Sunday, June 16, 2024

አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እየተገነባ ነው ወይ?

የዛሬ ሃያ ዓመት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. በፀደቀው ሕገ መንግሥት አማካይነት በፌዴራል ሥርዓት የምትመራው አገር አሥረኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በጋምቤላ እያከበረች ነው፡፡ በወቅቱ ሕገ መንግሥቱን በተወካዮቻቸው አማካይነት ያፀደቁት የአገሪቱ ሕዝቦች፣ ለፌዴራላዊው ሥርዓት ማበብ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን በመጠቀም በነፃ ፍላጎታቸው፣ በሕግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ዓላማ ከዳር ለማድረስም የግለሰብ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መሠረታዊ መብቶች የመከበራቸውን፣ የፆታ እኩልነት የመረጋገጡን፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ያላንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረግን አስፈላጊነት ፅኑ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ አገራቸው የራሳቸው አኩሪ ባህል ያላቸው፣ የየራሳቸው መልክዓ ምድር አሠፋፈር የነበራቸውና ያላቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች በመተሳሰር አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት አገር በመሆንዋ፣ ያፈሩት የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለ ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡ መጪው የጋራ ዕድላቸው መመሥረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆኑን ተቀብለዋል፡፡ ጥቅማቸውን፣ መብታቸውንና ነፃነታቸውን በጋራና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት አስፈላጊነትን አምነዋል፡፡ በትግላቸው በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፣ ይህ ሕገ መንግሥት ከላይ ለተገለጹት ዓላማዎችና ዕምነቶች ማሰሪያ እንዲሆናቸው በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት ማፅደቃቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ መሠረት ሕገ መንግሥቱ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ደንግጎ፣ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ተመሥርቷል፡፡ የአንድ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታም ተጀምሯል፡፡ ይህ ላለፉት ሃያ ዓመታት በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ዜጎች በልዩነት ውስጥ አንድነትን እንዲያጠናክሩ መሠረት የጣለ እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡ በዚህም መሠረት በየዓመቱ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ይከበራል፡፡ ነገር ግን ከበዓሉ አከባበርና ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በተጨማሪ፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ተግባር መሬት ላይ ይታያል ወይ? ይህ ጥያቄ የሚነሳው የፌዴራል ሥርዓቱ ዋና ዓላማ የአገሪቱ ዜጎች በእኩልነት መርህ አንድነታቸው መጥበቅ ስላለበት ነው፡፡ እዚህም እዚያም የሚታዩ ክፍተቶችና በወቅቱ ምላሽ የማያገኙ ጉዳዮች እያመረቀዙ ችግር ሲፈጥሩ ይታያሉ፡፡

አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ይፈጠርበታል የሚባለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ፅኑ መሠረት የሚኖረው ዴሞክራሲ ሲገነባና የሕገ መንግሥቱ መርሆዎች በትክክል ሥራ ላይ ሲውሉ ነው፡፡ ይህም ማለት ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በፖሊሲ ቀረፃዎችም ሆነ በውሳኔ አሰጣጥ ወቅት እኩል ተሳትፎ ሲኖራቸው፣ ሲደመጡ፣ ቅሬታዎቻቸው በአግባቡ ሲስተናገዱ፣ ሰብዓዊ ክብራቸው ሲጠበቅና የሕግ የበላይነት ሲከበር ነው፡፡ በተጨማሪም ሐሳባቸውን በነፃነት ሲገልጹ፣ የሚፈልጉትን ሲደግፉ፣ የማይፈልጉትን ሲቃወሙና በሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት በሰላም ሲተዳደሩ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ለይስሙላ በሚደረጉና መግባባት በማይፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ቢወጠሩ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ በተለይ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ አገራዊ የጋራ መግባባትን የሚፈጥሩ መሠረታዊ ጉዳዮች ካልተከበሩ ችግሮች መከሰታቸው አይቀርም፡፡

በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ እምነቶች፣ ባህሎች፣ የፖለቲካ አመለካከቶችና የመሳሰሉ ልዩነቶች በብዛት አሉ፡፡ እነዚህን ልዩነቶች በሒደት እያቀራረቡ በማጥበብ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት የሚቻለው ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ማዋል ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎችን የሚመልስ የፌዴራል ሥርዓት የሚገነባው ልዩነቶችን በማቻቻል ነው፡፡  በዚህም መሠረት የአገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማድረግ፣ ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራትን ማስወገድ፣ ሙስናን ከሥር መሠረቱ መንግሎ መጣል፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ ወዘተ ይቻላል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች ማሳካት ካልተቻለ ለፌዴራል ሥርዓቱ አደጋ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ቀርቶ የአገሪቱ ህልውናም ችግር ውስጥ ይወድቃል፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች ሕገ መንግሥቱን በመፃረርና የፌዴራል ሥርዓቱን ዓላማዎች ወደ ጎን በመግፋት በዜጎች ላይ ችግር የሚፈጥሩ ወገኖች አሉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዜጎች በመላ አገሪቱ የመዘዋወር፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መብት በመጋፋት የዜጎችን መዘዋወር መገደብ፣ ሀብት መዝረፍ፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ማፈናቀልና የተለያዩ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡ በአለፍ ገደም ክስ የተመሠረተባቸው አሉ ቢባል እንኳን ከዜጎች ሰቆቃና ሥቃይ አንፃር ውጤቱ እዚህ ግባ አይባልም፡፡ ይህ በራሱ ለፌዴራል ሥርዓቱ ጠንቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ችግር አሁንም ያላለቀ የቤት ሥራ እንዳለ ያሳያል፡፡ ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ልዩ ዞን የተዘጋጀው የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ጠቃሚነትን በአግባቡ ካለማስረዳት የመነጨ፣ ወይም በማስተር ፕላኑ ምክንያት ሊደርስ ይችላል የሚባለው ሥጋት ላይ በቂ ውይይት አለመደረጉ የፈጠረው ችግር ለዜጎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሰከን ያለ ውይይት ሲደረግ እንኳን አይታይም፡፡  

አንድ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዞው በሒደት ላይ ነው እንኳን ቢባል፣ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ ግን ብዙ ነገሮች እንደሚቀሩ ያሳያል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ ዜጎች ጥቅሞቻቸውን፣ መብቶቻቸውንና ነፃነታቸውን በጋራና በተደጋጋፊነት በማሳደግ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚገነቡበት መሠረት የጣሉት የዛሬ ሃያ ዓመት ነው፡፡ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን በመጠቀም በሕግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸውን ያበሰሩት የዛሬ ሃያ ዓመት ነው፡፡ በእርግጥ በእነዚህ ሃያ ዓመታት በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም፣ አሁንም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አሁን ፈተና ነው፡፡ ልዩነቶችን ማቻቻል አቅቶ በየቦታው ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ማዋል በማቃቱ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ጉዳዮች ተዳፍነዋል፡፡ በየቦታው ቅሬታ ይሰማል፡፡ አዳማጭ ግን የለም፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ችግር ሲፈጠር ከሰላማዊው መንገድ ይልቅ ኃይል ይበረታል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ መርሆዎች ጋር ይጋጫል፡፡ ለፌዴራል ሥርዓቱም ጠንቅ ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ሃያ ዓመት ሲሞላው መፈተሽ ያለባቸው ብርቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ጠንካራ የሚባሉ ጎኖች እንዳሉ ሆነው ድክመቶች ያለምንም ይሉኝታ ይታዩ፡፡ በስኬት ውስጥ የመሸጉ አሳሳቢ ችግሮች መፍትሔ ካልተፈለገላቸው፣ ስለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ መነጋገር ይከብዳል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ምሰሶዎች ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብት መሆን አለባቸው፡፡ የአገሪቱን 76 ብሔር ብሔረሰቦች የሚወክለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተለያዩ አመለካከቶችና ልዩነቶች የሚስተናገዱበት ሥርዓት በፅኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥና አሳታፊነቱ መጨመር አለበት፡፡ ለአፈናና ለአምባገነንነት ቦታ ሊሰጥ አይገባም፡፡ በብዝኃነታቸው ተከብረውና መብቶቻቸው ተጠብቆ ሊኖሩ የሚገባቸው ቡድኖች በአንድ አገር ጥላ ሥር የሚኖሩ ናቸው፡፡ ልዩ የሆኑባቸውን እሴቶች የቱንም ያህል ለመጠበቅ ቢጣጣሩ ጎን ለጎን የመለወጥና ኑሯቸውን የማሻሻል ህልማቸውን የሚደግፉ የጋራ አጀንዳቸው ግንባታ ላይ የራሳቸውን ድርሻ የማስቀመጥ ምግባራቸውን ሊረሱት አይገባም፡፡ ይህ ባልሆነበት ስለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ መነጋገር ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ለዚህም ነው በእርግጥ እየተገነባ ነው ወይ ተብሎ ጥያቄ የሚነሳው!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...