- ሰው ሠራሽ ሐይቅ ለመገንባት ታቅዷል
የአንድ መቶ ዓመት ዕድሜ ያላትን የአዳማ ከተማን አሁን ካለችበት በእጥፍ እንደሚያሳድግ የታመነበትን አዲስ ማስተር ፕላን፣ የከተማዋ አስተዳደር አዘጋጅቶ ለውይይት አቀረበ፡፡
የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጫላ በቀለ ለሪፖርተር እንገደለጹት፣ የከተማ አስተዳደሩ የአዲሱን ማስተር ፕላን ዝግጅት አጠናቆ ለከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት ለውይይት አቅርቧል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች በረቂቅ ማስተር ፕላኑ ላይ የሰጡት አስተያየት ተካቶ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ አቶ ጫላ አስረድተዋል፡፡
ከ500,000 በላይ ሕዝብ ብዛት ያላት አዳማ ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ13,000 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈች ከተማ ነች፡፡ አዲስ የተዘጋጀው ማስተር ፕላን የከተማዋን ስፋት ወደ 33,000 ሔክታር እንደሚያሳድግ ተገልጿል፡፡
አዲሱን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ 20,000 ሔክታር መሬት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ጫላ፣ ከአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳዳሪዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ከአካባቢያቸው የሚነሱ አርሶ አደሮች ካሉ በስምምነት ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው የመልሶ ማስፈር ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ ዓመታት አዲስ መሬት ማስፋት ብቻ ሳይሆን መልሶ ማልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
ለአዲሱ ማስተር ፕላን ትግበራ የሚፈለገው መሬት 30 በመቶ ለአረንጓዴ ልማት፣ 30 በመቶ ለመሠረተ ልማት፣ 40 በመቶ ለግንባታ እንዲውል መታቀዱን የገለጹት አቶ ጫላ፣ ለከተማዋ ውበትና የቱሪዝም ልማት የሚያግዝ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ለመገንባት እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ የተመሠረተችበትን 100ኛ ዓመት ያከበረችው የአዳማ ከተማ ‹‹የስምጥ ሸለቆ እንቁ›› በመባል ትታወቃለች፡፡ በደማቅ የንግድ እንቅስቃሴ የምትታወቀው አዳማ በሶደሬ ሪዞርት፣ ከተማ ውስጥ ባሉ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎችና ሎጆች ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ከተማ እንደሆነች ይነገራል፡፡
አዲስ የተዘጋጀው ማስተር ፕላን የንግድ፣ የመኖሪያና የኢንዱስትሪ ልማት የሚካሄድባቸውን ቦታዎች ለይቶ ማስቀመጡን አቶ ጫላ ተናግረዋል፡፡ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን መሠረት ልማቶች በመገንባት ላይ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የንፁህ የውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት የተከናወነ ሲሆን፣ በቅርቡ ሦስት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ተገንብቶ ተመርቋል፡፡ የአራት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት ላይ እንደሆነ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ በርካታ የኮብልስቶን መንገዶች መገንባታቸውን የገለጹት አቶ ጫላ፣ ቀስ በቀስ የተወሰኑ የኮብልስቶን መንገዶች በአስፋልት መንገዶች እንደሚለወጡ አስረድተዋል፡፡
የአገልግሎት ዘርፍ የከተማዋን የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመራ ቆይቷል፡፡ በቀጣይ በንግድ፣ በአምራች ዘርፍና በኮንፈረንስ ቱሪዝም ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የገጠመው ትልቅ ፈተና የወጣቶች ሥራ አጥነት መሆኑን የገለጹት አቶ ጫላ፣ በቀጣይ አስተዳደሩ በወጣቶች ሥራ ፈጠራ ላይ ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ 9,000 ያህል ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት አቶ ጫላ፣ በቅርቡ የሚመረቀው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኩ የተገነባው የቻይናው የሰንሻይን ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ከመጪው ሰኔ ጀምሮ 2,000 ያህል ሠራተኞች እንደሚቀጥር ታውቋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ለ80,000 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡
የአዳማ ከተማ አስተዳደር የገቢ ማሰባሰብ አፈጻጸሙን በማሻሻል በአሁኑ ወቅት በዓመት አንድ ቢሊዮን ብር መደበኛ ገቢ እንደሚሰበስብ የገለጹት አቶ ጫላ፣ ከተማዋን በኢትዮ ጂቡቲ ኮሪደር ላይ ስለምትገኝ፣ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኢትዮ ጂቢቲ የምድር ባቡር ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ዕድገት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት አስታውቀዋል፡፡
በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው አዲሱ የአዳማ ከተማ አስተዳዳር ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ ከጀመረ ወዲህ፣ በመልካም አስተዳዳር ትልቅ መሻሻል እንደታየ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡