሁን በአማራ ክልል ውስጥ በጉድጉድ ውኃ በመስኖ መልማት የሚችለው ሰፊ ዕምቅ ሀብት ከዚህም በኋላ ሥራ ላይ ለማዋል የአቅም ውስንንት በተደጋጋሚ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ያለው ተነሳሽነት የቀዘቀዘ መሆንም የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል፡፡

  የትግራይ ክልል ኃላፊዎች እንደገለጹት ደግሞ፣ ይህንን ፕሮጀክት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ችግሩ ከመልካም አስተዳደር ጋር ሊያያያዝ ቢችልም፣ አለማጣ ላይ ፓንፖች ተቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ ቀሪ ዕቃዎቹ መጥተው የተወሰኑ ጉድጓዶች ፓንፖች ተገጥመውላቸው ሥራው እንዲጀመር ይደረጋል ብለዋል፡፡

  በእነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ሁለቱም ክልሎች እየሰጡ ያሉት ምላሽ ግን የአቅም ችግር ማጋጠሙና በቂ በጀት ያለመገኘቱን የሚያሳይ ነው፡፡ የትግራይ ክልል የውኃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር አብረሃም እንደገለጹት፣ ጉድጓዶቹን ለማስጀመር ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ጉድጓዶቹን ሥራ ለማስጀመር ተከሰቱ ያሉዋቸውን የተለያዩ ምክንያቶችም ገልጸዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልጉ ፓንፖችን ያቀርብ ከነበረ ኩባንያ ጋር የተፈጠረው ያለመግባባትና ጉዳዩ በጽሕፈት ቤት ተይዞ መቆየቱ አንዱ ነው፡፡ ይህንን ችግር ቀርፈው ፓንፖቹን ተረክበውን በጥር ወር ተከላ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡

  የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ፕሮጀክቱን ሥራ ላይ ለማዋል የአቅም ውስንነት መኖሩን አውስተዋል፡፡ ይህም ዘላቂ መፍትሔ ይሰጣል ለተባለው ፕሮጀክት ቀዝቃዛ ምላሽ ቢሆንም፣ ይህ ፕሮጀክት በአካባቢው ላለው ድርቅ ዘለቄታዊ መፍትሔ መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡

  ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል የሚባለው ፕሮጀክት ሥራ ላይ አለማዋል ደግሞ፣ ‹ዕርዳታ አንሻም ጉድጓዱን ክፈቱልን› ለሚሉት አርሶ አደሮች መፍትሔ አይሆንም፡፡

  በእነዚህ ሁለት ክልሎች ቀድመው ሥራ ላይ መዋል የነበረባቸው ጉድጓዶች ሥራ ባለመጀመራቸው ከፍተኛ ጉዳይ ለማስከተሉ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑ ጉድጓድ የተቆፈረባቸው አካባቢዎች ላይ የደረሰው ድርቅ ነው፡፡ የራያ ቆቦ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ከድር ሙስጠፋ እንደገለጹት፣ ወረዳው 241 ሺሕ ሕዝብ ይኖርበታል፡፡ ‹‹በወቅታዊው ድርቅ በ23 ወረዳዎቹ ላይ ሰፋ ያለ ችግር ገጥሞናል፤›› ይላሉ፡፡ ከ23ቱ ደግሞ 11 የከፋ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡

  ‹‹በወረዳው ከ21 ሺሕ አርሶ አደሮች በላይ በመስኖ ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል፤›› ቢሉም፣ የተከሰተው ድርቅ ግን በወረዳው ከሚገኙ 106 ነዋሪዎች ከ78 ሺሕ ዕርዳታ የሚሹ ሆነዋል፡፡

  በራያ አላማጣ ወረዳ ደግሞ በ2007 የምርት ዘመን 1.7 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ የተገኘው 230 ሺሕ ኩንታል ብቻ ነው፡፡ ይኼም በወረዳው ውስጥ ካሉ  70 ሺሕ ነዋሪዎች አብዛኞቹ ተረጂ ሆነዋል፡፡ ቀሪዎቹ ነዋሪዎች የመስኖ ተጠቃሚዎች ነበሩ፡፡ በወረዳው በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ላይ ይረዳ የነበረው 15 ሺሕ ሕዝብ እንደሆነ የወረዳው ግብርና ኃላፊ አቶ አበራ በላይ ገልጸዋል፡፡

  በራያ አዘቦ ወረዳ ከ18ቱ ቀበሌዎች በተለየ የድርቁ ሰለባ በሆነችው ዋርግባ ቀበሌ 43,200 ሔክታር መሬት የሚታረስ ነው፡፡ በ2007 የምርት ዘመን 2.2 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 180,171 ኩንታል ብቻ ተገኝቷል፡፡ ይህም የዕቅዱን 8.3 በመቶ ብቻ ነው የተመረተው፡፡ ወረዳው 161,148 ሕዝብ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 77 በመቶው ምርት አላገኘም፡፡ በአጠቃላይ ከመስኖ ውጪ ያሉት ተጠቅተዋል፡፡ 124 ሺሕ ተረጂዎች አሉ ተብሎ ለመንግሥት ቀርቦ የተፈቀደላቸው ግን 87,005 ተረጂዎች ናቸው፡፡ ይህም በተፈገለው ልክ ዕርዳታ ያለመቅረቡን ያሳያል፡፡ መስኖው ሥራ ቢጀምር ኖሮ በዚህ አካባቢ ይህንን ያህል ተረጂ ይኖር እንዳልነበርና የምርት ቅናሽም ይከሰት እንደነበር ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡

  ራያና አዘቦ በመስኖ የበቀለ እንጂ በዝናብ የለማ መሬት የለም፡፡ መስኖ የሌለው እንደተቸገረ የሚናገሩት አቶ ፀጋ የተባሉት አርሶ አደር፣ ‹‹እኔ መስኖ አለኝ፡፡ እኔ ችግር ባይገጥመኝም ብዙዎች እየተቸገሩ ነው፤›› በማለት ሌሎችም እንዲደርሳቸውና እንዲጠቀሙ ውኃ መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

  - Advertisement -