የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባል የሆኑ ሁለት ፖሊሶች፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አንፈጽምም በማለታቸውና ዳኛ ሲጠራቸው እምቢተኛ ሆነዋል በሚል ቅጣት ተጣለባቸው፡፡
ቅጣቱ የተጣለባቸው የኮሚሽኑ አባላት፣ ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤና ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያ ሲሆኑ፣ ቅጣቱን ያስተላለፈባቸው፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድበ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡
ፖሊሶቹ ሊቀጡ የቻሉት፣ በተጠቀሰው ፍርድ ቤትና ችሎት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሠረተባቸው ሲኢቢ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሚስተር ታን ሊ ከሚባሉ ተከሳሾች ጋር በተገናኘ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ በዋስትና የሚቆዩ ሰዎችን አፈታት በሚመለከት፣ ከልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ፣ በመፍቻ ስለሚፈቱ እስረኞች መግባባት ላይ መደረሱን የችሎቱ ዳኛ አቶ ዳንኤል አረጋዊ የሰጡት የትዕዛዝ ሰነድ ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱና መምሪያው በተነጋገሩት መሠረት፣ በፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ የማረሚያ ቤት ማቆያ፣ የሕግ እስረኛ ጠባቂነት የተመደቡት ሁለቱ ፖሊሶች፣ ዋስትና የተፈቀደላቸውን ሚስተር ታን ሊን እንዲፈቱ የተላለፈላቸውን ትዕዛዝ ‹‹አንፈጽምም›› ማለታቸውን የቅጣት ሰነዱ ያስረዳል፡፡ የፍርድ ቤቱ ዳኛ ፖሊሶቹ እንዲቀርቡ በፍርድ ቤቱ ተላላኪዎችና ጸሐፊ ጭምር እንዲጠሩ ቢያደርጉም፣ እምቢተኛ በመሆናቸው፣ ለፌደራል ፖሊስ በተላለፈ ትዕዛዝ ፖሊሶቹ በ24 ሰዓታት ውስጥ ታስረው እንዲቀርቡ መደረጉን ሰነዱ ያብራራል፡፡ ፖሊሶቹ ታስረው ዳኛ ፊት ከቀረቡ በኋላ፣ ለምን ታዛዢ መሆን እንዳልቻሉ ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ ፍርድ ቤቱን ባለማሳመኑ፣ ለ14 ቀናት ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ የአባሎቹ መታሰር ያሳሰበው ኮሚሽኑ፣ በሕግ ክፍሉ ኃላፊ ኮማንደር ታደሰ ተስፋዬ ፊርማና በተቋሙ መሀተም ወጪ በተደረገ ደብዳቤ፣ አባሎቹ የታሰሩበት ሁኔታ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሀብቴ ፊቻላ ይግባኝ አቅርቦ ነበር፡፡
ኮሚሽኑ ባቀረበው ይግባኝ እንደገለጸው፣ ሚስተር ታን ሊ ግብር ባለመክፈል ወንጀል ተከሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የማስፈቻ ትዕዛዝ ተጽፎ ለፖሊሶቹ እስከሚደርሳቸው ድረስ፣ እስረኛውን እንዲፈቱ በቃል መታዘዛቸውን አልተቀበሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ያለፍርድ ቤት መፍቻ ትዕዛዝ እስረኛ መፍታት የሕግንም ሆነ የአሠራርን ደንብ ያልተከተለ በመሆኑ፣ በፖሊሶቹ ላይ የእስራት ቅጣት መተላለፉም ሆነ ዋስትና መከልከላቸው አግባብ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ ዋስ መሆን እንደሚችል በማብራራት ዋስትና ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ አመልክቶ ነበር፡፡ የችሎት መድፈር ወንጀል የዋስትና መብትን ጨምሮ መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችንና ሥነ ሥርዓቶችን ለማክበር እዚያው ያለቀጠሮ የሚወሰን (Summary Judgment) በመሆኑ አይመችም ተብሎ በሕግ ምሁራን ቅሬታ የሚቀርብበት ወንጀል መሆኑ ይታወቃል፡፡
አቤቱታውን የተመለከቱት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትም በሰጡት ውሳኔ፣ የሥር ፍርድ ቤት በፖሊሶቹ ላይ ያስተላለፈው ትዕዛዝ የመጨረሻ የጥፋተኝነት ወይም የቅጣት ውሳኔ አለመሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩ የጊዜያዊ የቀጠሮ ትዕዛዝ በመሆኑ፣ በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 184(ሀ) መሠረት ጊዜያዊ ትዕዛዞች ይግባኝ እንደማይባልባቸው በመግለጽ ይግባኙን ውድቅ አድርገውታል፡፡
ፖሊሶቹ 17 ቀናት በእሥር ከቆዩ በኋላ፣ ፍርድ ቤት ቀርበው በወንጀል ሕግ 449 (1ለ) ማለትም ‹‹የፍርድ ቤት ሥራ በማናቸውም መንገድ ያወከ እንደሆነ›› የሚለውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል፣ ሁለቱንም ፖሊሶች ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ በመሆኑም ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያ አንድ ወር በእስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቶ፣ በአንድ ወር ገደብ ሳይታሰሩ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤ ደግሞ በአንድ ዓመት እስራት ተቀጥተው፣ ሳይታሰሩ በአንድ ዓመት ገደብ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡