Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያም ያለ ትግራይ ትርጉም የላቸውም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ...

‹‹ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያም ያለ ትግራይ ትርጉም የላቸውም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያደረጉ የሚገኘውን ጉዞ ዓርብ ሚያዝያ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በመቀጠል መቐለ ከተማ ተገኝተው ለከተማው ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸው በዚህም ትግራይና ኢትዮጵያ የተሳሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያም ያለ ትግራይ ትርጉም የላቸውም፤›› ብለዋል፡፡

ትግራይ የጥበብ ወላጅ መሆኗን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትልልቅ ምሁራንና ነገሥታትን ያፈራች የአክሱም ጽዮንና የአብርሃ ወአፅብሃ ባለቤት እንደሆነች ተናግረዋል፡፡ ትግራይ ከሃይማኖት አልፈው የማንነት መገለጫ የሆኑት የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች ለመጀመርያ ጊዜ የገቡባት መሆኗን ገልጸው፣ የመላው ጥቁር ሕዝብና የነፃነትና የእኩልነት ደጋፊዎች ኩራት የሆነችው ዓድዋ የምትገኝበት መሆኗን አውስተዋል፡፡

ትግራይ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ መሠረት መሆኗንም ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በአገሪቱ ባጋጠሙ የፖለቲካ ግጭቶች፣ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተፈጠሩ ችግሮች እንዳዘኑ ገልጸው፣ ይህ ድርጊት እንዳይደገም አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ‹‹የትግራይ ሕዝብ አገሩን ከልቡ አውጥቶ የማያውቅና በክፉም ሆነ በመልካም ጊዜ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደነበረበት እንዲመለስ፣ መንግሥታቸው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ልዩነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተቻለውን እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

የስብሰባው ተሳታፊዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡ አንዷ ተሳታፊም፣ ኢሕአዴግ አገሪቷ ለገባችበት ቀውስ የአመራር ቁርጠኝነትን እንደ ችግር መጥቀሱ ተገቢ አይደለም በማለት ተችተዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የድርጅቱ አመራሮች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ጫካ መግባታቸው የቁርጠኝነት ችግር ስለሌለባቸው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ተሳታፊዋ ‹‹ቀድሞ የሕይወት ቁርጠኝነት የነበራቸው ታጋዮች አሁን እንዴት የውሳኔ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው አልቻሉም?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ትናንትና የነፃነት መሪ የነበራችሁ ዛሬ የሰላም፣ የዴሞራሲና የአንድነት መሪ መሆን እንዴት ተሳናችሁ?›› ብለዋል፡፡

የክልሉ አመራሮች በሌብነት ለዚያውም በሕዝብ ላይ በሚደረግ ሌብነት ላይ ቆመው መደራደራቸው እንደሚያስተዛዝብ ገልጸው፣ አመራሮቹ ራሳቸውን ማጥራት ካለባቸው በቃል ሳይሆን ከልብና በተግባራቸው ራሳቸውን እንዲያድሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ መቐለ ከማምራታቸው በፊት ሐሙስ ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማኅበራትን ተወካዮችንና ታዋቂ ሰዎችን በቤተ መንግሥት እራት ጋብዘዋል፡፡

በዚህ ወቅት ሰላማዊ የትግል ሥልት የሥልጣንና የዘመናዊነት መገለጫ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ያለ ጠንካራ የተፎካካሪ ፓርቲ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ግንባታ የትም እንደማያደርስ በመግለጽ ለዚህ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

ኢሕአዴግ ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው ካደረጉ ማናቸውም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...