Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤምባሲዎችን ካርታ ለማምከን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋገረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤምባሲዎችን ካርታ ለማምከን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋገረ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተለያዩ ግንባታዎች መሬት ከሊዝ ነፃ ወስደው ሳያለሙ ለዓመታት አጥረው ያስቀመጡ 18 ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ይዞታ ላይ በሚወሰደው ዕርምጃ ላይ፣ ባለፈው ሳምንት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋገረ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በጠራው ስብሰባ ላይ የተገኙት የከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊዎች፣ ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የወሰዱትን መሬት ባለማልማታቸው የሚወሰደውን ዕርምጃ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በመሬት ጉዳዮች ላይ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ለከተማው ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት ላይ ግንባታ ካላካሄዱ ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመነጋገር የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ፣ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማልማት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ መሬቱን ለመንግሥት እንዲያስረክቡና ለልማት ዝግጁ ሲሆኑ ደግሞ ሌላ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው የመፍትሔ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡

ይህ የመፍትሔ ሐሳብ ከቀረበ ከሦስት ወራት በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋግሯል፡፡ የከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለኤምባሲዎች፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለመንግሥትና ለግል ኩባንያዎች፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች በአጠቃላይ የሰጠው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ኅዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም. አብቅቷል፡፡

ለረዥም ዓመታት ያለምንም ግንባታ ከቆዩ ቦታዎች መካከል ለሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ የተሰጠው ቦታ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ቦታ በአፍሪካ ጎዳና (ቦሌ መንገድ) በፍሬንድሽፕና በዓለም ሕንፃ መካከል የሚገኝ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 8,000 ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡ ሳዑዲ ኤምባሲ ይህን ቦታ በ1987 ዓ.ም. የተረከበ ቢሆንም፣ ዋና መንገድ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ለፀጥታ ምቹ አይደለም በሚል ምክንያት ለከተማ ለአስተዳደሩ መልሶ አስረክቦ ነበር፡፡ አስተዳደሩም ለአትሌት ጌጤ ዋሚና ለአትሌት ስለሺ ስህን አከፋፍሎ ሰጥቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ኤምባሲው በድጋሚ መሬቱን በመጠየቁ አስተዳደሩ ከአትሌቶቹ ነጥቆ ለኤምባሲው መልሶ አስረክቧል፡፡ ነገር ግን ለ23 ዓመታት ምንም ዓይነት ግንባታ ሳይካሄድ ቦታው ያለ ሥራ ታጥሮ ይገኛል፡፡ ከኤምባሲዎች በተጨማሪ አስተዳደሩ 11 ለሚሆኑ ለመንግሥታዊ ተቋማት የሰጠውን ቦታ ሙሉ ለሙሉ ነጥቆ ወደ መሬት ባንክ ማስገባቱ ታውቋል፡፡

አስተዳደሩ አሁንም ቢሆን የግል ኩባንያዎችን ይዞታም ከሥር ከሥር ካርታ እያመከነ ቢሆንም ለሚድሮክ ይዞታዎች ግን ጊዜ ሰጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠራው ውይይት ላይ ታጥረው የተቀመጡ ይዞታዎች ጉዳይ ከፍተኛ ምሬት ያለበት ትችት የቀረበ ሲሆን፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርጋሞ ሀማሞና የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል አልይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ጀማል በሰጡት ምላሽ፣ ሼክ መሐመድ አል አሙዲ አገር ውስጥ ባለመሆናቸው በመመርያው መሠረት ዕርምጃ ሊወሰድ አልቻለም፡፡ ‹‹ምክንያቱም ሼክ አል አሙዲ ከመንግሥት ቀጥሎ በርካታ ኢንቨስትመንት ውስጥ የገቡና በርካታ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ልማታዊ ባለሀብት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት ቀድመው የሚደርሱ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት የእሳቸውን ይዞታ መንካት አያስፈልግም፡፡ አስተዳደሩ ዕርምጃው እንዲዘገይ ወስኗል፤›› በማለት አቶ ጀማል ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰባቢ አቶ ጳውሎስ ደጉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሬት የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ያለሥራ ታጥሮ መቀመጥ የለበትም፡፡ ‹‹ከዚህ አንፃር በተቻለ መጠን ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ሥራ ላይ ውለው በአሁኑ ወቅት ማልማት ያልቻሉ ባለይዞታዎች፣ ማልማት በሚችሉበት ወቅት ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው ሐሳብ አቅርበናል፤›› ሲሉ አቶ ጳውሎስ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...