Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በስንቱ እንብሰልሰል?

ሰላም! ሰላም! ሰላምና እሳት ገጠሙና ‘እፍ አሉ…’ አሉ። ደግሞ ሁለቱም ያለቆስቋሽና ያለጠበቃ አይሆንላቸውም እኮ። ‘እፍ…’ አባባላቸው ጠበቆቻቸውንና ቆስቋሾቻቸውን ገሸሽ አስባለ። ሰላም ወበቅ በዛባት፡፡ እሳትም አጓጉል ቅዝቃዜ ይሰማው ጀመር። ያለባህሪው መስሎና ተመሳስሎ መኖር የሚያውቅ መቼም ከፍጥረት ሁሉ እንደ ሰው ልጅ የለም። በመካከል አንዱ ሲጠቀም ሌላው ከአስብቶ አራጁ ይውላል። “ወይ አለመመከር! ወይ አለመዘከር!” ይላሉ ባሻዬ ከእኔ ይቅር ሲሉ። እናስ? እሳትና ሰላም ምክር ተቀመጡ። ስብሰባ አላልኩም። ይኼ በየቀኑ ተገልጋይ በቀጠሮ እየተጉላላ ስብሰባ ላይ ነን ዓይነቱን ማለቴ ነው። “ግን እኔ ምለው ስብሰባው ለመሰብሰብ ከሚሆን ለምን ላለመሰብሰብ አይሆንም?” አ አንዱ መቼ ዕለት አንድ ከክፍለ ሀገር መሸኛ ይዞ የመጣ ዘመዴ፤ መታወቂያ ላስወጣለት ሦስት አራት ቀናት ቢመላለስ ታክቶት ነው።

እኔ ደግሞ ድምፄን ከፍ አድርጌ፣ “ካልተሰበሰብንማ አንደኛውን በማኅበር መታቀፍ ምን ያስፈልጋል? አንደኛውን በዱር በገደሉ እንደ ሽፍታ አንኖርም?” ማለት። ይኼን ስል አንዱ ሰምቶኝ፣ “ሽፍታ በሸፈተበት ሆኖ ነው የሚሸልለው። ‘ጎበዝ ከሆንክ’ ሞክረው” አይለኝ መሰላችሁ? አያችሁ ግን? የእኛ ቸግር እንደ ዓሳ ሞት መቼ ከአናታችን ሆነ። ጭራው ላይ ነው ስላችሁ። “እና ለምን ጭራውን አንቆርጠውም?” ብሎ የባሻዬ ልጅ አዋየኝ። ባሻዬ ሰምተውት፣ “የነብርን ጭራ አይዙም ከያዙም አይለቁም፤” አሉታ። ሆሆ! እስኪ አሁን አርፈን ጭራን ለዝንብ ማባረሪያ እየተጠቀምን እንደመኖር በገዛ እጃችን ጭራን በሽሙጥ ፖለቲከኛ ማድረግ ምን ይባላል? እናማ በፆታ እኩልነት ተሠርቶ የማይታወቅ ሥራ ሠርተናል እያሉ ዋኖቻችን አኃዝ ይጠቅሳሉ፡፡ ጥንስሶቹ መስማት የፈለጉትን ብቻ እየሰሙ ወኔን በፆታ ይበይኑታል። አወይ ጣይቱ! አወይ እነ ህንደኬዎች። ምነው አንዴ ለምስክርነት መቃብር ፈንቅለው ባየናቸው።

ለነገሩ ሲፈጥረን ብናይም አናምንም። “ይኼ ትውልድ ምልክትን አጥብቆ ይሻል ይባል የለም ወይ?” ብዬ ባሻዬን ስጠይቃቸው፣ “እሱ ለእኛ አይደለም፤” ብለው በአጭሩ መለሱልኝ። ደህና አድርጌ ስለማውቃቸው ነገር ሲያሳጥሩ ይገቡኛል። እናንተም ይገባችኋል አይደል? ሌላው ቢቀር ባሻዬን በአካል ባታውቋቸው ከአንዳንድ ዘገባ አሰራጮች ሥልጠና ሳትወስዱ አትቀሩም። “ለነገሩ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ማለት አያስፈልግም፤” የሚባልበት ቴአትር ደጋግሞ ያየ ወዳጄ ትዝ አለኝ። እኔ እንደ ጥላሁን ገሠሠ የጥንቱ አይደለም ትዝም የሚለኝ። ትዝታ ለአቅመ ትዝታ ለደረሰ ብቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ንብረት ነው የሚሉትን ለግዜው አደብ ግዙ በሉልኝና ልቀጥል። ከመቀጠሌ በፊት የክብር ስፖንሰሬን ማስታወቂያ አሁን እከፍታለሁ። ‘ኤጭ! አትሰልቸና! አንዱን አንስቶ አንዱን መጣል ምንድነው?’ ዓይነት ስትሰላቹ ይታወቀኛል። ጎበዝ ከሆናችሁ . . . (ታላቅ ይቅርታ ምንትስ ከምንትስ ጋር ስትውል ምናምን ነገር ተምራ መጥታ’ ነው ብላችሁ ዝለሉኝ) ማለቴ አቅም ከላችሁ መጀመሪያ የአየር ሰዓቱን ፍሬውን አሳንሰው ገለባውን ከምረው ከተቆጣጠሩት ጋር ተሳፈጡ። ምነው? አሁን ማን ይሙት ቢራ በደረሰበት የማትደርሱት ጭምር በማስታወቂያው ብዛት ብቻ ስካር ስካር አላላችሁም? እኮ!

እና ምን እያልኳችሁ ነበር? አዎ ባሻዬ ‘ለእኛ አልተጻፈም’ አሉኝ አልኳችሁና ማስታወቂያ አበዛሁ። አሁን ተመልሰናል። እንኳን ለአገራችን አበቃን ይባላል ታዲያ። ነው እንኳን ለክልላችን አበቃን ነው የሚባለው? እኔ ምን አውቄ ታዲያ? ባሻዬን፣ “ለእኛ የተጻፈው ምን ይላል?” አልኳቸው። “ለምን አትተወኝም ልጅ አንበርብር?” አሉኝ ምሳጤያቸው ክፉኛ ደቁሷቸው። “ማን አለኝ ብዬ ልተወው?” ስላቸው አንጀታቸውን ልበላ፣ “አልተጻፈማ። ያልተጻፈውን ከየት ልውለደው?” ብለው ተቆጡ። “እኔ ብራና ቀለሙን ላዘጋጅ። መቼም ይኼ ትውልድ በብራና የተጻፈን ጽሑፍ በመናቅና ከልክ ባለፈ አግዝፎ በማየት የሚስተካከለው የለምና አንድም በመናቅ አንድም ለአምልኮ በደረሰ አድናቆት እርስዎ ቢጽፉት ያዋጣል፤” ማለት። የደላላ ነገር ሁሉ በያዋጣልና አያዋጣም ዥዋዥዌ ሲወዛወዙ መኖር አይደል። ባሻዬ “ማ? እኔ? ‘ይህ ትውልድ ያለምልክት አያምንም። ምልክት ሲያይም ምልክቱን ለማየቱ ሌላ ምልክት ይሻል’ ብዬ ነው የምጽፈው? አላደርገውም፤” ብለው በቃል ተወጡት። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ እንበልና ምልክት ምንድነው ብለን እንጠይቅ? እንዴ! እኔ እኮ እናድም አላልኩም። እንጠይቅ ነው ያልኩት፡፡ ምን ያስደነግጣችኋል? ደግሞ መልሱ በእጃችን መስሎኝ። ግድ የለም እጅ እጃችሁን ስታዩ አመድ አፋሽነታችሁ ከኑሮ ውድነት ጋር ተጎዳኝቶ እንዳይሸነቁጣችሁ መልሱ ይኼው፡፡ ምልክት . . . እ? . . . ምልክት፣ ‘ቅንጣት ታህል ዘር በስብሳ ፍሬ ስታፈራ፣ ማለትም አንድም ስታኮራ አንድም ስታስፈራራ’ ማለት ነው።  ማለት ያው ማለት ማለት ነው! እናንተን መቼ አጣኋችሁ አጥንት  አትቆርጥሙ ስትባሉ ወተት ወተቱን መያያዛችሁ መቼ ጠፋኝ። ሞኝህን ፈልግ አለ ያገሬ ሰው!

ሞኝ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? ‘አወይ ልጅነቴ ማርና ወተቴ’ የምንላት ነገር። “ምን ነገር አላት?” አለኝ ባለፈው የባሻዬ ልጅ። እሱ ደግሞ ምሁርነቱን መሰሰት አንዳንዴ ይቀናዋል መሰለኝ። አሁን እስኪ መዋለ ንዋይን በፍትሐዊነት ለማከ’ፋፈል ይሳሳ ይሆናል። ነዳጅ ወጣ ቢባል አንቀጽ ሰላሳ ሰጠኝን ቀዳችሁ ስጡኝና ወደምሄድበት ልሂድ የሚል ቢገኝም አይደንቅ ይሆናል። ነዳጅ ነዋ ሰውን ሰው ከማድረግ አልፎ አይኤስ ለሚባለው አረመኔ ሳይቀር ነው የገቢ ምንጭ የፈጠረው። ያላየነውን አናውራ የሚባለው መቼም ተጠያቂነትና ኃላፊነትን አውቆ ለሚሠራ ተቋም እንጂ ለአሸባሪ አይመስለኝም። ግን እንዴት ዕውቀት ይሰሰታል? እኔ ሰሰተ አላልኩም አደራ። እንዲያው ነገሩን ነው።

እናላችሁ ነገር ሊፈልገኝ ‘ምን ነገር አላት?’ ሲለኝ፣ “ነገር ባይኖራት ኖሮ በቆሎና በሽሮ አድገን የት ያየነውን ማርና ወተት ነው የምናስታውሰው?” አልኩት። በበኩሌ ከማር ይልቅ የላስኩት ስኳር ነው ትዝ የሚለኝ። አሁን ስኳርና መልካም ትዳር ጥቂቶች ዘንድ ብቻ በሚኝበት ጊዜ ላይ እ? አይበለውና . . . እ? ‘እንዲህ በስኳር ችግር የተጠበስነው የትናንቱ ትውልድ አባላት ከቀበሌ በአሳር በስፍር የተገኘን ስኳር ተደብቆ ይቅም ስለነበረ ነው’ ቢባል አንደኛ የምበሰብሰው እኮ እኔ ነበርኩ። “እኮ ደርግ ፋሺስት መንግሥት ተብሎ መፈረጁ አድኖን? አንድያው! ወዲህ ሰሞን ላልሰን ቢሆን ኖሮ ልተርፍ?” የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። “ወደን ነው? አሁን እኮ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ዘመን ላይ ነን…” ብዬ ሳልጨርስ (የጨረስኩላችሁ በገዛ መድረኬ ማይኩ በእጄ ስላለ ነው) “ሆድ ይፍጀው” ብሎ ዝም አለ። እኔም ዝም። ዝም ዝም። ‘ስኳር ስኳር አለኝ ብቀምሰው ከንፈሩን’ የሚለውን እያዳመጣችሁ ነገራ ነገሩን ብትረሱት ጥሩ ነው። አይ ስኳርና ስርቆሽ! አይ ብዝበዛና እኛ። መቼ ይሆን ግን ሙሰኛ አንገቱን ደፍቶ የሚጓዝበት ቀን የሚመጣው?

 ማርና ወተት ከተነሳ አይቀር እነሆ አንድ ገጠመኝ። ሰሞኑን ነው። አዲሱ ትውልድ ልጅነቱን ‘ዲጂታላይዝድ’ በሆነ መንገድ እያጣጣመ እንደሆነ ለዘመኑ ሰው አይነገርም። ለቀባሪው ማርዳት ነው። “እየጣመው ይሁን እየመረረው ብቻ ጥናት ያስፈልገዋል፤” ስል “ወይ አንተ!” አለኝ አንድ ዳያስፖራ ኢንቨስተር ደንበኛዬ። ዓመት ገደማ ልጆቹን በማልጠራው ዋጋ  አንድ ‘ቡርዢዋዚ’ ትምህርት ቤት አስገባና ለማመላስ እንዲመቸው ትምህርት ቤቱ አካባቢ አንድ ጥሩ ቪላ መግዛት ፈለገ። አጋዛሁት። “እንዴት?” ስለው “ኧረ ተወኝ። አጥኑ ሲባሉ ‘ኤልሲዲውን’ ቀይረውና አጠናለሁ፣ አንብቡ ሲባሉ አዲስ ‘ቨርዢን ታብሌት’ ካልተገዛልኝ ከደብተር አላነብም’ እያሉ የምን ጥናት ነው እነሱ ላይ የሚሠራው። ካልክስ ጥናቱ ወላጅ ላይ ነው የሚያስፈልገው፤” ብሎ ልጅ በማሳደግ እያየ ያለውን አበሳ አጫወተኝ። አሁን ሰሞኑን ታዲያ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሲከበር (በነገራችን ላይ ሦስት ልጆች አሉት) አንዱ ‘ጊሌ’ ግዛ ሲለው አንዷ ‘የትግራይን ክልል ባህላዊ አለባበስ ይዤ ስለምቀርብ በወርቅ አንቆጥቁጠኝ’ ስትለው ከሃያ ሺሕ ብር በላይ ማውጣቱን ደረሰኝ እያሳየ ነገረኝ። እኔ ምለው? አትጣለው ይወራረድ ይሆናል ልበለው እንዴ ደውዬ? አጣሩና ንገሩኝ እስኪ።

ኋላ፣ “መቼም ይኼ ይኼ ነገር ሕገ መንግሥቱ ላይ አልተጻፈም፤” ሲለኝ ሳቄ መጣ። ውሎ አድሮ ቤቱን ሊሸጠው እንደሆነና ገዢ እንድፈልግ ነገረኝ። ግራ እንደገባኝ  ገዢ ይዤ ሄጄ ቤቱን ሳሳይለት ልጆቹን ተዋወቅኳቸው። የሚገርማችሁ በዓሉ አልፎም ወንዱ ልጅ ጊሌውን ሴት ልጁም ወርቋን አናወልቅም እንዳሉ ነበሩ። በዚህ ዕድሜያቸው ስለአገራቸው ሕዝብና ባህል ያላቸው ዕውቀትና ፍቅር ዛሬ እንዲህ ከሆነ ሲያድጉ እንዴት ይጎመራ ይሆን? እያልኩ ደስ አለኝ። መቼም ልጅ ይወደኛል ብዬ ላጫውታቸው ቀረብ ብዬ ማሙሽዬ ሚሚዬ ከማለቴ ሴቷ “ዳዲ is he crazy?” ትለዋለች። ወንዱ ያው (በእንግሊዘኛ ነው) “ለምን ወደ አዕምሮ ሕሙማን መርጃ አትወስደውም?” ይለዋል። ምን አድርጌያቸው እንደሆነ አትጠይቁኝም? እንደ ሕፃን አባበለን ብለው ደብሯቿው ነዋ። የቱን ይዘን የቱን አንደምንጥል ተውትና ብቻ አንድ ትልቅ ሰው ቤታችን ሲመጣ እንዴት እንሆን እንደነበር እኛን፣ የትናንትናዎቹን አስቡን። እናስ? አሥር ዓመት ያልደፈነ አንድ ሕፃን በሙሉ ሰው ሒሳብ ልሰላ እያለ ኪሳራውን ጠቅላላ ወላጅ ላይ መከመር ይቻላል? አቤት! ይኼኔ ሌላ ነገር ላወራ መስሏችሁ ሰፍ ብላችሁኋል አይደል? ወይ እኛና ወሬ!

እንሰነባበት? አዎ ይሻለናል። ያ ዳያስፖራ ደንበኛዬ ልጆቼ፣ “አንድ ቋንቋ ብቻ እየተማሩ እንዴት ይዘልቃሉ?” ብሎ ነው ቤቱን የሸጠው። በኋላ ነገረኝ። እናማ ይዟቸው ወደ መጣበት ሊጓዝ ነው። እንጃ ከየት ወደ የት እንደሆነ። ብቻ ብዙ ነገር ተዘበራርቆብኛል። በነገራችን ላይ የሰላምንና የእሳትን መጨረሻ ነገርኳችሁ? ያልነገርኳችሁ መጨረሻ ስለሌላቸው ነው። ምክንያቱም ገና ከስብሰባ አልወጡም። እኛም እነሱም መቼ እንደምንወጣ አናውቅም። ሥራችን ነገር ብቻ ሆኗል። እያደርን ወደኋላ እያየን መገንፈል መገፋፋት አልሰለቸን ብሏል። እንዲያው ነገሩን ነው እንጂ እሱማ እንዲህ ነው “እንዲህ ነው ማለት አያስፈልግም” ብሎ መተው ይሻል ይሆን ብዬ ተውኩት። ልተወው እልና ግን የማያስተው ነገር ሲገጥመኝ ያብሰለስለኛል፡፡ የሆነስ ሆነና በስንቱ እንብሰልሰል? ቻው! መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት