Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የትግራይና የአማራ ክልሎች ቡና አምራች ለማድረግ አዲስ ዕቅድ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ክልሎች የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሊያቋቁሙ ነው

ከዚህ ቀደም በቡና አምራችነታቸው የማይታወቁት የትግራይና የአማራ ክልሎች ቡና ማምረት የሚያስችላቸው አዲስ ዕቅድ ተዘጋጀ፡፡

በከፍተኛ ደረጃ በቡና ምርት የሚታወቁት ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ናቸው፡፡ በአነስተኛ ደረጃ በቡና ምርት የሚታወቁት ደግሞ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ናቸው፡፡ ትግራይና አማራ ከቡና ምርቶች ጋር ስማቸው ተያይዞ አያውቅም፡፡ ነገር ግን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አዲስ በነደፈው ዕቅድ፣ የቡና ምርት መልክዓ ምድራዊ ካርታ ከደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል፣ ወደ ሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል እንዲለጠጥ አድርጓል፡፡

በዚህ መሠረት በትግራይ ክልል ደቡብ ትግራይ ዞን ራያ፣ አላማጣና መሆኒ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ፣ አዊ እና ጎንደር የተለያዩ የተመረጡ ወረዳዎች ቡና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ታጭተዋል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ አመኑ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ቡና ማምረት ከተጀመረ ረዥም ጊዜ እንደመሆኑ አመራረቱ ባህላዊ ነው፡፡ በአንፃሩ አማራና ትግራይ ክልሎች ለቡና ምርት አዲስ በመሆናቸው በዘመናዊ መንገድ ቡና ማምረት የሚያስችላቸው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ገበሬዎች በመከራ ቡና እያመረቱ ናቸው፡፡

‹‹በሙከራ ደረጃ የትግራይ ቡና ከሐረር ስፔሻሊቲ ቡና ጋር ተመሳሳይነት አለው፤›› ያሉት አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹በአማራ ክልልም እንዲሁ ተወዳጅ ጣዕም ያለው ቡና የሚመረት በመሆኑ፣ ምርቱን በዘመናዊ መንገድ ለማልማት ታቅዷል፤›› ብለዋል፡፡

በትግራይና በአማራ በዘመናዊ መልክ የሚመረቱ ቡናዎች ከሌሎች አካባቢዎች የተለየ ጣዕም ያላቸው በመሆኑ ሳይቀላቀሉ ለገበያ የሚቀርቡበት አሠራር ከመፍጠር በተጨማሪ፣ በዓለም ገበያ ውስጥ ተመራጭ እየሆነ የመጣው ከማሳ ጀምሮ የሚታወቅ የአመራረት ሥልት ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ፍቅሩ አስረድተዋል፡፡

ወደ እነዚህ አካባቢዎች የቡና ምርትን ማስፋት ሁለት ጠቀሜታዎች እንዳሉትም አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው አገሪቱ ከቡና የውጭ ገበያ የምታገኘውን ምንዛሪ ማሳደግ ነው፡፡ ሁለተኛው ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ቋሚ ሰብል ቢኖር፣ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በቋሚ ሰብሎቹ ድርቅ የሚያሳድርባቸውን ጉዳት እንዲቋቋሙ የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት አምስት ሚሊዮን አርሶ አደሮች በቡና ምርት ይተዳደራሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች በሥራቸው አምስት ቤተሰብ አለ ቢባል በዘርፉ 25 ሚሊዮን ሕዝብ ይተዳደራል፡፡ ዘርፉ የፈጠረው የሥራ ዕድልና ሀብት ከፍተኛ እንደሆነም ይነገራል፡፡ የቡና ምርቱ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ይሸፍናል፡፡

ባለፈው የበጀት ዓመት በሚኒስቴሩ ጥናት መሠረት 548 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ተመርቷል፡፡ ይህንን ምርት በዚህ ዓመት ከእጥፍ በላይ የመጨመር ዕቅድ ተይዟል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ከተመረተው ምርት 256,775 ሜትሪክ ቶን ቡና ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 183 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ተልኳል፡፡

በቡና ላይ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ኅዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቋቋም የወሰነው አዲሱ የቡናና  ሻይ ግብይት ባለሥልጣን ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ይህንን ባለሥልጣን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በማደራጀት ላይ ይገኛል፡፡

በፌደራል ደረጃ ከሚደራጀው ከዚህ ባለሥልጣን በተጨማሪ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ተመሳሳይ መሥሪያ ቤት እንዲያደራጁ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ትግራይና አማራ ክልሎች ባለሥልጣን ባይሆንም፣ ምርቱን የሚቆጣጠርና የሚያስፋፋ ክፍል እንዲያዋቅሩ መግባባት ላይ መደረሱን አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል፡፡

በፌደራል ደረጃ የሚቋቋመው የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከንግድ ሚኒስቴር የቡና ግብይት ክፍልና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ደግሞ የቡና ሻይና ዳይሬክቶሬት ይዞ በአዲስ መልክ የሚደራጅ መሆኑ ታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑን የሚመራው ዋና ዳይሬክተር በቅርቡ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች