Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅሕዳር 29 ቀን 2008 ዓ .ም 10ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በጋምቤላ ከተማ...

ሕዳር 29 ቀን 2008 ዓ .ም 10ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በጋምቤላ ከተማ ሲከበር

ቀን:

ውኃ የሸሸህ ዓሣ

መንጋህ የጠፋብህ ጉሮኖህን ያጣህ

እድለቢስ ዓሣ ከውኃህ የወጣህ

ላትሆነው ላይሆንህ ስደት የተጋባህ

ና ተመለስና ግባ ከውኃህ ከመንጋህ

      ከአድባር ዓይነሥጋ ከአውጋር ሽታ ርቆ

      ገላም አይመቸው ባዳ ቤት ተሳቆ

      ውል እያለ አፈሩ ውል እያለ አገሩ

      ሱስ ነው ውኃ ጥም ነው ስቃይ ነው አዳሩ

አገር ያሻት ሥጋህ ትረፍ ከሥጋቱ

የተጠማች ነፍስህ ትርካ ከጥማቱ

ቀዬህ ተቀላቀል ብቸኛው እንሰሳ

ተመለስ ባህርህ የወጣኸው ዓሣ

      ሕይወትህ በምንጫ እንደአዲስ ታንፃ

      ከመረበሽ ደዌ በአገር ፍቅር ትንፃ

      የአድማስ ወዲያ ማዶ ሰውነትህ ይብቃ

      ከአይሆንልህ ኑሮ ከቁም ቅዠት ንቃ

  • ተፈሪ ዓለሙ፣ የካፊያ ምች፣ 2007 ዓ.ም.

**************

ለጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በሊዝ የተገዛው አዲስ ጀት የሚያበረው አጣ

የጣሊያን መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገር አገር ሲጓዙ እንዲበሩበት የገዛው አዲስና ዘመናዊ ጀት አብራሪ ማጣቱ ተገለጸ፡፡

ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣ አውሮፕላኑ ከዩናይትድ ዓረብ ኢሚሬትስ ኢትሃድ ኤርዌይስ ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር በወር አንድ ሚሊዮን ዩሮ የሊዝ ክፍያ ስምምነት ተደርጎበት ጣሊያን የገባው፡፡ ሆኖም አውሮፕላኑ የገባው በጣሊያን አውሮፕላኑን ሊያበር የሚችል ባለሙያ ሳይሠለጥን ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አውሮፕላን ማብረር የሚችሉት የአየር ኃይል አባላት ብቻ ቢሆኑም፣ ለዘመናዊው አውሮፕላን የሚመጥን ሥልጠና ባለመውሰዳቸው ሥልጠና እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡

አንድ ሚሊዮን ዩሮ የሊዝ ዋጋ በወር የሚከፈልበት አዲስ አውሮፕላን የተገዛው፣ ከዚህ ቀደም የነበረውና አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቲዮ ሬንዚ የሚጠቀሙበት ኤ319 አውሮፕላን በማርጀቱና በየአምስት ሰዓቱ ነዳጅ ለመሙላት በየአገሮቹ ማረፍ ስላለበት ነው፡፡

**************

የአይጦች ጉባኤ

የአይጦች ወግ እንዲህ ነው፤ የአይጦች ድንበርና ቅጥር እየተደፈረ፣ በየዕለቱ ባልታሰበ ሁኔታ ድንገት እያደፈጡ ቀለብ የሚያደርጓቸውን ድመቶች ጉዳይ በተመለከተ ታላቅ ጉባኤ ተካሄደ፡፡ በዚህ በመፍትሔ አፈላላጊነት በሚጠበቅ ጉባኤ ላይ ከድንገተኛው የድመቶች አደን ማምለጫ የሚሆኑ በርካታ ሐሳቦች ተነስተው ቢወድቁም፤ በመጨረሻ ግን አንድ ጎረምሳ አይጥ ተነሳና የሚከተለውን የመፍትሔ ሐሳብ አቀረበ፡፡ ‹‹የድመቶችን ድንገተኛ አደን አስቀድመን የምናውቅበትና የምንጠነቀቅበት ብቸኛ መፍትሔ ነው ብዬ የማስበው ነገር ቢኖር በድመቶች አንገት ላይ ትንሽዬ ቃጭል ማሰርን ነው፡፡ ይህም ከሆነ ድመቶች ወደኛ በመጡና በቀረቡ ቁጥር የቃጭሉን ድምፅ ስለምንሰማ ዘለን ጉድጓዳችን ውስጥ ጥልቅ በማለት ማምለጥ እንችላለን›› ብሎ ወጣቱ አይጥ ተቀመጠ፡፡

የወጣቱን አይጥ መፍትሔ አዘል ሐሳብ ያደመጠው የአይጦቹ ጉባኤ፣ ለሐሳቡ አድናቆት በመስጠት በጭብጨባና በእልልታ ቀውጢ ሆነ፡፡ ተገላገልን፣ ከመበላት ዳንን፣ ዕድሜችንን አራዘምን ተባለ፡፡ አይጦች ሁሉ የምሥራቹን እንደሰሙ ጥርስ-በጥርስ ሆኑ፡፡

ጭብጨባውና እልልታው ረዥም ጊዜ ቆይቶ ጋብ ሲል፣ አንድ በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ አዛውንት አይጥ ከተቀመጡበት ብድግ አሉና ‹‹ወጣቱ ያቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ በእውነቱ ከሆነ እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን …›› ብለው የመቃወሚያ ሐሳባቸውን ከማቅረባቸው በፊት ጉባኤው ማጉረምረም ጀመረ፡፡ ከወደመድረኩ አካባቢ ፀጥታ እንዲከበር ትዕዛዝ ተላልፎ አይጦች ሁሉ ፀጥ ሲሉ አዛውንቱ ንግግራቸውን ቀጠሉ፤ ‹‹እውነቴን እኮ ነው፡፡ መፍትሔው ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ያንን ትንሽ ቃጭል ከድመቶች አንገት ላይ የሚያንጠለጥለው ማነው?›› አሉና መሠረታዊውን ጥያቄ ወርውረው ተቀመጡ፡፡ ሁሉም አይጥ የጉዳዩ አሳሳቢነት ገብቶት ዝም አለ፡፡ ግማሹም በሆዱ (በሬ ሆይ- በሬ ሆይ፣ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ) ሳይል እንዳልቀረ ይጠረጠራል፡፡ እውነትም ቃጭሉን በድመቶች አንገት ላይ ማን ያንጠለጥለዋል?

  • አሸናፊ ደምሴ፣ የኢሕአዴግ የማርያም መንገድ፣ 2007 ዓ.ም.

***********

ከፍርድ ለማምለጥ ራሱን ፅኑ ሕመምተኛ ያስመሰለው ግለሰብ ተጋለጠ

የ48 ዓመቱ አለን ናይት አዛውንት ጎረቤቱን 41 ሺሕ ፓውንድ አጭበርብረሃል ተብሎ ክስ ይመሠረትበታል፡፡ ክስ የተመሠረተበት ናይት፣ ፍርድ ቤት ከመከራከር ይልቅ የመረጠው ቤቱ ውስጥ ታማሚ መስሎ መተኛትን ነበር፡፡ እንደ ፅኑ ሕመምተኛ (ኮማ) ውስጥ እንዳለ በማስመሰል ያለፉት ሁለት ዓመታትን ያጭበረበረው ናይት፣ የተጋለጠ ሲሆን ያለውን በመኪና የሚሳብ ካራቫን ሽጦ ዕዳውን እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡

ሚረር እንደዘገበው፣ ናይት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ጥሪ ሲደርሰው፣ የ33 ዓመት ሚስቱ ሄለን ናይት በመገኘት ‹‹ከሶፋ ላይ አይነሳም፣ ሙሉ ቀንም አይንቀሳቀስም በፅኑ ታሟል›› በማለት አሳውቃ ነበር፡፡ ሆኖም ናይትና ባለቤቱ ቤተሰብ ለመጎብኘት እንግሊዝ፣ ሳዋንሳ መሄዳቸውን በማረጋገጡ፣ ናይት ራሱን በሽተኛ ነኝ ያለው ውሸት መሆኑ ተረጋግጦበታል፡፡

ናይት ‹‹ያልጋ ቁራኛ የደዌ ዳኛ ነኝ›› ባለበት ወቅት በሌለበት አራት ዓመት እሥራት የተፈረደበት ሲሆን፣ ታምሜያለሁ ብሎ በማጭበርበሩ ተጨማሪ ሁለት ዓመት ከሁለት ወር ተፈርዶበታል፡፡

ናይት ራሱን ታማሚ ባስመሰለበት ወቅት፣ ሚስቱ ሄለን በፍርድ ቤት የተያዘው ጉዳይ ውድቅ እንዲሆን ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብታ ነበር፡፡

ሞናሊዛ

ብዙ ተተችታለች ብዙ ንትርክ በቅርቡ ፈጥራ ነበር፡፡ ገሚሱ በእርግዝናዋ ወራት የተሠራች በመሆንዋ ሆዷን ለመደበቅ ነው እጆቿን እሆዷ ላይ ያሳረፈችው አሏት፤ ገሚሶቹ ሠዓሊው ሞዴል ሳይሆን ወንዱን በሴት አምሳል ሠርቶት ነው አሉት፡፡

አታርፍም ዓይኗ ብዙ ሰው በአንድ ጊዜ ይመለከታል፤ በዋጋም በኩል ከፍተኛው የሥዕል ዋጋ የተተመነላት ለሷ ነው፡፡ ‹‹ሞናሊዛ››

ሰሎሞን ተሰማ ዜማ አውጥቶላት ጥላሁን አጣጥሞ ተጫውቶላታል፡፡ ሠዓሊው ሞናሊዛን በ90 የፈረንሣይ ፍራንክ በዘመኑ ለነበረው የፈረንሣይ ንጉሥ ወዶ ሳይሆን በንጉሡ ውትወታ ሸጦለታል ተብሎ ተጽፏል፡፡ በዓመቱ በ1974 መጀመሪያ ገደማ የወጣው ለፊጋሮ የተባለው የኢጣልያን መጽሔት እንዲህ ይል ነበር፡፡

ሌዎናርዶ ዳቪንቺ ከኢጣሊያ ወደ ፈረንሣይ ከመሄዱ በፊት የሠራው ሥዕል ነበረው፤ ሠዓሊው ያንን ሥዕል ስለአልወደደው ፈረንሣይ አገር ሲደርስ የመጀመሪያውን ሥዕል አጥፍቶ ሞናሊዛን በላዩ ሠርቶበት ሲያበቃ ይኸኛውንም ሥዕል ባይጠላውም ከሌሎቹ ሥዕሎች ጋር ሊወዳደር አይችልም በማለት እቤቱ ውስጥ ባለው የመታጠቢያ ቤት በር ላይ ከውስጥ በኩል ለጥፏት ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩት የፈረንሳይ ንጉሥ የሌዎናርዶ ዳቪንቺን ቤት በጎበኘበት ጊዜ በአጋጣሚ ሥዕሏን አያትና እንዲሸጥለት በጣም ለመነው፤ ዳቪንቺ የሥዕሉ ውበት ይህን ያህል ስለአልሆነ ሊያጥላላው ቢሞክርም ንጉሡ እምቢ ብሎ በ90 የፈረንሣይ ፍራንክ ገዝቷት ሄዶ በንጉሡ ቤት ሥፍራ ተሰጣት፡፡ ብዙ ጊዜ አልቆየችም ወዲያው ከንጉሡ ሳሎን ጠፋች፣ ተሰረቀች፡፡ ንጉሡ ለሥዕሏ ፍቅር ሳይሆን ቤቱ በመደፈሩ በአዋጅ መልክ ሥዕሏን የሰረቀው ሰው እንዲመልስ አዘዘ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሥዕሏ ስም ተራባ፣ ዋጋዋም ጨመረ፡፡ ሥዕሏ አልተመለሰችም ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ተገኘች፡፡

ብዙ ጊዜ ተሰርቃ የመሸጡ ነገር ችግር በመፍጠሩ ተመልሳለች፤ በቅርቡ [1967 ዓ.ም.] ወደጃፓን ለትርኢት ተልካ ሳለ የብዙ ሚሊዮን ብር ዋስትና ተደርጎላት ተጉዛ በምትታይበትም ወቅት በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ቁጥጥርና ጥበቃ ተደርጎላታል፡፡

  • ‹‹ቁም ነገር›› (1967)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...