Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየማይነገሩ ፍርኃቶች

የማይነገሩ ፍርኃቶች

ቀን:

ወ/ሮ የትነበርሽ በላይ የተወለዱት ሆሳዕና አካባቢ ነው፡፡ የ60 ዓመቷ የቤት እመቤት በትውልድ ቀያቸው አጃቾ የሚባል ወንዝ ላይ የተሠራ የእንጨት ድልድይ እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡ ልጅ ሳሉ በድልድዩ የሚሸጋገሩ ሰዎች ድልድዩ ተሰብሮ ውኃ እንደሚወስዳቸው ይነገራቸው ስለነበር ወደ ድልድዩ ሄደው አያቁም፡፡

በትክክል ባያስታውሱም የ20 ዓመት ወጣት ሳሉ ጀምሮ ማንኛውንም ድልድይ የመሻገር ፍርኃት እንዳለባቸው ማወቃቸውን ይናገራሉ፡፡ እርግጠኛ ባይሆኑም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት አስተዳደጋቸውን ነው፡፡ ድልድይ ከገጠማቸው ሌላ መንገድ ቀይረው ይሄዳሉ፡፡ በድልድይ መሻገር የግድ ከሆነባቸው ሰዎች ተደግፈው ያልፋሉ፡፡ ድልድዩን ከረገጡበት ቅፅበት ጀምሮ እስኪያጠናቅቁ ሰውነታቸው ይንቀጠቀጣል፣ ልባቸውም በኃይል ይመታል፡፡ ‹‹ሰውነቴ ይንዘፈዘፋል፣ ራሴን ያዞረኛል፣ ድልድዩ መሀል ላይ ስደርስም ጭው ይልብኛል፣ ጎርፍ የሚወስደኝ ይመስለኛል፤›› ሲሉ የሚሰማቸውን ለመግለጽ ይሞክራሉ፡፡

ማንኛውም ሰው የአንዳች ነገር ፍርኃት እንደሚኖረው ስለሚያምኑ ፍርኃታቸውን እንደ ችግር አያዩትም፡፡ በቀለበት መንገድ ወይም በድልድዮች ከመጓዝ ራሳቸውን አቅበው ከመኖር ውጪ ይህን ፍርኃት ማስወገድ ይገባኛል ብለውም አያምኑም፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች የወ/ሮ የትነበርሽን ሁኔታ ጌሪሮፎብያ (የድልድይ ፍርኃት) ይሉታል፡፡

የ25 ዓመቷ ወ/ሪት ሜሮን የኋላእሸት የእባብ ፍርኃት (ኦፊዶዩፎብያ) መቼ እንደጀመራት በትክክል ባታውቅም ከምታስታውስበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ፍርኃት አለባት፡፡ በልጅነቷ ቤት ውስጥ ሆና፣ መንገድ ላይ ስትሄድም እባብ ሊመጣባት እንደሚችል ስለምታስብ ትጨነቃለች፡፡ ከፍ ስትል በተደጋጋሚ በህልሟ እባብ ታይ ጀመር፡፡ በእኩለ ለሊት እያለቀሰች ከእንቅልፏ የነቃችባቸው ምሽቶች ጥቂት አይደሉም፡፡ አንድ ሌሊት እባብ መኝታ ክፍሏ ውስጥ ሲገባ በሕልሟ ታያለች፡፡ በነጋታው ጠዋት ቤተሰቦቿ የመኝታ ክፍሏን በር አሽገው፣ ግርግዳ አፍርሰው ሌላ በር እንዲያወጡላት አደረገች፡፡

ዛሬ ድረስ ቤቷን ጨምሮ፣ በተከደኑ ቁሳቁሶች፣ በመፀዳጃ ቤትና ሌሎችም ቦታዎች እባብ እንደሚኖር ስለምታስብ የምትጨናነቅበት ጊዜአት አሉ፡፡ የእባብ ፍርኃቷ አላላውስ የሚላት ጊዜም አለ፡፡ ስለ እባብ ስታስብና ምስሉን እንኳን መመልከት ይረብሻታል፡፡ ከዚህ ቀደም በዕውን ሁለት ጊዜ እባብ የገጠማት ሲሆን፣ ተደናብራ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ምን ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ባለማወቅ ለመሮጥ፣ ለመዝለል ቢቃጣትም ካለችበት መንቀሳቀስ አልቻለችም፡፡

የእባብ ፍርኃቷ በዓለም ላይ የታወቀና ስያሜ ያለው እንደሆነ ያወቀችው በቅርቡ ነው፡፡ በፍርኃቷ ሳቢያ ብዙ ውጣ ውረዶች ቢገጥሟትም፣ መፍትሔ ለመፈለግ መሞከር በራሱ የበለጠ ስለ እባብ እንድታስብ እንደሚያደርጋት ስለምታምን ምንም አላደረገችም፡፡ ቤተሰቦቿና የቅርብ ጓደኞቿ ከፍርሃቷ ለማላቀቅ ሲሉ ቢመክሯትም፣ ስለ እባብ መወራቱ አስጨነቃት እንጂ አላቀለለላትም፡፡ የእባብ ፍርኃቷ በሕይወቷ ማድረግ ከምትፈልጋቸው ብዙ ነገሮች እንዳቀባትም በሐዘኔታ ትገልጻለች፡፡

ፎብያ (ምክንያት አልባ ፍርኃት) ያለባቸውና በሚፈሩት ነገር ሳቢያ የዕለት ተዕለት ውሏቸው የሚበጠበጥ ብዙዎች ናቸው፡፡ ፍርኃት የሚያሳድሩባቸው ነገሮች በእውን ሳይገጥሟቸው ገጥመዋቸውም የሚጨነቁ፣ የሚጠበቡ አሉ፡፡ አንዳንዶች ሐኪም ሲያማክሩ ሌሎች ከፍርኃታቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ምክንያት አልባ ፍርኃቶች ሲኖሩበት መንቀጥቀጥ፣ የልብ ምት መጨመር፣ ራስ ማዞር፣ መተንፈስ አለመቻል፣ ማላብና ሌሎችም የሰውነት ለውጦች ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡

ተመራማሪዎች ከለዩዋቸው ምክንያት አልባ ፍርኃቶች ውስጥ የከፍታ (አክሮፎቢያ)፣ የዱር እንስሳት (አግሪዞፎቢያ)፣ መንገድ የማቋረጥ (አጊሮፎቢያ)፣ የአበባ (አንቶፎቢያ)፣ የበረራ (ኤይሮፎቢያ)፣ የደስታ (ኪሮፎቢያ)፣ የቴክኖሎጂ (ሳይብሮፎቢያ)፣ የአምልኮ ቦታዎች (ኢኖክሎፎቢያ)፣ የማርጀት (ግሮንቶፎቢያ)፣ የፀሐይ (ሒልዩፎቢያ)፣ የመተኛት (ሒፕሮፎቢያ)፣ የፍቅር (ፊሎፎቢያ)ና ልጅ የመውለድ (ቶኰፎቢያ) መጥቀስ ይቻላል፡፡ መሰል ፍርኃቶች ሕይወታቸውን ያመሰቃቀሉባቸው ብዙዎች ቢሆኑም፣ ፍርኃታቸውን ለማስወገድ ባደረጉት ጥረት አንዳች በጎ ነገር የፈጠሩም አይጠፉም፡፡ ለምሳሌ አምፖልን የፈጠረው ቶማስ ኤዲሰን የጨለማ ፍርሃት (ኒክቶፎቢያ) እንደነበረበት ይነገራል፡፡

አቶ መርሻ አበራ 62 ዓመታቸው ሲሆን፣ በሥራቸው ምክንያት በተለያዩ አገሮች ተዘዋውረዋል፡፡ በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ ሩስያ፣ ካይሮ፣ ግሪክ፣ እሥራኤልና ሌሎችም አገሮች ሲጓዙ ከሦስት ፎቅ በዘለለ ሕንፃ ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ በ1984 ዓ.ም. ሠንጋተራ አካባቢ በሚገኘውና በተለምዶ ሞርጌጅ ሕንፃ ተብሎ በሚጠራው የቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ ሕንፃ ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ ከወትሮው የተለየ ስሜት ሳይሰማቸው ሕንፃውን መውጣት ይጀምራሉ፡፡ ወደ አምስተኛ ፎቅ ሲደርሱ ግን እግራቸው ተሳሰረባቸው፡፡ ፎቁ ቢደረመስ የሚል ፍርኃት ያስጨንቃቸው ጀመር፡፡ የሕንፃውን ግድግዳ ደገፍ ሲሉ ከሕንፃው ሥር ውር ውር የሚሉትን መኪኖች ተመለከቱ፡፡ ራሳቸውን ያዞራቸው፣ ያልባቸውም ጀመር፡፡ ደረጃውን ፈጠን ፈጠን እያሉ የሚወጡ ሰዎች ሲመለከቱ እንዴት አይፈሩም ብለው ግራ ተጋቡ፡፡ ፍርኃታቸው ከቁጥጥራቸው ውጪ ሆኖባቸው ስብሰባውን ትተው ወደ ታች መውረዱን ተያያዙት፡፡ ሕንፃውን ለቀው እንደወጡ እፎይታ ተሰማቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከተወሰነ ደረጃ በላይ ሕንፃ አይወጡም፡፡ ከሰዎች ጋር ቀጠሮ ኖሯቸው አልያም ለስብሰባ ሕንፃ መውጣት ግድ ሲሆንባቸው ፎቁን አብሯቸው የሚወጣ ሰው ያፈላልጋሉ፡፡ እንዲህም ፎቅ ከወጡ በኋላ ጥሩ ስሜት ስለማይሰማቸው ጉዳያቸውን ሳያጠናቀቁ የወረዱበት ጊዜም ጥቂት አይደለም፡፡

በአንድ አጋጣሚ የአንድ ሕንፃ ጠባቂ ፎቅ አብሯቸው  እንዲወጣና እንዲወርድ እንደከፈሉት ያስታውሳሉ፡፡ ለሥራ ሆቴል ውስጥ አምስተኛ ፎቅ ላይ አልጋ ተይዞላቸው ሻወር ሊወስዱ ይገባሉ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ መቆየት ግን አልቻሉም፡፡ በፍጥነት ወደ አልጋቸው መሔድ ግድ ሆነባቸው፡፡ ሁሌም ውስጣቸው ሕንፃ እንደሚደረመስ ስለሚነግራቸው በፍርኃት ይሞላሉ፡፡ ብዙ ሰዎች ያለ ፍርኃት ሕንፃ ይወጣሉ ዘመን አመጣሽ ሊፍቶችም አደጋ አያደርሱም እያሉ ራሳቸውን ለማጽናናት ቢጣጣሩም አይሳካላቸውም፡፡

ከጥቂት ጓደኞቻቸው ውጪ ቤተሰቦቻቸውና ሌሎች ወዳጆቻቸው ስለ ፍርኃታቸው አያውቁም፡፡ ሰዎች ፍርኃታቸውን እንደሚረዱላቸውም አያስቡም፡፡ ፍርኃታቸው በሥራቸው ተፅዕኖ ቢያሳድርም እንኳን እስካሁን መፍትሔ አላፈላለጉም፡፡ ረዣዥም ፎቆችን አለመውጣትን እንደተሻለ አማራጭ ይዘዋል፡፡

ከአቶ መርሻ በተቃራኒው ለፍርኃቱ መፍትሔ እንዳገኘ የሚናገረው የ33 ዓመቱ መምህር ሕንፃ አረፋይኔ ነው፡፡ የተወለደው ዛላንበሳ ሲሆን፣ በወጣትነቱ ቀይ ባህርን አቋርጦ ወደ አስመራና ምፅዋ አዘውትሮ ይሄድ ነበር፡፡ ቀይ ባህር ውስጥ አሳ ነባሪ አለ ቢባልም ከመዋኘት ወደ ኋላ አይልም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ምን እንደመታው ባያስታውስም ባህሩ አካባቢ ሳለ እግሩ ይጎዳል፡፡ ከዛ በኋላ ለውኃ መጥፎ ስሜት እንዳደረበት ይናገራል፡፡

ባህር ወይም ሐይቅ ይቅርና ብርጭቆ ውስጥ ያለ ውኃ ሲመለከት መረበሽ ጀመረ፡፡ ብርጭቆ በእጁ ይዞ በብርጭቆው ያለው የውኃ መጠን በዝቶ ይታየዋል፡፡ በፍርኃት ለቋቸው የተሰበሩ ብርጭቆዎች ብዙ ናቸው፡፡ ለረዥም ጊዜ ሰውነቱን መታጠብም ይከብደው ነበር፡፡ ሰውነቱ ላይ የሚወርደው ውኃ ዓይኖቹን ሲጋርደው ባህር ውስጥ እንዳለ ስለሚሰማው በፍጥነት ይወጣል፡፡ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት አደጋ እንደሚያደርሱበት ስለሚያምንም ሁሌ ይሰጋል፡፡

ፍርሃቱን ያካፈለው ሰው ግን አልነበረም፡፡ ሰዎች ደካማ ጎኑን ካወቁ የሚንቁት ይመስለው ነበር፡፡ አንዳንዶች ፍርኃቱን ባለመገንዘብ ከመቀናጣት ጋር እንደሚያያይዙት ይገምታል፡፡ ለዓመታት ከተሰቃየ በኋላ መፍትሔ ያገኘው ኮተቤ መምህራን ኮሌጅን ሲቀላቀል ነው፡፡ የሥነ ልቦና ትምህርት ሲወስድ የውኃ ፍርኃት (ሐይድሮፎቢያ) እንዳለበት ስላወቀ መፍትሔ ለማግኘት መጻሕፍት ማንበብ ጀመረ፡፡

ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርኃትን ለማስወገድ የሚረዱ ንድፈ ሐሳቦችን እያጠና በራሱ ላይ ሙከራ ማድረግም ጀመረ፡፡ ከሙከራዎቹ አንዱ ፍርኃቱን መጋፈጥ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ባቦጋያ ሐይቅ ላይ በጀልባ እየተጓዘ ልብሱንና ጫማውን ሳያወልቅ ወደ ውኃው ዘሎ ገባ፡፡ የልብሱና ጫማው ክብደት ውኃው ወደ ታች እንዲጎትተው እንደሚያደርግ ቢያውቅም፣ ደፍሮ መግባቱ ፍርኃቱን በመጠኑ እንደቀረፈለት ይናገራል፡፡ የሚረብሹትን የውኃ ውስጥ እንስሳት በበጎ መንገድ ማየት እንዲችል ለማድረግ፣ ስለ እንስሳት መልካም ነገር እየተናገረ ራሱን ይቀዳና በሚተኛበት ወቅት ይከፍተዋል፡፡ ይህ አዕምሮው አሉታዊ ሐሳቡን እንዲለውጥ እንዳገዘውም ይገልጻል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመዋኘትም የመታጠብም ችግር የለበትም፡፡ ከውኃ ጋር የተያያዙ ጥናቶችን እያነበበም ይመራመራል፡፡ በእሱ እምነት፣ ሰዎች የሚያስፈሯቸውን ነገሮች ተጋፍጠው በተቃራኒው ለበጎ ነገር ማዋል ይችላሉ፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርነው ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት ቃልኪዳን አድማሱ፣ ፎቢያ (ምክንያት አልባ ፍርኃት) ነገሮች ከሆኑት በላይ አጋንኖ ይሆናሉ ብሎ መፍራት ነው፡፡ ፍርኃቱ አንዳች አጋጣሚን መነሻ በማድረግ አልያም ባልተጨበጠ ምክንያት ሊፈጠር ይችላል፡፡ የሚፈሩትን ነገር ተጋፍጠው የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ሁሉ፣ ሙሉ በሙሉ ሽሽትን የሚመርጡም አሉ፡፡ ሰዎች የአንድ ነገር ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርኃት እንዳለባቸው ከሞከሩበት በኋላ ወይም ሳይገጥማቸው ሊያውቁ ይችላሉ፡፡

ጀነራላይዝድ ፎብያ ጠቅለል ያለ ፍርሃት ሲሆን፣ ስፔስፊክ ፎብያ የውስን ነገሮች ፍርኃት ነው፡፡ ስፔስፊክ ፎብያ የሚባሉት ከ90 በላይ ናቸው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ከእነዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚገጥሙት የተለያዩ የእንስሳቶች ፍርኃት፣ የከፍታ ፍርኃት (አክሮፎቢያ)፣ የደም ፍርኃት (ሔሞፎቢያ) እና ሰዎች በርከት ባሉባቸው አካባቢዎች የመናገር ፍርኃት (ሶሻል ፎብያ) ናቸው፡፡ ሌሎችም ምክንያት አልባ ፍርኃቶች ቢኖሩም፣ ፍርኃት እንደ ችግር ስለማይወሰድ ወደ አደባባይ የሚወጡበት አጋጣሚ አናሳ ነው፡፡

ችግር እንዳለባቸው ተገንዝበው ወደ ሕክምና ባለሙያ የሚሄዱ ሰዎች ጥቂት ሲሆኑ፣ ፍርኃታቸው በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው እየተጫናቸው የሚሰቃዩት ያመዝናሉ ይላል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ሰዎች ችግሩን ያቀሉታል፤ ፍርሃት ያለባቸው ሰዎችንም አይረዷቸውም፤ በዚህ ሁኔታ ችግራቸው ሊባባስም ይችላል፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሠሩ ተጨባጭ ጥናቶች ባይኖሩም በሌሎች አገሮች የተሠሩት፣  ብዙዎች ለምክንያት አልባ ፍርኃት እንደሚጋለጡ ያሳያሉ፡፡ ካሉት ከ90 በላይ የሚሆኑ የፍርኃት ዓይነቶች ቢያንስ አንዱ የሌለበት ሰው የለም ለማለት ይቻላል፡፡ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አንዳንዶቹ ዓይነቶች የማይከሰቱበት አልያም ከሰዎች አኗኗር ጋር በመዋሃድ ቀላል የሚሆኑበት ጊዜ አለ፡፡

ምክንያት አልባ ፍርኃትን ለማስወገድ ጥቅም ላይ ከሚውሉ የሕክምና መንገዶች መካከል አንቲ አንዛይቲ (ከውጥረት የሚያረጋጉ መድሐኒቶች)ና ሳይኮቴራፒ (የሥነ ልቦና ሕክምና) ይጠቀሳሉ፡፡ ኮግኒቲቭ ቢሄቭየራል ቴራፒ (ሲቢቲ) ሰዎች ከሚፈሯቸው ነገሮች ጋር ያያያዟቸውን አሉታዊ ነገሮች በአወንታዊ ለመለወጥ የሚያገለግል ሕክምና ነው፡፡ ቢሄቭየራል (የባህሪ ሕክምና) ሰዎች ስለአንድ ነገር ያላቸውን ፍርኃት አስወግዶ አለመፍራትን የማስተማር መንገድ ነው፡፡ ሰዎች የሚፈሯቸውን ነገሮች ቀስ በቀስ የማለማመድ ሒደት ደግሞ ኢንዲጎ ኤክስፖዥር ይባላል፡፡ ፍለዲንግ ሰዎች የሚፈሩትን ነገር በአንድ ጊዜ እንዲጋፈጡ የሚደረግበት መንገድ ነው፡፡ አዕምሮ ፍርኃቱ ምክንያት አልባ እንደሆነ ሲገነዘብ ፍርኃቱ ሊለቅ እንደሚችል ባለሙያው ይናገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...