Wednesday, February 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለበጎ የታሰበው ክፋት እንዳያበላሸው!

በመላ አገሪቷ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ኢትዮጵያውያን በተስፋ ተሞልተው የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ መሆናቸው፣ አገሩን ለሚወድ ማንኛውም ሰው ዕፎይታ ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ አብረው ለመሠለፍ የሚያስችላቸው ጅማሬ እየታየ በመሆኑ፣ ብዙዎች መጪውን ጊዜ በብሩህ ተስፋ ተሞልተው ቢጠብቁ አይገርምም፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በነውጥና በሁከት ውስጥ የነበረች አገር የሰላም ንፋስ እየነፈሰባት ኢትዮጵያውያን አገራቸው የፍትሕ፣ የዴሞክራሲ፣ የልማትና የብልፅግና አምባ እንድትሆን ይመኛሉ፡፡ በተለይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመጀመርያውን ታሪካዊ ንግግር በፓርላማ ካደረጉ በኋላ፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአካል በመገኘት እየተወያዩ ነው፡፡ በጅግጅጋ፣ በአምቦና በመለ ከተሞች ከሕዝብ ተወካዮች ጋር ከመነጋራቸውም በላይ፣ በአዲስ አበባ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር፣ እንዲሁም ከመላ አገሪቱ ከተውጣጡ 25 ሺሕ ወጣቶች ጋር ተገናኝተው ሐሳብ መለዋወጣቸው በጎ ጅምር ነው፡፡ ይህ ጅምር ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋርም ቀጥሏል፡፡ ሕዝብን በቀጥታና በሚወክሉት በኩል በማግኘት ማነጋገር ባህል መሆን አለበት፡፡ ይህ በጎ ጅምር እንዳይበላሽ ደግሞ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ ላለፉት 27 ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ ሲቆይ እጅግ የመረረ ተቃውሞ ያጋጠመው ባለፉት ሦስት ዓመታት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ብቅ ጥልቅ የሚሉ የዜጎችን ሕይወት ያጠፉ የተለያዩ ተቃውሞዎች ቢታዩም፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት ግን በመጠናቸውም ሆነ በገጽታቸው የከበዱ ነበሩ፡፡ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርካታ ዜጎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በግጭቶች ምክንያት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ መጠኑ የማይታወቅ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ከአንዴም ሁለቴ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ አገሪቷ ከመቼውም ጊዜ በላይ መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆና ህልውናዋ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡ የአገሪቱ ሕዝብም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሰንብቷል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ውጥንቅጥ ውስጥ ለመውጣት በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጭምር ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ትግል ተደርጎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመሪነት እርካቡን ተቆናጠው ልጓሙን ጨብጠዋል፡፡ በዚህ ወቅትም ከስህተት በመማር አገርን መካስ እንደሚያስፈልግ፣ ኢትዮጵያ የሁሉም አገርና ቤት እንደሆነች፣ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲና ነፃነት እንደሚገባቸው፣ ወጣቶች ለአገራቸው እንዲቆሙ፣ ፋታ የማይሰጡ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን፣ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ የፍቅርና የይቅርታ መሆን እንደሚገባው፣ በአገር ጉዳይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ አብረው መሠለፍ እንዳለባቸው፣ ወዘተ. ጉዳዮች ላይ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል፡፡

‹‹ጥሩ እንድታገኝ ጥሩ ተመኝ›› እንደሚባለው ለአገር በጎ ነገሮች ሲታሰቡ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያንን ያስደስታል፡፡ ነገር ግን የአገር የጋራ ጉዳይን እንደ ፀጉር በመሰንጠቅና ጨለምተኛ በመሆን መልካም ጅማሬዎችን ለማደብዘዝ መሞከር ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይ የብሔር፣ የሃይማኖትና የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶችን እየታከኩ የጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዳይፈጠር ማደናቀፍ ለአገር አይጠቅምም፡፡ በጎነት በክፋት ሲከበብ የምትጎዳው አገር ናት፡፡ የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት እንዳልሆነ ሁሉ፣ ልዩነት ማለት ደግሞ የመጠፋፋት ተቃርኖ አይደለም፡፡ የሐሳብ የበላይነት ሊኖር የሚችለው በነፃ ውድድር ፉክክር በማድረግ የሕዝብን ልብ መግዛት ሲቻል ነው፡፡ በር ዘግቶ በመዶለት ወይም በማሴር ሳይሆን በአደባባይ ለሕዝብ ዓላማን አስረድቶ ተቀባይነት ማግኘት ሲቻል ነው፡፡ ሕዝባዊ ነኝ ማለት የሚቻለውም ለሕዝብ ፍላጎት በመገዛት ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአሻጥርና ከሴራ  የዞረ ድምር ፖለቲካ መገላገል ይኖርበታል፡፡ ማታለልና ማጭበርበር፣ አድርባይነትና አስመሳይነት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገለል ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ በጎነትን በክፋት የሚያበላሹ ከንቱ ድርጊቶች ናቸውና፡፡

በኢትዮጵያ ምድር አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከተፈለገ ዜጎች በነፃነት ሐሳባቸውን ይግለጹ፣ በነፃነት ይደራጁ፣ የመሰላቸውን ይደግፉ፣ የማይፈልጉትን ይቃወሙ፣ በፍትሕ ፊት እኩል መሆናቸው ይረጋገጥ፣ ሕገወጥና ብልሹ አሠራሮች ይወገዱ፣ የሕግ የበላይነት ይስፈን፣ ዜጎች በፈለጉት ሥፍራ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብታቸው በተግባር ይረጋገጥ፡፡ ዜጎች ሰላማዊና ሕጋዊ በመሆን ለአገራቸው በኃላፊነት ስሜት የሚሠሩበት ዓውድ ይመቻች፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ይወገዱ፡፡ በሥልጣን መባለግ የማይቻልበት ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ይረጋገጥ፡፡ በሕግ ዋስትና ያገኙ መብቶች በሙሉ ሥራ ላይ ይዋሉ፡፡ ‹‹. . .  ዴሞክራሲ ያለነፃነት አይታሰብም፡፡ ነፃነት ከመንግሥት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም፡፡ ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ፀጋ እንጂ. . .፡፡›› እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት አሠራሩ ሕጋዊ ብቻ ሆኖ ዜጎች በነፃነት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ አለበት፡፡ በነፃነት ሐሳባቸውን ያንፀባርቁ ዘንድም በሩን በስፋት መክፈት ይኖርበታል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ክፋት በጎነትን ማሸነፍ አይችልም፡፡ መጪዎቹ ሁለት ዓመታት በዚህ መንገድ ከተከናወኑ ኢትዮጵያ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ በአስገራሚ ሁኔታ ማከናወን ትችላለች፡፡ እግረ መንገዷን የተበላሸ ገጽታዋንም ታድሳለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊታቸው በርካታ ሥራዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ ሕዝብም ብዙ ነገር ይጠብቃል፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች በመዘርዘር ሐሳብ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባው ማሳሰቢያዎቹ ኃላፊነት የተሞላባቸው እንዲሆኑ ነው፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚቀርቡ ማሳሰቢያዎች የኢትዮጵያን አስቸጋሪና ውስብስብ ፖለቲካ ያመዛዘኑና የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ አንገብጋቢ የሚባሉ አጣዳፊ ጉዳዮች ቅድሚያ ቢያገኙ ተመራጭ ነው፡፡ በሒደት ደግሞ በቅደም ተከተል የሚፈቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ማጤንም ተገቢ ነው፡፡ ከጠባብ ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች በመላቀቅ አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረብ አለባቸው፡፡ በፖለቲካ ቀውሱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች መልሰው እንዲቋቋሙ፣ ከፍተኛ እክል ያጋጠመው ኢኮኖሚ እንዲያገግም፣ ለዓመታት የተዘጋው የፖለቲካ ምኅዳር እንዲከፈት፣ ከእስር መለቀቅ ያለባቸው ዜጎች እንዲፈቱ፣ ነፃ የሐሳብ ልውውጦችና ውይይቶች በስፋት እንዲጀመሩ፣ ወዘተ. በጎ ሆኖ መቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ከክፋት የሚገኘው ጥፋት ብቻ ነው፡፡

አሁን ጊዜው የተግባር መሆን አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡዋቸው በተግባር ይረጋገጡ ዘንድ መጠነ ሰፊ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነት አፅንኦት ያስፈልገዋል፡፡ ከሕግ በላይ መሆን አገር እንደሚያበላሽ በሚገባ ታይቷል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲጠፋ ግለሰቦች ሕግ ይሆናሉ፡፡ ሕግ የተበዳዮች ጋሻ መሆን ሲገባው የበዳዮች መሣሪያ ይሆናል፡፡ ዘረፋና ሌብነት አገር ይለበልባሉ፡፡ ዜጎችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር ያደርጋሉ፡፡ መብታቸውን ሲጠይቁ ምላሹ ዱላ ይሆናል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሥና አገር ቀውስ ውስጥ ትዘፈቃለች፡፡ የሕግ የበላይነት ካልኖረ ሕጎች ማጥቂያ ስለሚሆኑ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ አገር በሕግ የበላይነት ሥር ካልተመራች ክፉ ነገሮች በበጎነት ላይ ጥላቸውን እያጠሉ ለሕዝብ መቅሰፍት ይሆናሉ፡፡ አዲሱ የለውጥ ንፋስ በርትቶና ጠንክሮ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ጉዳያቸው አንድ ላይ መቆምን ባህል እንዲያደርጉ የሁሉም ወገን ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ መጠራጠርና ነገሮችን በትኩረት መከታተል የሰው ልጅ ባህሪ ቢሆንም፣ ከስሜታዊነት በመላቀቅ በምክንያታዊ አስተሳሰቦች መታገዝ የግድ ይላል፡፡ ተጠራጣሪነት በጨለምተኝነት ከታገዘ አንድ ዕርምጃ መራመድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን የለውጡ ጀልባ ቀዛፊ በመሆን የድርሻን እያዋጡ ስህተትን ማረም ግን ረዥም ርቀት ያስኬዳል፡፡ በእሳትና በጭድ ተቃርኖ ውስጥ ሆኖ መጪውን ጊዜ ድንግዝግዝ ከማድረግ፣ በልዩነት ውስጥ ሆኖ ለጋራ ጉዳይ አንድ መሆን እንደሚቻል ማሳየት የትውልዱ ኃላፊነት ነው፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለምና፡፡ በመሆኑም ለበጎ የታሰበው ክፋት እንዳያበላሸው መጠንቀቅ ይበጃል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...